Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዓሉ ለገጽታ ግንባታና ለኢንቨስትመንት ጉልህ ድርሻ አለው!

0 302

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዓሉ ለገጽታ ግንባታና ለኢንቨስትመንት ጉልህ ድርሻ አለው!

                                                     ደስታ ኃይሉ

በመጪው ህዳር 29 በአፋር ክልል መዲና ሰመራ ላይ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ይከበራል። ታዲያ ዕለቱን አስመልክቶ ክልሎች ውስጥ የሚከናወኑት ግንባታዎች አንዳንዶች እንደሚሉት ከቀኑ ፍጆታ የዘለለ ፋይዳ ያለው ነው። በአሁኑ ወቅት የክልሎች አቅም ተቀራራቢ እየሆነ መጥቷል። በዚህ ላይ በበዓሉ የሚከናወኑት ግንባታዎች ከዕለቱ ፍጆታ ባሻገር ለገጽታ ግንባታ ድርሻ ከፍተኛ ነው።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት በጫንቃቸው ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን ዘውዳዊ የጭቆናና የአፈና ሥርዓት በቃን ብለው በየካቲት 1966 ሕዝባዊ ዓመጽ ለማስወገድ ታግለዋል። ግና  ከአፄው አስከፊ ሥርዓት በከፋ ሃገሪቷን ለጦርነትና ለድህነት የዳረገው የደርግ አገዛዝ በጠመንጃ አፈሙዝ በትረ ስልጣኑን ለመያዝ ችሏል፡፡

 

ምንም እንኳን ደርግ በትረ ስልጣኑን ሲይዝ ስልጣን ለሰፊው ሕዝብ የማስረከብ የይስሙላ ቃል ቢገባም ቃሉን ገቢራዊ አለማድረጉን ስልጣን በያዘ ማግሥት በሚፈፅማቸው አምባገነናዊ ድርጊቶቹ አረጋገጠ፡፡

 

በተለይም የሕዝቦችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚደፈጥጥ አዋጆችን በማውጣት የስራ ማቆም አድማ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመናገርና የመፃፍ መብቶች አገደ፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩም ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚታገሉ ዜጐችን በግፍ መጨፍጨፉን በይፋ ተያያዘው፡፡

 

ይህ አስከፊ በደልና ጭቆና ያንገሸገሻቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአነስተኛ የሰው ኃይልና ትጥቅ ትግል በጀመሩ ቁርጠኛ የሕዝብ ልጆች ግንባር ቀደም መሪነትና መስዋዕትነት ጨፍጫፊውን ሥርዓት አምረው መታገል ጀመሩ፡፡

 

እንኳንስ በተደራጀ ፖለቲካዊ አመራር ይቅርና የኢትዮጵያ ብሔር በሔረሰቦች በጭሰኝነትና ፊውዳላዊ በሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት የበላይነት በተረጋገጠበትና ከፍተኛ ጭቆናና ምዝበራ በሚደርስባቸው ወቅት እንኳን ግፉንና ጭቆናውን አሜን ብለው ሳይቀበሉ ባልተደራጀ ሁኔታ  ለአፍታም ቢሆን ትግል አቋርጠው አያውቁም፡፡

 

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የፊውዳሉን ስርዓት ለመገርሰስ በተገኘው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተደረጉ የገበሬዎች አመፅ እንደታገሉ ሁሉ በወታደራዊው አምባገነን ስርዓት ወቅትም ስርዓቱን ለመጣል በበርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈው በተለያዩ አቅጣጫዎች መራራ ትግላቸውን አካሂደው የጭቆናና የአፈና አገዛዝ እንዲያበቃ አድርገዋል፡፡

በእኩልነትና በአንድነት መንፈስ በጋራ የሚኖሩት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አሁን ለደረሱበት የእኩልነት፣ የዴሞክራሲና የልማት ዘመን  እጅግ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል፡፡

ወደር የለሽ መስዋዕትነት የጠየቀ የትጥቅ ትግል አድረገውም አስከፊውን ስርዓት ከጫንቃቸው በመራራና እልህ አስጨራሽ ትግላቸው በመጣልና ታላቁን ሀገራዊ ድል በማብሰር ዛሬ ለተገኘው የፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች አብቅተውናል፡፡

እንደሚታወቀው ባለፉት ሥርዓቶች መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተነፍገው  ከነበሩ መብቶቻቸው መካከል የራስን ዕድል በራስ  መወሰን አንዱ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና በሌሎች ዓለም አቀፍ ዶክመንቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕውቅና እግኝቶ የነበረ ቢሆንም ያለፉት የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ይህንን መብት አፍነውት ኖረዋል፡፡

በመሆኑም በተለይም ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ሆነው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት  የመሳተፍ  መብት አልነበራቸውም፡፡

በአካባቢያቸው አስተዳደር ውስጥ በአመራር ላይ የሚቀመጡ አስተዳደሮችና ዳኞች በማዕከላዊ መንግስት የሚሾሙ ነበሩ፡፡ የመንግስት ሠራተኞችን ሁኔታ ብንመለከት እንኳ ሙሉ በሙሉ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ነበሩ፡፡

የአካባቢው ተወላጆች እንኳንስ መሾም ይቅርና በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ የመካተት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ግመል በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያህል አስቸጋሪ ነበር፡፡ በመሆኑም እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት  ተነፍጓቸው በሌሎች እየተተዳደሩ፤ ሀብታቸውም እተየመዘበረ ሊኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡  

የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለጽጉበት ዕድል ተነፍጓቸውም ኖረዋል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ፤ ገሚሶቹ “ብረት ሰባሪ…ወዘተ” እየተባሉ የሚጠሩ ነበሩ፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር  ወዘተ. መብት አልነበራቸውም።

አብዛኛው ቋንቋዎችን እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና  በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም እጅግ  የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡ ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበር እንዲሁም የማስፋፋት መብታቸው  የተነፈገ እንደነበርም የኋላ ታሪካችን ያስረዳል፡፡

ያለፉት ሥርዓቶች  መለያ ባህሪይ  ተደርጎ  ሊወሰድ  የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር ነው፡፡ የአካል ደህንነት፣ በህይወት  የመኖር  መብት፣ ክብርን ከሚያዋርዱ አያያዞች የመጠበቅ ወዘተ. የሚጣስባቸው ነበሩ፡፡

ከዚህም አለፎ ኢ- ሰብዓዊ ለሆነ እስር መዳረግ፣ እገታ ወዘተ. ወንጀሎች  የሚፈጸምባቸው  በመሆኑ ዜጎች ለከፋ  ስቃይና ስደት ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  እኩል ሆነው የሚታዩበት  ሁኔታዎች ያልነበረባቸው መሆናቸውን የኋላ ታሪካችን ያመለክታል፡፡

ከላይ ለማሳያነት ከተገለጹት ጉዳዩች ባሻገር በሌሎች መብቶች  ላይም ከፍተኛ  አፈና ሲካሄድላቸው የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ  ሁኔታዎች  ግን የደርግ  ሥርዓት በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ዳግም ላይመለስ ሥርዓተ- ቀብሩ በተፈጸመ ማግስት ሊወገዱና የመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ሊከበሩ በቅተዋል፡፡ የአፋር ክልል ደግሞ የዚህ ትሩፋት ተቋዳሽ ነው፡፡

ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተወያይተው ህዳር 29 ቀን  1987 ዓ.ም ያጸደቁት ህገ – መንግሥት  የራስን ዕድል በራስ  የመወሰን፣ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ  ውክልና  የማግኘት፣ በቋንቋ የመጠቀምና  የማሳደግ ፣ባህልን የመግለጽ፣ ማዳበርና ማስፋፋት እንዲሁም ታሪክን የመጠበቅ እና ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ አረጋግጧል፡፡

ከላይ በውስን ደረጃም ቢሆን ባለፉት ሥርዓቶች  የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጨፈለቁ የነበሩባቸው መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡ ይህን ሁኔታ ግን መላው ህዝቦች በመስዋእትነታቸው እውን ባደረጉት የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት ለዘመናት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለማግኘት የበቁበት ድልን ተጎናጽፈዋል፡፡ በክልሎች ደረጃም ልማት እየተመጣጠነ ነው፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር ከዕለቱ ባሻገር ለአዘጋጁ ክልል ገፅታን ይገነባል፡፡ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተመልሰው ክልሉ እንዲያድግ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy