Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ሲባል…?

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ሲባል…?

                                                        ታዬ ከበደ

ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ በቅርቡ ይፋ ሆኗል። ስትራቴጂው ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ አቅርቢትን በማመቻቸት እንዲሁም ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ተገልጿል። የፋይናንስ አከታችነቱ እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ እንደሚዘልቅ ነው።

ይህም ከዚህ ቀደም በፋይናንስ አሰራር ውስጥ ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመድረስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ህብረተሰቡ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂውን በምን ዓይነት መንገድ መጠቀም እንዳለበት ግንዛቤ መስጠት ይገባል ብዬ አስባለሁ። እናም ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘኋቸውን የጉዳዩን አንኳር ነጥቦች ለመመልከት እሞክራለሁ።

እንደሚታወቀው ሁሉ ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ የዜጎችን ቁጠባ ከፍ የማድረግ፣ ፍላጎቱ በከፍተኛ ደረጃ እያየለ የመጣውን ብድር የማግኘት ዕድልን የሚያሰፋ፣ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን የሚያሳድግ፣ የስራ ዕድል የመፍጠር እንዲሁም የዜጎች ገቢን በማሳደግ የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

ይህ ሁኔታም የሀገራችን በተባበበረ ክንድ በድህነት ላይ የጀመረችውን ዘመቻ በማሳለጥ የድህነት መጠንን ትርጉም ባለው ደረጃ ሊቀንስ ይችላል። ሥራውም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ብሄራዊ የፋይናንስ አካታች ካውንስል በመሰየም መስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም ተጀምሯል።

ታዲያ በጅምሩ ወቅት ከግምት ውስጥ መምጣት ያለባቸው የዘመናዊነትና ቴክኖሎጂን በብቃት የመጠቀም ስራዎች መጠናከር ይኖርበታል። ስትራቴጂው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ቀደም ሲል የጠቀስኩት በመሆኑ ለተግባራዊቱ ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ እያንዳንዱን አርሶ አደር መድረስ የሚችልበት የዘመናዊነት አሰራር ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ ተጠቃሚዎች ብዛት በአገር ቤት ውስጥ እየጨመረ ቢሆንም፤ ይህን ወደ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በማዳረስ መጠኑን ይበልጥ ማስፋት ይገባል።

ለዚህ ትግበራም በአሁኑ ወቅት እውን የሆነው የብሄራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ጠቀሜታው የትየለሌ በመሆኑ ከወዲሁ የነበሩ እጥረቶችን በመፈተሽ ለተግባራዊነቱ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል።

ስትራቴጂው አቨስትመንትን የሚያሳልጥና የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያጎለብት መሆኑ በሀገር ውስጥ የምጣኔ ሃብት እድገት የሚያበረክተው አስተዋዕኦ ከፍተኛ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ባለፉት 10 ዓመታት ኢንቨስትመንትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በቁጠባም ረገድ አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል። በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ የሚገኘው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠይቀው የኢንቨስትመንት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል።

አንዱና ዋነኛው ፈታኝ ጉዳይ ታዲያ ለኢንቨስትመንቱ መሸፈኛ የሚያስፈልገው የአገር ውስጥ ፋይናንስ ግኝት እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የቁጠባ መጠን መሻሻል የሚታይበት ቢሆንም ያን ያህል አጥጋቢ ባለመሆኑ፤ ልማቱን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በከፊል ለማቅረብ እንዲቻል የአገር ውስጥ የቁጠባ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ ማደግ እንደሚኖርበት ይታመናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂው ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

እርግጥ ይህን የሀገር ውስጥ ቁጠባን የማሳደግ ግብ ለማሳካት በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥም የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ለማሳደግ የማስተማርና የማነሳሳት እንቅስቃሴዎች፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸውን ተቋማት የማስፋፋት፣ የወለድ ምጣኔን የማሻሻል፣ የግል ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎትን የመዘርጋት፣ የመንግስት የማህበራዊ ዋስትና ሽፋንን ይበልጥ እንዲጠናከር የማድረግ፣ የቤት የቁጠባ ፕሮግራም የማከናወን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቁጠባ ቦንድና ሌሎች በጅምር ላይ ያሉ የቁጠባ ዘዴዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት ወጪን በዋነኝነት የካፒታል ክምችት ለሚፈጥር የኢንቨስትመንት ወጪ በመመደብ በቁጠባ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል የተደረገው ጥረት የአገር ውስጥ ቁጠባ ከፍ እንዲል አግዟል፡፡ እነዚህ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት አስገኝተዋል፡፡ በዚህ ላይ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ የሚዘልቀው ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ሲታከልበት ቁጠባውን ምን ያህል ሊያሳድገው እንደሚችል ለመገንዘብ አይከብድም፡፡

የዜጎችን እና የንግድ ድርጅቶችን ቁጠባ ከፍ ለማድረግ እስካሁን የታየውን አበረታች እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ከዚህም አኳያ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋትና ወደ ዝቅተኛ አሃዝ መለወጥ፣ ህዝቡን ማስተማርና ማነሳሳት፣ የቁጠባ መሳሪያዎችና አገልግሎቶችን ማስፋፋትና ማጠናከር እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ዕድገቱን ማፋጠንና የሥራ ዕድልን ይበልጥ የማስፋፋት ጉዳዩች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ የብሄራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ለዘላቂና ፈጣን ዕድገቱ ምቹ የሆነ የማክሮ ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል ያለው ሚዛን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

በመሆኑም በተለይ በማኑፋክቸሪንግና በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎችና በሌሎች መስኮች የሚከናወኑ የግልና የመንግስት ኢንቨስትመንቶች ፈጣን ዕድገትን በማረጋገጥ ትልቅ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይም ከፍተኛ ግምት ላለው ኢንቨስትመንት መሸፈኛ የሚያስፈልገው ፋይናንስ በአብዛኛው ከአገር ውስጥ ለማሰባሰብ ካልተቻለ ደግሞ የፈጣን ዕድገቱ ዘላቂነት አደጋ ላይ መውደቁ የሚቀር አይመስለኝም፡፡

እናም በኢንቨስትመንትና በአገር ውስጥ ቁጠባ መካከል ያለውን ሚዛን ለማመጣጠን የአገር ውስጥ ቁጠባን በተጀመረው አቅጣጫ ማሳደግ የግድ ይላል፡፡ እናም የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂው በዚህ ረገድ ያሉትን ክፍተቶች መሙላት የሚችል ነው፡፡

በጥቅሉ በቁጠባና በኢንቨስትመንት መካከል ያለውን ሚዛን ለማጥበብ የሚከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም ክፍተቶቹን ሙሉ በሙሉ መድፈን ይቻላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለሆነም ጉድለቶቹን ለመሸፈንና የታቀደውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠል ስትራቴጂው ጉልህ ሚና ያለው ስለሆነ ሁሉም የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዩችን እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ የማዝለቅ ተግባር ከወዲሁ ስራውን በሚያሳለጥ መልኩ መከናወን እንዳለበት መግለፅ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy