Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተጠያቂነትን በማንገስ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል!

0 296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተጠያቂነትን በማንገስ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል!

                                 ዳዊት ምትኩ

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የተፈጠረውን ግጭት ለጠፋው የሰው ህይወት፣ ለወደመው ንብረትና ለተፈናቀሉ ዜጎቻችን ምክንያት የሆነኑ ጉዳዩችን በመለየት በየትኛውም አካል ላይ ተጠያቂ የመሆን አሰራርን ማንገስ ይገባል። ይህ የተጠያቂነት አሰራር በአሁኑ ወቅት እየተሰራበት ቢሆንም፤ ይበልጥ በማጠናከር የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተጠያቂነትወሳኝ ጉዳይ ነው። ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድንና ድርጅት በሚያከናውናቸው ስራዎች ተጠያቂ ካልሆነ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አይቻልም። ስለሆነም ለተጠያቂነት ቅድሚያ በመስጠት ህግ ለሁሉም ዜጎች እኩል መሆኑን ማሳየት ይገባል።

ዛሬ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ለውጥ ባለቤቶችና ለሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሚሆን ዕድገት በሁሉም መስኮች እያስመዘገቡ ነው። በዚህም የህዳሴያቸውን ጉዞ ቅርብ ለማድረግ ግስጋሴያቸውን ተያይዘውታል።

ሆኖም በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት ይበልጥ መስፈን ይኖርበታል። የመንግስት አሰራሮች ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መንፈስ እውን መሆን አለበት። ይህ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሀገሪቱ ህዝቦች መንገስት እንደያከናውነው የሚፈልጉት ጉዳይ ነው።

እናም መንግስት ሁሌም በአሰራሮቹ ላይ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝቦችን ህገ መንግስታዊ ፍላጎት እውን ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም በመሆኑ በየጊዜው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የየወራት ስራዎቹን ያቀርባል። ያስገመግማል። መጠንከርና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዩች ላይ የሚሰጡትን አስተያየቶችንም ይቀበላል።

የመንግስት የተጠያቂነት አሰራር የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው። በዴሞክራሲ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው። ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው።

እናም የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 26 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም።

እናም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል። የአሰራሩን ተጠያቂነትና ግልፅነት በዚያኑ ልክ ለህዝቡ ማረጋገጥ ይኖርበታል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው። በመሆኑም ማንኛውም አዋጅ ሲወጣ ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል እንጂ ለተለየ የህብረተሰብ ክፍል ተለይቶ አይደለም። እናም ፖለቲከኛውም፣ ሙዚቀኛውም፣ መሃንዲሱም፣ ሀኪሙም፣ ቀዳሹም ሆነ ተኳሹ…ሀገሪቱ ያወጣችውን ህግ የማክበርና በእርሱም የመመራት ግዴታ አለበት። በመሆኑም አንድ ግለሰብ ባለሙያ አሊያም የተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ ሙያውን ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባልነቱን እንደ መከላከያ ምሽግ በመጠቀም ህገ ወጥ ተግባርን መፈፀም የህግ የበላይነት ገቢራዊ እንዳይሆን የሚያግድ አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል።

እንደሚታወቀው በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል።

ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው። ይህም የህገ መንግስቱን አንቀፅ 56 የሚመለከት ነው። በዚህ አንቀፅ መሰረት በምክር ቤተ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተገልጿል።

ይህም የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ከህገ መንግስቱ አኳያ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ናቸው። ከእነርሱም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ውስጥ በአሸባሪነት የተሰየሙትን ኦነግንና ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ከደገፈ ወይም የእነርሱን ዓላማ ለማሳካት በተለያዩ መንገዶች ከተንቀሳቀሰ ከህግ የበላይነት ጋር እየተጋጨ መሆኑን ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ የሽብር ቡድኖች ህገ መንግስቱን ተፃርረው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው ነው። እናም እነርሱን አለመደገፍ የህግ የበላይነትን ማክበር ሲሆን፣ የእነርሱን ህገ ወጥ ዓላማ በማናቸውም መንገድ መደገፍ ደግሞ የህግ የበላይነትን መፃረር መሆኑን መረዳት ይገባል።

የህግ የበላይነት ልዕልና ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ።

የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል። ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ማናቸውም ግለሰብ ይሁን ቡድን የህግ የበላይነትን ተላልፎ ለፈፀመው ተግባር ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ይገባል።

ከዚህ አኳያ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የሰው ህይወትን ለቀጠፈውና ንብረት ላወደመው እንዲሁም ለመፈናቀል ምክንያት የሆነው ግጭት እንዴት፣ በማን ጠንሳሽነትና ለምን ዓላማ እንደተፈጠረ በመመርመር ተጠያቂነን በማንገስ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy