Artcles

ሰንደቅ ዓላማችንን አክብረን እናስከብር

By Admin

October 14, 2017

 

ሰንደቅ ዓላማችንን አክብረን እናስከብር! ዘአማን በላይ 10ኛው የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተከበረ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል። ሰንደቅ ዓላማን ቀን ስናከብር በተለምደ ‘ባንዴራ’ እየተባለ የሚጠራው ስለ ሰንደቃችን ክብር ማውሳት ያስፈልጋል። ሰንደቅ ዓላማ ክብር ያለውና በህገ መንግስቱ መሰረት የአሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲተገበር ተስማምተው እውን ያደረጉት ነው።

የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተቻችለውና ተፈቃቅደው የሚኖሩባት፣ ከ75 በላይ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ባለቤት የሆነች፣ ህዝቦቿ ተከባብረውና ተሳስበው እንዲሁም በችግርም ሆነ በደስታ ብሎም በክፉ ቀን በአብሮነት የሚኖሩባት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ልጆች መሆናችን የሚንፀባረቀው በሰንደቅ ዓላማው ውስጥ ነው። ሰንደቅ ዓላማችን የትላንት ማንነታዊ አሻራችን መገለጫ ነው። ርግጥ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅት ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ነፃ የነበሩት ሁለት ብቻ ነበሩ። ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ ናት። ብዙዎች የአፍሪካ አገሮች ነፃ ከወጡ በኋላ የኢትዮጵያን ባንዲራ ቅጂ ለመውሰድ ሞክረዋል— ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነትና የክብር ተምሣሌት ስለሆነ።

ቀድማ በሀገሯ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ልብ ውስጥ የተሰቀለችና የተውለበለበች ብቸኛ ኩሩና የቀዳሚ ድል ዓርማና ምሣሌ፣ የመላው አፍሪካውያን ጌጥ ሆና የታየች ይህች የኛ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ናት። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እድለኛነቷም ምንጩ እዚሁ ውስጥ ያለ ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት አገራዊ ጉዳይ ሲነሳ ሰንደቅ ዓለማውን አስቀድሞና ከፍ አድርጎ በመያዝ ታላቅነቱን ያስታውሳል። እርግጥም ‘ሰንደቅ ዓላማችንን እናክብር’ ሲባል፤ ትናንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት ብለው በጀግንነት ለወደቁት እንዲሁም ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው እንድንኖር ላበቁን ጀግኖች አያቶቻችንና አባቶቻችን እንዲሁም ሞተው ላስከበሩን ውድ የህዝብ ልጆች ክብር ይሁን ማለት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ለኢትዮጵያና ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነት ለወደቁት ሰማዕታት ሁሉ የላቀውና የደመቀው ክብር ይድረሳቸው ማለትም ነው።

እናም ወጣቱ ትውልድ ሰንደቅ ዓላማውን ሲያስብ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን መገንዘብ አለበት። ስለ ሰንደቅ ዓላማው አንዳችም ግንዛቤ ሳይዝ በጭፍኑ የህገ ወጦችን፣ የፀረ-ሰላም ሃይሎችንና የአሸባሪዎችን አሉባልታ በመስማት በስሜት መነዳት የለበትም። ወጣቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዕውን ለማደረግ ውድ የህዝብ ልጆች ባካሄዱት እልህ አስጨራሽና መራር ትግል መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን ማሳለፋቸውን ማወቅ አለበት። ይህ ትግላቸውም በ1988 ዓ.ም በቁጥር 16/1988 ‘የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ’ እንዲወጣ መሰረት ጥለዋል። ሰንደቅ ዓላማው ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን ውድ የህዝብ ልጆች ደማቸውን ዋጅተውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡን ብርቅዬ ሃብታችን ነው። የማንነታችን መገለጫም ጭምር።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሰማዕታቱን አደራ ተቀብለው በተለይም ላለፉት 22 ዓመታት በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ተሰባስበው አያሌ ሀገራዊ ተግራትን ፈፅመዋል። ሁሉን አቀፍ ዕድገት እያስመዘገቡም ዛሬ ላይ መድረስ ችለዋል። ይህ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ትሩፋት ሊገኝ የቻለው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት እየተመሩ ብዝሃነታቸውን የጥንካሬያቸው ምንጭ አድርገው በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ሌት ተቀን በመስራታቸው መሆኑን እንደምትገነዘቡልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ርግጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልዩነቱን የጥንካሬው መሰረት አድርጎ በመቁጠር በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስቦ ድህነትን ለማሸነፍ ላለፉት ዓመታት ታግሏል። የውጤት ባለቤት በመሆንም ለህዳሴው መደላድል ለማኖር ደፋ ቀና እያለ ነው። ዛሬ የብዝሃነት ድር ድህነትን እጅ ከወርች ጠፍሮ በማሰር ላይ ነው፤ የዘመናት የሃፍረት መለያ የሆነውንና ቀና ብሎ እንዳይሄድ አንገቱን ያስደፋውን ቀንደኛ ጠላቱን መልሶ አንገቱን እያስደፋው ነው። ህዝቡ በሁሉም የልማት ዘርፎች ከጫፍ እሰከ ጫፍ በመንቀሳቀስ በሰንደቅ ዓላማው አጊጦና አሸብርቆ የትናንት የውርደት ምንጩን ዛሬ ላይ ድል በመንሳት ወደ ፊት እየገሰገሰ ነው፤ የማይቀረውን የዕድገት ተስፋ በቅርብ ርቀት እያየም ነው። ብዝሃነቱ የድሉ ምንጭ እንጂ የልዩነቱና የመፋለሱ ምክንያት እንዳልሆነ ላለፉት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት በተግባራዊ ክንዋኔው ያረጋገጠው ይህ ህዝብ፤ ነገም ይህን ጥንካሬውን አጠናክሮ በመቀጠል ድሉን ይበልጥ ማስፋፋቱ አይቀሬ ነው። ይህን የሰንደቅ ዓላማውን ፋይዳ ወጣቱ ትውልድ በሚገባ መገንዘብ ይኖርበታል። ወጣቱ የነገ ተስፋውን መሰነቅ የሚችለው በሰንደቅ ዓላማው ስር በመሆን እንጂ በህገ ወጦች ተገፋፍቶ በሚያከናውነው ፀረ-የሰንደቅ ዓላማ ዲስኩር አይደለም። የወጣቱ ተስፋ የሆነው የሀገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ እውን የሚሆነው በኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ስር እንጂ ፀረ-ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች እንደ ወራጅ ወንዝ በሚቀዱለት የአሉባልታ ቦይ አይደለም።

ርግጥ የእነርሱ ተግባርና ዓላማ ከወጣቱ ፍላጎት ጋር የሚገናኝ ነው ማለት አይቻልም። ወጣቱ ተስፋ ያለውና የዚህች ሀገር የነገ ተስፋ ነው። ህገ ወጦች፣ ፀረ ሰላም ሃይሎችና አሸባሪዎች ግን ሰንደቅ ዓላማውን በማጣጣል የወጣቱን ተስፋ ለማጨለም የተሰለፉ ናቸው። እናም ወጣቱ የእነዚህን ሃይሎች አሮጌ ሴራ መንቃት መቻል አለበት። ታዲያ ለወጣቱ ሰንደቅ ዓላማውን ለማስረዳት አትሌቶቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲወዳደሩ የሚኖረንን ስሜት ማውሳት ብቻ በቂ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው አትሌቶቻችን በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሁም እግር ኳስ ተጫዋቾቻችን ሰንደቅ ዓላማችንን ይዘው ሲሰለፉና የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ፣ እንደገናም ውድድር ገብተው ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ሲጋጠሙ፣ እኛም በቴሌቪዥን መስኮትም አሊያም በአካል ስንከታተል ‘ወይኔ ተቀደምን!’ አሊያም ‘ብራቮ አሸነፍን!’ እያልን እንቅልፍ አጥተን የምንጠበበው፣ የምንጨነቀውና የምንጮኸው እንዲሁም እልህና ሲቃ የሚተናነቀን ብሎም በዓለም ፊት ሁሌም አሸናፊ ሆነን መታየትን የምንመርጠው ለሰንደቅ ዓላማችን ካለን ፍቅር በመነጨ መሆኑ ማንም ሊክደው አይችልም። አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ ሲያውለበልቡ አሊያም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አፍሪካን ወክላ ‘ባንዴራዋ’ ሲውለበለብ የሚሰማን ኩራትም ለሰንደቅ ዓላማችን ካለን ፍቅር የመነጨ ነው።

በመሆኑም ይህን ኩራትና ፍቅር እየፈለግን ሰንደቅ ዓላማውን ልናሳንሰው አይገባም። እናም እዚህ ላይ በተለያዩ ሀገራዊና ክልላዊ እንዲሁም ሀዝባዊ በዓላት ላይ የሌላ ወገንን ባንዴራ ይዞ መውጣት አሊያም ሰንደቅ ዓላማውን ኣሳንሶ መመልከት የህግም ቢሆን ተጠያቂነት ያለው መሆኑንም መገንዘብ ይገባል። በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ ሶስት ላይ ሰንደቅ ዓላማውን አስመልክቶ በግልፅ እንደተደነገገው፤ ሶስት ጉዳዩች በሚገባ ሰፍረዋል። አንደኛው፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ እንደሚኖረውና ሶስቱም ቀለሞች እኩል ሆነው በአግድም እንደሚቀመጡ ይገልፃል። ሁለተኛው፤ ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ የሚያስረዳ ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው እንደሚችል የሚገልፅ ነው።

ይህ ድንጋጌ የፀደቀው በመላው የሀገራችን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሀዝቦች ነው። እናም ከዚህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ውጭ ያለን ባንዴራ ይዞ መውጣት አይቻልም። የህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት በግልፅ መቃወም ስለሆነ ህገ ወጥነትም ነው። በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየሙትን ቡድኖች ባንዴራ በማንኛውም መንግስታዊም ይሁን ህዝባዊ በዓላት ላይ ማውለብለብ ህግ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በገሃድ መፃረር ስለሆነ ክልክል ነው። በትርጓሜ ደረጃም ሰንደቅ ዓላማው መሃል ላይ በሰማያዊ መደብ የተቀመጠውን ኮከብና ጨረሮችን ያልያዘ ባንዴራንም መያዝ ህገ ወጥነት ነው። ምክንያቱም ህገ መንግስቱ ላይ እንደሰፈረው ሰንደቅ ዓላማው መሃል ላይ ያለው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ስለሆነ ነው። ብሔራዊው ዓርማ የሌለበትን ልሙጥ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዴራን ይዞ መውጣት በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት እንዳይኖሩ መፈለግ ነው። ይህን የሚፈልጉት ደግሞ የሀገራችን ህዝቦች ጠላቶች የሆኑ ሃይሎች እንጂ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚኖር ሰላማዊ ዜጋ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም የህዝቦችን እኩልነትና አንድነት የማይመኝ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለ ህዝብ በተግባሩ መልሶ ራሱን ሊፃረር ስለማይችል ነው።

በአጠቃላይ የአሸባሪዎችንና የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎችን ባንዴራ ይዞ በአደባባይ መውጣት ክልክል ብቻ ሳይሆን ራስንም መፃረር ጭምር ነው። እናም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ሁሉም ዜጋ ሊኮንነው ይገባል። የድርጊቱን ተሳታፊዎች በአደባባም ሊያወግዛቸው ግድ ይላል። ሰንደቅ ዓላማችንን ማክበርና ማስከበር የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑ ሁሌም ሊዘነጋ አይገባም።