Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በግጭት ውስጥ ሁሌም ተጎጂው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው!

0 405

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በግጭት ውስጥ ሁሌም ተጎጂው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው!

                                                        ታዬ ከበደ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ አንዱን ለይቶ “የእገሌ ብሔር እንዲህ ሆነ” ማለት ትርጉም የለውም። ችግሩን ይበልጥ ከማወሳሰብ በስተቀር ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም።

አገራችን ውስጥ በሚከሰት ማንኛውም ግጭት ተጎጂው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው ብሎ አስፍቶ መመልከት ይገባል። እናም የምናከናውናቸው ማናቸውም ተግባሮች ከዚህ አስተሳሰብ አኳያ መቃኘት የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ከሁለቱ ተጎራባች ህዝቦች ድንበር ወዲህና ወዲያ ማዶ የሚገኙትና በሁለንተናዊ ዘርፎች ተቀራርበው ለበርካታ ዓመታት አብረው የኖሩት ህዝቦች ምንም ዓይነት የመጋጨት ፍላጎት እንደሌላቸው ለመንግስት ደጋግመው መናገራቸውን አቶ ኃይለማርያም ለምክር ቤቱ መግለፃቸው፤ በእኔ እምነት መነሻውና መድረሻው ሁለት ጉዳዮችን የያዘ ይመስለኛል።

አንደኛው ላለፉት 26 ዓመታት ገደማ ሀገራችን እየገነባች የመጣችው ፌዴራላዊ ስርዓት ለግጭት የሚሆን ቦታ የሌለው መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለዘመናት በአንድነት የኖረ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች አገራዊ ትውፊቶች የተሳሰረን ህዝብ የራሳቸው የጥበትም ይሁን የትምክህት አጀንዳ ያላቸው ታጣቂዎችና የታችኛው እርከን አመራሮች ሳቢያ በአንድ ጀንበር የሚፈጠር መለያየት ሊኖር ስለማይችል ነው።

ሁለቱን ወሰን ተጋሪ ህዝቦችን ጨምሮ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በደማቸው ዋጅተው እውን እንዲሆን ያደረጉት የኢፌዴሪ ሕገ መንግስትና እርሱን ተከትሎ እውን የሆነው የሀገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ለግጭት የሚሆን ቦታን የላቸውም። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ለግጭት የሚሆን ምህዳር የሌለ መሆኑ በሕገ መንግስቱ መግቢያ በተገቢው ሁኔታ ተብራርቷል።

የሕገ መንግስቱን መግቢያ በከፊል ስንመለከተው፤ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነጻ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤…ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤ መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤ ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤…” የሚል የህዝቦችን ፍላጎትን ይዞ እናገኛዋለን።

ይህም የአገራችን ህዝቦች የሚሹት ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ ማህበረ-ኢኮኖሚ እድገታቸውን እንዲፋጠን አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዲገነባ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ጥቅምና አመለካከት ያላቸው፣ ይህን ጥቅማቸውን እየተደጋገፉ በጋራ በማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው ያረጋግጣል።

ከዛሬ 23 ዓመት በፊት በሀገራችን ህዝቦች ሙሉ ፈቃድ እውን የሆነው ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እምነታቸውም ይሁን መፃዒ ዕድላቸው በሚመሰርቱት አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘውግ ያለው ሥርዓት ላይ እንጂ፤ ያለፉት ሥርዓቶች ጥለውት የሄዱትን የተበላሸ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰቦችን መልሶ መላልሶ በማመንዠግ ቁርሾ መያዝና ይህንንም ለግጭት ብሎም ለንፁሃን ህይወት መጥፊያነት በማለም አይደለም።

አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ህዝቦች ይሻሉ ሲባል፤ በራሳቸው እምነትና ፈቃድ እንዲፈጠር የፈለጉት ፌዴራላዊ ሥርዓት የተዛቡ ቀደምት ግንኙነታችንን ያስተካክልልናል፣ አንዳችን የሌላችንን ሃይማኖት፣ እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በማክበር በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘን እናድጋለን፣ የጋራ ተጠቃሚነታችንንም እናሳድጋለን ማለት ነው።

በዚህ የህዝቦች እምነት መሰረት፤ አንዱ ብሔር ከሌላኛው ጋር ተስማምቶና የጋራ ሃብቱን በጋራ ለማልማት እንዲሁም ጥቅሙን በፍትሐዊነትና እኩልነት ለማጣጣም ፍላጎት መኖሩን ያሳያል። ይህም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አንድ የጋራ ማህበረሰብን የመፍጠር ዓላማን ያነገበ እንጂ፤ ‘አንተ ከወዲያ ማዶ ነህ…እኔ ደግሞ ከወዲህ ማዶነኝ’ በሚል ህዝቦችን በቦታ የመከፋፈል መንፈስ ላይ የተመሰረተ አይደለም።

እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እንኳንስ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በምትከተለው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ፤ በገዛ ሀገራቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያ መብታቸው ተገፍፎ ‘ከዚህ ቦታ እንዳታልፉ’ ተብለው ከነጮች ጋር ምንም ዓይነት የጋራ መስተጋብር እንዳይኖራቸው በቦታ ተገድበው ይኖሩ በነበሩት የደቡብ አፍሪካ ዜጎች እንኳን ዛሬ ላይ የሚያስታውሱት አይመስለኝም።

እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከዘመነ-አፓርታይድ ጋር አብሮ ከስሟል። ሰዎችን በቦታ ከፍሎ ‘እዚህ ቦታ ላይ ድርሽ ትልና ውርድ ከራሴ በል’ የሚል አስተሳሰብ ዘመኑ ያለፈበት ኋላ ቀር ነው። ከፋፋይና የየትኛውንም ህዝብ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ ቦታ የለውም። የ‘ከዚህ ወዲህና ወዲያ’ አስተሳሰብ ቦታ ሊኖረው አይችልም። እዚህ ያለው እዚያ ሄዶ የመስራት፣ እዚያ ያለው እዚህ መጥቶ ካልሰራ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊያመጡት ያሰቡት አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ሊገነባ የሚችል አይመስለኝም።

በመሆኑም አንድ በምጣኔ ሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት በኢትዮጵያ ሶማሌ ውስጥ ያለው ዜጋ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውም የኢትዮጵያ ሶማሌ ሄዶ መስራት አለበት። ማንኛውም ዜጋ የመንቀሳቀስና በየትኛውም ክልል ሄዶ ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ያለው መሆኑ ሁሌም ታሳቢ መሆን አለበት።

የጋራ ወግ፣ ባህልና ትውፊት ያለው፣ በዘመናት አብሮነት ገመድ የተሳሰረ፣ በተለይም አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ገንብቶ የማየት ራዕይ ያለው የሁለቱም ክልል ህዝብ በጥቂቶች ፍላጎት እንዲህ በቀላሉ ሊለያይ የሚችል አይደለም። በፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውስጥ አገራዊ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታን ለማስረፅ ለ23 ዓመታት አብረው በመፈቃቀድ ኖረውና በአገራችን ለተገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ የራሳቸውን አሻራ በማኖር ላይ ያሉት ወንድምና እህት ህዝቦች በጥቂቶች ፍላጎትና ሴራ ሊፈቱ አይገባም። በመሆኑም የትኛውም ወገን በግጭት ወቅት ተጎጂው ኢትዮጵያዊ እንጂ ፅንፈኞች  ‘የእገሌ ጎሳ’ በማለት እንደሚያስወሩት አለመሆኑን በመገንዘብ ግጭትን ማራቅ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy