Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ችግሩ ሃገራዊ ነው

0 366

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ችግሩ ሃገራዊ ነው

ብ. ነጋሽ

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል ከድንበር መካለል ችግር ጋር በተያያዘ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በአካባቢው ግጭት መቀስቀስ ለሚፈልጉ አካላት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል። ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት በ1997 ዓ/ም በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች አወዛጋቢ በነበሩ ቀበሌዎች ድንበሩን ለመለየት ህዝበ ውሳኔ አካሂደው ነበር። ይህ በሁለት ክልሎች መሃከል የድንበር አለመግባባት ጥያቄ ሲነሳ ምላሽ የሚያገኝበት ህገመንግስታዊ ስርአት በመሆኑ ተገቢ እርምጃ ነበር። ይሁን እንጂ፣ የትኛው ቀበሌ ወደየትኛው ክልል መካለል እንደሚገባው በህዝበ ወሳኔ ማረጋገጥ ቢቻልም፣ መሬት ላይ ያሉ መንደሮችና ቤተዘመዶችን ሁለት ቦታ ሊሰነጥቅ ስለሚችል ከህዝብ ጋር በመወያያት መሬት ላይ የማካለል ሥራ መከናወን ነበረበት። ይህ ግን ሳይሰራ ተትቷል። የተተወው ለፈጣሪ  ይሁን ለሌላ ምድራዊ አካል እስሰካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።

ይህ መሬት ላይ ሳይካለል የቆየ የሁለቱ ክልሎች ድንበር፣ ወሰኑ ስለማይታወቅ ከሁለቱ ክልሎች ነዋሪዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ወዝግብ የሚያስነሳበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ብቻ አይደለም፤ በሁለቱ ክልሎች ድንበር ላይ የሚኖሩ ሰዎች እንደማንኛውም ሁለት የተለያየ ብሄራዊ ማንነት ያላቸው ህዝቦች አዋሳኝ አካባቢዎች እንደሚሆነው ተለዋዋጭ ማነነት (shifting) ያላቸው ሰዎች በተለይ ፖለቲከኞች የራሳቸውን ጥቅም ፍለጋ እንደየሁኔታው አንዴ ከወዲህኛው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከወዲያኛው በመወከልና በመሾም ህዝቡን ግራ ሲያጋቡ የቆዩበት ሁኔታ ነበር። እነዚህ በተለዋዋጭ ማንነት፣ ጥቅም ፍለጋ ወዲያና ወዲህ የሚወዛወዙ ፖለቲከኞች የሚኖሩበትም ማህበረሰብ አብሯቸው እንዲዋዥቅ ሲያደርጉ ነው የቆዩት። ይህ ሁኔታ ደግሞ የድንበሩን ጉዳይ አወዛጋቢ የበለጠ ውስብስብና አወዛጋቢ አድርጎታል። በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይ ቦረና አካባቢ ይህ ችግር በተጨባጭ አጋጥሟል። ለእነዚህ ዋዣቂ ሰዎች ከነማህበረሰባቸው እዚህም እዚያም እንዲሆኑ ያስቻላቸው የሁለቱ ክልሎች ድንበር መሬት አለመካለሉ ነው።

ይህ ሁኔታ የፈጠረው፣ መደናገር፣ ውዝግብና አለመግባባት ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ለሌሎች ግጭት መቀስቀስና ጥቃት መሰንዘር ለሚፈልጉ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የምትዋሰንበት ክልለ ነው። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከጅቡቲም ጋር በጨረፈታ ይዋሰናል። ይህ ሁኔታ በተለይ ሶማሊያ ለረጅም ዓመታት መንግስት አልባ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ፣ ክልሉን ማንኛውም ህገወጥ ንግድ የሚዘዋወርበት ቀጠና እንዲሆን አድርጎታል። ወደኢትዮጵያ የሚገባና የሚወጣ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በአመዛኙ ይህንኑ መስመር የተከተለ ነው። ከደቡብ ምስራቅ እስከሰሜን ምስራው የሃገሪቱ አካባቢዎች ወደሃገር ውስጥ የሚዘልቀው ህገወጥ የንግድ ሸቀጥ ይህን መስመር የተከተለ ነው። ይህ የህገወጥ ንግድ መስመር ሸቀጥ ወደኢትዮጵያ የሚገባበት ብቻ አይደለም። ከኢትዮጵያም በህገወጥ መንገድ ሸቀጥ ይወጣበታል። በተለይ በህገወጥ መንገድ ከሃገሪቱ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ (ዶላር) በአብዛኛው በዚህ መስመር የሚወጣ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት በሰፈነበትና የህግ የበላይነት በተረጋገጠበት መጠን የህገወጥ ንግዱ እንቅስቃሴ መንገድ ይጠብባል። በመሆኑም በዚህ ህገወጥ ንግድ ውስጥ የሚሳተፉ የወንበዴ ቡድኖች የህግ የበላይነት ሊከበር የማይችልበትን ሁኔታ መፍጠር ይፈልጋሉ። ህገወጥ ንግዱ በወንበዴ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ካሉ ኪራይ ሰብሳቢ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የክልልና የፌደራል መንግስት ሰላም አስከባሪ ሃይል አንዳንድ አባላትና አዛዦች ጋር በመመሳጠር የሚከናወን ነው። ይህ የጥቅም ትስስር አካባቢውን የግጭትና የትርምስ ቀጠና በማድረግ የህግ የበላይነትን ስፍራ የማሳጣት ተግባር በሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትና ድጋፍ የሚነናወን እንዲሆን ያደረገበት ሁኔታ አለ።  

ሰላምና መረጋጋትን በማጥፋት የህግ የበላይነትን የሚደፍቅ ሁኔታ መፍጠር ግን ሰበብ ይፈልጋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች መሬት ላይ ሳይካለል የተቀመጠው የድንበር ጉዳይ ግጭት ለመቀስቀስ አመቺ ሰበብ ሆኗል።

በዚህ ሁኔታ፣ በኦሮሚያም ይሁን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስታት ጥብቅ ቁጥጥር መላወሻ ያጡት የህገወጥ ንግድ ወንበዴዎች፣ ከአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሰላም አስከባሪ ሃይል አዛዦችና አባላት ጋር በመመሳጠር የድንበር ምክንያት የህዝብ ለህዝብ ግጭት የተፈጠረ በማስመሰል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ በመፈጸም፣ መንደር በማቃጠል፣ በዘረፋ ወዘተ የህግ የበላይነትን ለማስከበር አዳጋች የሆነ ግርግር ፈጥረዋል። ይህ አካሄድ ለዘለቄታው አንዱ ህዝብ ሌላው ላይ እንዲነሳና ለቁጥጥር የማያመች ግጭት የመቀስቀስ ዓላማ ያለው ነው። ይህ ሁኔታ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተጨባጭ ታይቷል።

የሚገርመው የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስ በኪራይ ሰብሳቢ የሰራ ሃላፊዎችና የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት የተሰነዘረው ጥቃት እንደታሰበው አጠቃላይ የእርስ በርስ ግጭት መፍጠር አልቻለም። በድንበር አካባቢ የሚኖሩት የኦሮሞና የሶማሌ ተወላጆች አንዱ ሌላው ላይ ሜንጫ አልሰነዘሩም፣ ጦር አልተወራወሩም፣ ክላሽንኮቭ አልተታኮሱም። በትቃቱ የተገደሉትና የተፈናቀሉት ሰዎች፣ ለሞትና ለመፈናቀል ያበቃቸው የተደራጀ  መለዮ ለባሽ ታጣቂ ኃይል መሆኑን መስክረዋል። ህዝብ ተነሳብን፣ ጥቃት ሰነዘረብን የሚል ምስክርነት የሰጠ አንድም ተፈናቃይ አልተሰማም።

በአጠቃላይ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል የተቀሰቀሰው ብዙዎች የሞቱበት፣ ግማሽ ሚሊየን ያህል ሰዎች የተፈናቀሉበት ግጭት በድንበር ምክንያት የተፈጠረ አይደለም፤ የህዝብ ለህዝብ ግጭትም አይደለም። ግጭቱ በአካባቢው የህግ የበላይነትን ለማጥፋት በህገወጥ ንግድ ወንበዴዎችና በኪራይ ሰብሳቢ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች የተፈጠረ ነው። እነዚህ የህግ የበላይነትን ለማጥፋት የተነሱ ቡድኖችና ግለሰቦች ግጭቱ የህዝብ ለህዝብ ግጭት እንዲሆን ለማድረግ ሞክረዋል። ከሁለቱ ክልሎች አወሳኝ አካባቢዎች ዘልቀው ጥቃት ሰንዝረዋል። ይህን ያደረጉት በአጠቃላይ በኦሮሞና በሶማሌ ህዝብ መሃከል መብረጃ የሌለው ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ነው።  

ከድንበር በብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ርቀው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢዎች በርካታ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ግጭቱ የድንበር ሳይሆን ድንበርን ሰበብ በማድረግ የህግ የበላይነትን ለማጥፋት በኪራይ ሰብሳቢዎችና ወንበዴዎች የተፈጠረ መሆኑን ያመለክታል።

እንግዲህ፤ አሁን ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች በዚህ ወንበዴዎቸና ኪራይ ሰብሳቢዎች በፈጠሩት ግጭት ተፈናቅለዋል። የሞቱ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ወገኖች ምን ያህል እንደሆኑ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም። የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ጉዳዩን መርምሮ ይፋ በሚያደረገው ሪፖርት እነዚህ መረጃዎች የገለጻሉ ብለን እንጠብቃለን።

አሁን በዚህ በህገወጦች ድርጊት ከመኖሪያ አካባቢያቸውና ከንብረታቸው የተፈናቀሉ ግማሽ ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎቸ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማቅረብና መልሶ ለማቋቋም ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።  እስካሁን ባለው መረጃ ኦሮሚያ ውስጥ ከ270 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተሰባስቧል። ተፈናቃዮቹን ለማጽናናት በርካታ ዜጎች፤ ባለሃብቶች፣ አትሌቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሰራ ሃላፊዎች ወዘተ በርካታ ተፈናቃዮች በሰፈሩባቸው ሃረርና ድሬዳዋ መጠለያ ጣቢያዎች በመገኘት ጎብኝተዋል።

ይሁን እንጂ፤ ችግሩ በተለይ ከፍተኛ ተፈናቃዮችን ያስተናገደው የኦሮሚያ ክልል በተወሰነ ደረጃ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ችግር ብቻ ተደርጎ የተወሰደበት ሁኔታ አለ። ልብ በሉ፤ ይህ ችግር በሁለቱ ክልል ህዝቦች መሃከል የተፈጠረ አይደለም፤ የሁለቱ ክልሎች መንግስታት የሚመሩትም አልነበረም። እርግጥ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የጸጥታ ኃይሎች እጅ አለበት – የኪራይ ሰብሳቢ ሃላፊዎች እጅ። ይህ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነት እንደአመለካካት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ያመለክታል። ይህ ደግሞ ችግሩን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ብቻ ሳይሆነ ሃገራዊ ችግር እንዲሆን ያደርገዋል።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለቱን ክልሎች የሚያቋርጡ መንገዶች የሃገሪቱ የወጪ ንግድ የሚካሄድባቸውም ናቸው። በተለይ ከኦሮሚያ ሃረርጌ ዞኖች የሚነሳው የወጪ ንግድ ጫት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን አቋርጦ ነው የሚያልፈው። በሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች የህግ የበላይነትን ማጥፋትን መድረሻው አድርጎ የተቀሰቀሰው ግጭት፣ ይህን የወጪ ንግድ ገትቶታል። እስካሁን ክልሎቹን የሚያቋርጡ መንገዶች በፌደራል የሰላም አስከባሪ ኃይል ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ወሳኔ ቢተላለፍም፣ ይህ ተግባራዊ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። መጠኑ ምንም ያህል ይሁን፣ በዚህ ምክንያት ሃገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እያጣች ነው። ይህ ደግሞ ችግሩ የሁለቱ ክልሎች ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱ ችግር እንዲሆን ያደርገዋል።

ከምንም በላይ ደግሞ በግኝቱ ምክንያት ከኑሯቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፣ በየትኛውም ክልል ከሚኖሩ ህዝቦች ጋር በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር የሚኖሩ ዜግነትን የሚጋሩ ህዝቦች። ይህም ችግሩን የመላ የሃገሪቱ ህዝብ ችግር ያደርገዋል።

እርግጥ ነው፤ የኢፌዴሪ መንግስት በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረውን ችግር እንደሃገራዊ ችግር ተመልክቶታል። በሁለቱም ክልሎች የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ ሰዎች ከኑሯቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ወሳኔ አሳልፏል። አፈጻጸሙ ግን በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በኩል ችግር እንዳለበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዳግም ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለግጭት ስጋት ያለባቸው የድንበር አካባቢዎችን በነጻ የጸጥታ ከጠናነት በመከለል ሰላም የመጠበቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑም ይታወቃል።

ይሁን እንጂ፤ ችግሩን የመላው ኢትዮጵያውያን ችግር መሆኑን በማሳየት ወቅታዊ ችግሩ ላይ በመረባረብ ረገድ፣ እንዲሁም ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች ይታያሉ። በግጭቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው ህዝባዊ እንቅስቃሴ በኦሮሚያ ክልል የተገደበ ነው። እርግጥ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞዎች ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በላይ ያላቸውን አንድነት አጉልቶ በሚያሳይ ሁኔታ ወገኖቻቸውን ለመርዳት የሚደነቅ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። የተቀሩት የትዮጵያ ክልሎች ግን ጉዳዩን እንደሃገር ጉዳይ ሳይሆን፣ እንደ ባዳ የሩቅ ተመልካች የሆኑበት ሁኔታን ታዝበናል።

በመሆኑም በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረውን የተፈጠረው ችግር ክልላዊ ብቻ ሳይሆን ሃገራዊ መሆኑን ታሳቢ በማደረግ፣ እንዲሁም በተፈጠረው ግጭት የተጎዱት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህን በኪራይ ሰብሳቢዎችና በወንበዴዎች ትብብር የተፈጠረ ችግር እንደ አንድ አካባቢ ችግር ሳይሆን በማንኛውም አካባቢ ሊፈጠር እንደሚችል የሃገር ችግር በመገንዘብ፣ መቼምና የትም እንዳያጋጥም መንቃት ያስፈልጋል። በግጭቱ ከቤትና ንብረታቸው ተፈናቀለው ለእለት ኑሮና ለዘለቄታው ለመቋቋም የወገንን ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች የሚደረገውም ድጋፍም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው። ችግሩ ሃገራዊ ችግርና ነው።       

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy