ethiopian news

Artcles

ሰንደቅ ዓላማውን ማክበር ሕዝቦችን ማክበር ነው

By Admin

October 10, 2017

ሰንደቅ ዓላማውን ማክበር ሕዝቦችን ማክበር ነው

ኢብሳ ነመራ

ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም 10ኛው የኢፌዴሪ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ይከበራል። እርግጥ ነው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ዘውዳዊና የወታደራዊ ቡድን የመንግስት ሥርአቶችም ሰንደቅ ዓላማ ነበራት። ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ይሁን እንጂ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመከባበርና በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያላት ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊት ሃገር በፍቃዳቸው መስርተው የሚኖሩበት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከቀደሙት ሥርአቶች የተለየ ትርጉም አለው።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዘውዳዊው፣ በወታደራዊውና አሁን በኢፌዴሪ የመንግስት ሥርአቶች አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ህብረ ቀለማት ያሉት መሆኑ ያመሳስላቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከ1967 እስከ 1980 ዓ/ም  ለአስራ ሶስት ዓመታት በቆየው የጊዜያዊ ወታደራዊ ደርግ አስራሶስት የሽግግር አመታት፣ እንዲሁም ከ1983 ማገባደጃ እስከ 1987 ዓ/ም ለሶስት ዓመታት በቆየው የሽግግር መንግስት ወቅት ካልሆነ በስተቀር አርማ አጥቶ አያውቅም። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ሌጣውን የተውለበለበው በእነዚህ የሽሽግር መንግስታት ወቅት ብቻ ነበር። ከዚህ ውጭ በሶስቱም ሥርአቶች መሃከሉ ላይ አርማ ነበረው።

በዘወዳዊ ሥርአት ሰንደቅ ዓላማው ነገሥታቱ የዘር ሃረጋችን ይመዘዝበታል የሚሉት የይሁዳዊነት መለያ አንበሳና አንበሳው የያዘው ዘንግ ላይ ዘውዳዊው ሥርአት ክርስቲያናዊ መሆኑን የሚያንጸባረቅ መስቀል ያለበት አርማ ነበረው። ይህ ሰንደቅ ዓላማ፣ በሰንደቅ ዓላማው ስር እንዲተዳደሩ የተደረጉትን የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ወይም በመሃከላቸው ያለውን ወይም ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት አያንጸባርቅም። በሃገሪቱ ያሉ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችንም አይወክልም። በመሆኑም ሰንደቃላው የኢትዮጵያውያን አልነበረም።

ከአስራ ሶስት ዓመታት የሽግግር እድሜ በኋላ ወታደራዊው ደርግ የመሰረተው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢህዴሪ) መንግስት ሰንደቅ ዓላማም አርማ ነበረው። ይህ አርማ የስንዴ ዘለላና የማሽን ጥርስ ኖሮት ልማትን ቢያንጸባርቅም በሰማያዊ ቀለም ሰላምን ለመወከል ቢሞክርም አናቱ ላይ የአክሱምን ሃውልት ያስቀምጣል። ይህ  አርማው በዋናነት የሦስት ሺህ ዘመን የኢትዮጵያ የመንግስት ታሪክ ቀጣይ መሆኑን ማመልከት ላይ ያተኮረ መሆኑን ያሳያል። ይህን የሦስት ሺህ ዘመን የመንግስት ታሪክ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አይጋሩትም። እናም አርማው የሃገሪቱን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነትና በመሃከላቸው ያለውን ወይም ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት የሚያንጸባርቅ አልነበረም።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዘውዳዊውና ከወታደራዊው አሃዳዊ ሥርአት ነጻ ለመውጣት የትጥቅ ትግልን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ታግለዋል። በዚህ የነጻነት ትግል ሞተዋል፣ ተግረፈዋል፣ አካላቸው ጎደሏል፣ ተሰደዋል፣ ተዋርደዋል። በዚህ ምክንያት የአሃዳዊ ሥርአቶቹ ሰንደቃላማ ነጻነታቸውን ሳይሆን ይደርስባቸው የነበረውን ጭቆናና ስቃይ ነው የሚያስታውሳቸው። የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ልዩ አርማ እንዲኖረው የተደረገው ይህን ጠባሳ በመሻር በመሃከላቸው ያለው አዲስ የመከባበርና የእኩልነት ግንኙነትና ነጻነታቸው በሰንደቃላማው ላይ እንዲጸባረቅ ለማድረግ ነው።

ወደኋላ ተመልሰን የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ይዘት የተወሰነበትን ሁኔታ እናስታውስ። ከወታደራዊው የደርግ መንግስት ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸውን ነጻ መንግስት ከመመሰረት ይልቅ አንድ የጋራ ሃገር መስርተው መኖር የሚችሉበትን እድል ለመሞከር ነበር የተስማሙት። ሰኔ 1983 ዓ/ም በተካሄደው በሃገሪቱ ሁሉም የተቃዋሚ ሃይሎች በተሳተፉበት ኮንፈረንስ ላይ። በዚህ ኮንፈረንስ፣ በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሰረት የህዝቦች አንድነት ያለው ሃገር ለመመስረት የሽግግር መንግስት አቋቋሙ።

የዚህ የሽግግር መንግስት ዋና ተግባር ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚመሰርቱት መንግስት ህገመንግስት ማዘጋጀት ነበር። በዚህ ህገመንግስት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ያላት ፌደራላዊት ሃገር ለመመስረት ተስማሙ።

በህገመንግስቱ ዝግጅት ወቅት ይህች የጋራ ፌደራላዊት ሃገር የምትወከልበት ሰንደቅዓላማ ጉዳይ አወዛጋቢና ብዙ ውይይት የተደረገበት ነበር። ባለፉት ሥርአቶች በጭቆና ስር የኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለጭቆና የዳረጓቸው አሃዳዊ ሥርአቶች ሲጠቀሙበት የነበረውን  ሰንደቅዓላማ የፌደራላዊው መንግስት ሰንደቅዓላማ ሆኖ እንዲያገለግል ፍላጎት አልነበራቸውም። ከቀደመው የተለየ ሰንደቃላማ እንዲኖር የሚል ሃሳብ ያቀረቡ ብዙዎች ነበሩ።

በሌላ በኩል ያለፉት አሃዳዊ ሥርአቶች ጨቋኞች የነበሩ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ እንዲሁም የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች በአንድ ግንባር ተሰልፈው መስዋዕትነት በመክፈል ሃገሪቱን ከቅኝ ገዢ አውሮፓውያን ወረራ ተከላክለው ነጻነቷን ጠብቀዋል። ሌሎችም በጎ የጋራ ጉዳዮች ውስጥ አልፈዋል። ይህን ያገራ በጎ ታሪካቸውን መነሻ በማድረግ የፌደራሉ መንግስት ሰንደቅ ዓላማ መሰረቱ ቀድሞ እንደነበረው አርንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ መሆኑ ላይ ተስማምተዋል። ይሁን እንጂ ሰንደቅ ዓላማው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖቶች የተጎናጸፉትን ነጻነት፣ እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በእኩልነት የህዝቦች አንድነት ያላት ሃገር መመስረታቸውን የሚያንጸባርቅ አርማ እንዲኖረው ተስማምተዋል።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 3 “የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ” በሚል ርዕስ ሥር፣

 

 

ይላል።

የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 በአንቀጽ 5 የሰንደቅ ዓላማ ምንነት በሚል ርዕስ ስር

 

 

ይላል።

እንግዲህ አሁን አንዳንድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ቡድኖች እንደሚያደርጉት በህገመንግስቱ የተቀረጸውን የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ የተለያየ መሰረተ ቢስ ቅጥያ እየሰጡ እንደማይቀበሉት ሲገልጹ ይሰማል። ልብ በሉ፤ ይህን የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ አለመቀበል በሃገሪቱ ብሄሮች፣ በሄረሰቦችና ህዝቦች ፍቃድ የተመሰረተውን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ አንድነት አለመቀበል ነው። ይህ ፌደራላዊ አንድነት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን በሃገሪቱ የነበሩት አሃዳዊ ሥርአቶች ውስጥ በነበረው ጭቆና የተፈጠረው ብሄራዊ ቅራኔና ቅራኔው በወለደው የነጻነት ትግል በታሪካዊ አስገዳጅነት የመጣ ነው። በመሆኑም ፌደራላዊ አንድነቱን አለመቀበል እንዲፈጠር ያደረገውን አስገዳጅ ታሪካዊ ሁኔታ መካድ ነው። በሌላ በኩል፣ በታሪካዊ አስገዳጅ ሁኔታ የተሻረው አሃዳዊ ሥርአት ዳግም ሊመለስ ስለማይችል፣ ፌደራላዊ አንድነቱን መቃወም ሃገሪቱ እንድትፈርስ ከመፈለግ የተለየ መድረሻ አይኖረውም።

የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠበት ፌደራላዊ ሥርአት የብሄር ቅራኔን በመፍታት በሃገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ አድርጓል። አልፎ አልፎ ከወሰን ይገባኛል፣ ከማንነትና ከአስተዳደር ጥያቄ ጋር በተገናኘ አለመግባበቶችና ግጭቶች ሲያጋጥሙ የቆዩ ቢሆንም፣ እነዚህ ሁኔታዎች ከፌደራላዊ ስርአቱ የመነጩ ሳይሆኑ የአፈጻጻም ችግር ውጤቶች ናቸው። የፌደራላዊው ሥርአት ህገመንግስት የዚህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍታት የሚያስችል ሥርአት አለው።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሃገሪቱ ሰላም ማረጋገጥ የተቻለው በዚሀ ምክንያት ነው። ይህ በፌደራላዊ ሥርአቱ የተረጋገጠ ሰላም፣ ህዝቡ ትኩረቱን ወደልማት እንዲመልስ ዕድል ሰጥቷል። ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ስጋት እንዳይኖርባቸው በማድረግ ሃብታቸውን ስራ ላይ እንዲያውሉ አድርጓል። የውጭ ባለለሃብቶች ወደሃገሪቱ እንዲገቡ የሚስብ ዋስትና ፈጥሯል። እነዚህ ፌደራላዊ ሥርአቱ ያረጋገጣቸው ሁኔታዎች ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ተከታታይ በአማካይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ አስችለዋል።

ይህ  ተከታታይ እድገት በህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ላይ ተጨባጭ መሻሻል አምጥቷል። እናም ፌደራላዊ ሥርአቱ የሃገሪቱ የሰላምና የልማት መሰረት ነው። የሰላምና የልማት መሰረት የሆነው ፌደራላዊ ስርዓት መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ማክበር የኢትዮጵያ ብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን የማክበር የመጀመሪያው እርምጃ ነው።