Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በተሃድሶው ችግሮች እየተፈቱ ነው!

0 373

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በተሃድሶው ችግሮች እየተፈቱ ነው!

                                                           ታዬ ከበደ

ጥልቅ ተሃድሶው ከተጀመረበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለችግሮች በመንግስት የተሰጡ ምላሾችን በርካታ ናቸው። መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው የወሰዳቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ችግሮችን በሂደት እየፈቱ ነው። ይህም እንደ አገር እየሰራን መታደሳችንን ከቀጠልን ወደፊትም የላቀ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል የሚያመላክት ነው።

በጥልቅ ተሃድሶው የአገራችን ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ እየተካሄዱ ባሉት የውይይትና የግምገማ መድረኮች የመንግስትን ባለስልጣኖች ከሃላፊነታቸው አንስቷል። ከዚህ አኳያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ህዝቡ በግምገማው ያካሄደውን ሹም ሽር መካሄዱ ዋቢ ነው። ይህም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመታደስ ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት እያመጣ እንጂ፣ አንዳንድ ፅንፈኞች እንደሚሉት ውጤት አልባ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ጥልቅ ተሃድሶው ዋጋ ያለውና የአገሪቱን ችግሮች በመግባባት እየፈታ ነው።

እርግጥ በየትኛውም ዴክራሲያዊ ሀገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። ምንም እንኳን በሀገራችንም መንግሥትና ህዝብ በመገንባት ላይ የሚገኙት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ለጋ ቢሆንም፤ እንደ ጀማሪ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ከዚህ ነባራዊ ክስተት የፀዳንና ጉድለቶች የሉብንም ብሎ ለመናገር አይቻልም።

ለነገሩ የኢፌዴሪ መንግስትና እርሱን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር በመሆን በየጊዜው በሚወስዷቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች በመጠኑም ቢሆን እየቀረፉ ቢሆኑም፤ የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ተገኝቷል ማለት አይቻልም። እንዲያውም አስተሳሰቦቹ እየገነገኑ ጫፍ ላይ እየወጡ ይመስላሉ። በአመዛኙ ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የሚፀየፍና እንደ ነውር የሚያይ የመንግስት ስራ አስፈፃሚን ብሎም ህዝብን በተሟላ ሁኔታ መፍጠር አልተቻለም። በሰጪም ይሁን በተቀባይ መካከል ያለው አስተሳሰብ አንድና ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሆነውም ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት አስተሳሰቦች ብሎም ልማቱ የፈጠራቸው አንዳንድ ሁኔታዎች አስተዋፅኦ ያደረጉ ይመስለኛል።

ሲቪል ሰርቪሱ ምንም እንኳን በሀገራችን ውስጥ ለተገኘው ልማት የበኩሉን ድርሻ ቢያበረክትም ከዚህ ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ ውጪ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ስልጣን የህዝብ ማገልገያ ሳይሆን የራስ መገልገያ ሊሆን ችሏል።

ይህን አመለካከት ለመለወጥ ደግሞ በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የአስፈፃሚነት ስራን የሚከውኑት የሲቪል ሰርቪሱ አካላት በአመለካከት ብሎም በአደረጃጀት ለውጦች ውስጥ ማለፍ የግድ ይላቸዋል። የእነርሱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ በማለፋቸውም የተጠያቂነት መንፈስ ተፈጥሯል፤ እየተፈጠረም ነው። በዚህም ውጤቶች ተገኝተዋል።

በተሃድሶው ውጤትም መላው የሀገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በበጎ ገፅታ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ያደረጋት ይመስለኛል። የምትከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የሰላም ጠባቂ፣ መጠጊያና መጠለያ ሆናለች።

መንግስት በጥልቅ የመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የትኛውንም ወገን የሚለይ አይደለም።

መንግስት ከህዝቡ ጋር የተጀመራቸው የትግበራ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል። የዚህ ውጤትም በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል። በዚህም የህግ የበላይነትንና የተጠያቂነት መንፈስን ማስረፅ ተችሏል።

እስቲ እዚህ ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሁኔታን በመስሌነት እናንሳ። አስተዳደሩ ባለፉት 10 ዓመታት የተጓዘበት መንገድና ያመጣቸው ለውጦች የጥልቅ ተሃድሶው መነሻ መሆናቸውን በማስታወቅ፣ በእነዚህ ዓመታት በከተማዋ በተከናወኑት ስራዎች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች በመጡት ለውጦች በየደረጃው መብቱን የሚጠይቅና ጥቅሙን የሚያስከብር ህብረተሰብ መፍጠር እንደተቻለ ተገልጿል። በጥልቅ ተሃድሶውም ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ከህዝቡ ጋር በመሆን ርምጃዎች ተወስደዋል። እነዚህ ርምጃዎች በከተማዋ የተፈጠሩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዙ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮች ለህዝቡ ሁሉን አቀፍ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ወቅታዊና ተገቢ ምላሽ ባለመሰጠቱ የተከሰቱ በመሆናቸው፤ እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ርብርብ እያደረገ ነው። ያም ሆኖ ህብረተሰቡ አሁንም በበቂ ሁኔታ በመሳተፍ በከተማዋ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት የመፍትሔው አካል መሆን ይጠበቅበታል። በጥልቅ ተሃድሶው እርምጃ መልሶ ተጠቃሚው እርሱ ስለሆነ ነው።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት፣ ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ለህዝብ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ህዝቡም በማንኛውም ተወካዩ ላይ አመኔታ ሲያጣ በማንኛውም ወቅት ከቦታው የማንሳት መብት እንዳለው ያስቀምጣል። መነሻው የህዝብ የስልጣን ሉዓላዊነት መከበር ነው።

ህዝቡ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ሿሚና ሻሪ የሚሆነው እርሱ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ስልጣን የሚመነጨው ከህዝብ እንጂ ከማንም አይደለም። ተሿሚው በህዝብ በጎ ፈቃድ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥና የሚነሳ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ተሿሚው በራሱ ፈቃድ አይደለም ስልጣን ላይ የተቀመጠው።

ጥሩ ሲሰራ ጥንካሬውን እንዲያጎለብት፣ ሲደክምም ድክመቱን የሚያሳየውና ከዚያ በላይም በገሃድ በምዝበራ ውስጥ ገብቶ ሲገኝ ካለበት ቦታ የሚያነሳው ህዝብ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ ፈላጭና ቆራጩ ህዝብ እንጂ ባለስልጣን አይደለም። ሊሆንም አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ህዝቦች በከፈሉት መስዋዕትነት ባለፉት ስርዓቶች እንዲቀር ያደረጉት ነው።

እነዚህ ዕውነታዎችም የህዝቡን አመኔታ በመሸርሸር ለሁከትና ለብጥብጥ መዳረጋቸው የሚቀር አይመስለኝም። በሁከትና በብጥብጥ ውስጥ የሚኖር ህዝብ ደግሞ ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ሊያደርግ አይችልም። ከዚህ አኳያ በ2008 ዓ.ም የታየው ችግር ተጠቃሽ ነው።

እንዲህ ዓይነት ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ተሃድሶው በሂደት እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል። በየጊዜው የሚስተዋሉ ችግሮችን እየተከታተሉ ተገቢ ምላሽ መስጠትና ለዚህ የሚሆን መፍትሔ አደራጅቶ በማይቀለበስ መልኩ ለህዝብ ማሳወቅ የአንድ ጊዜ ስራ አይደለም። ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው ሊሆን ይገባል። በአሁኑ ወቅት የጥልቅ ተሃድሶው ስራ ችግሮችን እየፈታ ነው። ሂደቱን አጠናክሮ መቀጠል ችግሩን የበለጠ ለመፍታት ያስችላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy