Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስርዓቱን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማጠልሸት አባዜ

0 369

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስርዓቱን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማጠልሸት አባዜ

                                                        ቶሎሳ ኡርጌሳ

የሀገራችንን ሰላም የማይመኙ ፅንፈኛ ኃይሎች የፌዴራል ስርዓቱን ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ የማጣጣል፣ ድክመትን ብቻ የማፈላለግ ስራ ላይ ተጠምደዋል። እነዚህ ኃይሎች የፌዴራል ስርዓቱ ለስኬቶቻችን ሁሉ መነሻ መሆኑን እያወቁ ሊናገሩት አይደፍሩም። ምክንያቱም ዓላማቸው ስርዓቱ ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ምንም ፋይዳ እንዳልፈፀመ በማስመሰል ስርዓቱን ማጠልሸት ስለሆነ ነው።

ፅንፈኞቹ በሀገራችን ውስጥ አንድ ቦታ ላይ የሆነ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ችግሩን በማጦዝ በመላው ሀገራችን ውስጥ የተከሰተ በማስመሰል ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የህዝቦችን ሰላም ለመንሳት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ማናቸውም ችግሮች በመሰረታዊነት የስርዓቱ ምንጮች እንዳሆኑ እያወቁ ስርዓቱን ጥላሸት ከመቀባት የታቀቡበት ቀን የለም።

ርግጥ ፅንፈኞቹ የፌዴራል ስርዓቱን ማጣጣል የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ስርዓቱ ገና እውን ሲሆን ጀምሮ ይህን ሴራቸውን ከአንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ጋር በመሆን ሲከውኑ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ፅንፈኞቹ የፌዴራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደ ማያባራ ጦርነት ውስጥ ትገባለች፤ ሀገሪቱም የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿም በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይጨራረሳሉ በማለት አሟርተው ነበር። የፖለቲካ ተንታኞች ብዙ ቀበጣጠሩ፤ ጽንፈኞች ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለሀገሪቱ አይበጅም ሲሉ ብዙ አራገቡ።

እነዚህ ፅንፈኞችና መገናኛ ብዙሃን በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አልነበረም—ይልቁንም የቀድሞው ስርዓት ናፋቂ ከሆኑት ፅንፈኛ ሃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ።

ያም ሆኖ ፅንፈኞቹና መገናኛ ብዙሃኑ ያሻቸውን ቢሉም መንግሥትና ህዝቡ በውዠንብራቸው ሳይዘናጉ ብዝሃነታቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው ለጋራ ዕድገት መረባረቡን በመምረጣቸው ዛሬ ለበቁበት ሁለንተናዊ ዕድገት ደርሰዋል።

ርግጥ አንዳንድ ፅንፈኞች በብሔር ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ሲገልፁ ይስተዋላል። እውነታው ግን ምልከታ የተለየ ነው። ምክንያቱም በህዝቦች እምነት የቆመው ስርዓት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን በመስጠታቸው ነው።

ይህም እንኳንስ ፌዴራላዊ ስርዓቱ አያስኬድም ሊያስብል ቀርቶ፤ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ምርጥ ትምህርት ሰጪ ሆኗል። በስርዓቱ የፖለቲካል- ኢኮኖሚ አውድ ውስጥ የህዝቦች ሚና ወሳኝ በመሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያ በልማት ብቻ ሳይሆን፤ በሰላምና በዴሞክራሲ ግንባታ ተጠቃሽ መሆን ችላለች።

ይህ የሆነውም የሀገሪቱ ህዝቦች ስርዓቱን በእምነትና በፍላጎት ስለሚመሩት ነው። ስለሆነም ፅንፈኞች ስርዓቱን አስመልክተው አንዴ ‘እንዲህ ይሆናል’ ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘እንዲህ መሆኑ አይቀርም’ እያሉ የሚነዙት ሟርት ቦታ ሊኖረው አይችልም። በምንም ዓይነት ሁኔታም ቅቡል አይሆንም። ምክንያቱም የስርዓቱ ተጨባጭ ሁኔታና የእነርሱ ሟርት “አራምባና ቆቦ” የሚሉት ዓይነት ስለሆነ ነው።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው እነርሱው በፍላጎታቸው እውን ባደረጉት ህገ መንግስት ላይ ተደንግጓል። እንዲሁም የኃይማኖትና መንግስት መለያየትም በመርህ ደረጃ ተቀምጦ መንግስት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታ ተጥሎበታል።

ሰው ሁሉ በህግ ፊት እኩል በመሆኑ የትኛውም ማንነት ከሌላው የማይበልጥና የማያንስ መሆኑም ተረጋግጧል። እነዚህ ሁሉ እውነታዎች በሀገራችን ህዝቦች ፍላጎትና እምነት ላይ ተመስርተው እውን በመሆን ላይ የሚገኙ ናቸው። ያለ እነርሱ ፈቃድ ማንም ሊቀንሳቸው አሊያም ሊሽራቸው አይችልም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ብሔር በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለፅ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው። ሁሉም ብሔር ራሱን በራስ የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዲረጋገጥለት ተደርጓል። ይህም ህዝቦች በስዓቱ የሚደምቁበት አውድ እንጂ ለመለያየታችን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል የሚያስረዳ ነው። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶች ስርዓቱ የህዝቦች ፍላጎት መድመቂያ ጌጣቸው መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፌዴራላዊ ስርዓቱ የማዕዘን ድንጋይ ብቻ አይደሉም። ሀገራችን የተያያዘቻቸውን የልማት ዕቅዶች በአጥጋቢ ሁኔታ እየፈፀሙ የመጡ የሀገሪቱ ኃይልና ጉልበት ጭምርም ናቸው። እናም የትኛውም ፅንፈኛ ኃይል ያሻውን ቢያወራም በጋራ የማደግ አንድነት ኃይል እየታገዝን የህዳሴ ጉዟችንን እውን ማድረጋችን የሚቀር አይመስለኝም።

ይህ ማለት ግን ፌዴራላዊ ስርዓቱ በአፈፃፀም ረገድ አልጋ በአልጋ ዕውን እየሆነ ነው ማለት አይደለም። ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶች እንዲሁም በስርዓቱ ውስጥ የሚፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በአፈፃፀም ሂደቱ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ አሻራ ማሳረፋቸው አይቀርም።

ይሁንና እኛ ሀገር ውስጥ እየተገነባ ያለው ሥርዓት ራሱን በራሱ እያረመና እያስተካከለ የሚሄድ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ማንኛውም ፌዴራላዊ ሥርዓት በአንድ ጀምበር የሚገነባ እንዳልሆነ ሁሉ፤ እዚህ ሀገር ውስጥም የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው ነባራዊ ሃቅ ነው። እናም በሥርዓት አገነባቡ ሂደት ውስጥ ስንክሳሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ዋናው ነገር እነዚህ ጊዜያዊ ስንክሳሮች በብቃት እየተፈቱ የመሄዳቸው ጉዳይ ነው።

ከዚህ አኳያ በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ የደረሰ ነው። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ ነባሪያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው የሚኖሩበትን አስተማማኝ ሥርዓት መፍጠር ላይ ናቸው።

ፅንፈኞቹ የፈለጉትን ቢሉም የእኛ ሀገር ፌዴራላዊ ስርዓት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አይደለም። ጠንካራና ህዝባዊ መሰረት ያለው ነው። በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መፈቃቀድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሁም የህዝቦች አንድነት የሚገለፅበት ስርዓት ነው። እናም በእነርሱ አሉባልታ ሊፈርስ የሚችል አይደለም።

ርግጥ በማንኛውም ሀገር ከችግሮችና ከተግዳሮቶች ነፃ ሊሆን አይችልም። ምንም እንኳን ስርዓቱ እነዚህን ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ ሀገራችንንና ህዝቦቿን ዛሬ ላይ ላሉበት አስተማማኝ የሰላም ቁመና ቢያበቃትም፤ አሁንም ቢሆን ከችግሮችና ከተግዳሮቶች የነፃ ነው ማለት አይደለም።

በአንድ በኩል ስርዓቱን የሚመሩት ሰዎች በመሆናቸው ከአቅም ውስንነትና ከሌሎች ነባራዊ ጉዳዩች ጋር ተያይዞ ከችግሮችና ከተግዳሮቶች ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። በሌላ በኩልም ችግሮችና ተግዳሮቶች ነባራዊ ክስተቶች ናቸው።

እናም ዋናው ነገር ችግሮቹና ተግዳሮቶቹ መሰረታዊና አላላውስ የሚሉ እንዳይሆኑ የማድረግ ጉዳይ ነው።  ታዲያ ከዚህ አኳያ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በመፍታት ራሱን በራሱ የማረም አቅምና ብቃት ያለው በመሆኑ ይህንኑ እውን ሲያደርግ ዛሬ ላይ ደርሷል።

ሀገራችን ውስጥ እየተተገበረ ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከዚህ ቀደም ያጋጠሙትን ውጣ ውረዶችን እየፈታና ችግሮችን እያረመ የመጣ በመሆኑ እነዚህ ተግዳሮቶች እየፈታ ነው።

ዛሬ ስርዓቱን ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ቢሆንም፤ የችግሮቹ አራማጅ ኃይሎች የዘመናት ጥያቄያቸውን በህገ መንግስቱ ያረጋገጡት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለመሆናቸው፤ ከመንግስት ጋር ሆነው በስርዓቱ አማካኝነት ተግዳሮቶቹን እየፈቱ ቀጥለዋል። ነገም ተጠናክረው ይቀጥላሉ። ይህም የፅንፈኞችን አፍ የሚያሲዝ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy