Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አላዋቂ ሳሚ

0 465

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አላዋቂ ሳሚ ∙ ∙ ∙ ∙ ∙
ስሜነህ

መንግስት በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረውን የአገሪቱን ሃይል የማመንጨት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ ከ7 በላይ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችና 3 የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ተገንብተው ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉ ይታወቃል። ተገንብተው ሥራ ላይ ከዋሉት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች  ዋናዎቹ የግልገል ጊቤ 1ኛ (180 ሜጋ ዋት)፣ የጢስ ዓባይ 2ኛ (73 ሜጋ ዋት)፣ የተከዜ ኃይል ማመንጫ (300 ሜጋ ዋት)፣ የግልገል ግቤ II (420 ሜጋ ዋት)፣ የበለስ ኃይል ማመንጫ (460 ሜጋ ዋት) እና የፊንጫ አመርቲ ነሼ ኃይል ማመንጫ (97 ሜጋ ዋት)  የግቤ ሶስት(1870 ሜጋዋት)ሲሆኑ በነፋስ ኃይል ማመንጫዎች በኩል የአሸጐዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ (12ዐ ሜጋ ዋት) የአዳማ 1 የነፋስ ኃይል ማመንጫ (51 ሜጋ ዋት)  የአዳማ ሁለት የነፋስ ኃይል ማመንጫ (153 ሜጋ ዋት) ናቸው። በአጠቃላይ እነዚህንና ሌሎች የኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት የማመንጨት አቅማችን 4400 ሜጋ ዋት ደርሷል።

ሃገራችን ከተሃድሶ ወዲህ በተከታታይ ባስመዘገበችው ፈጣን ልማት በየአመቱ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የሃይል ፍላጎት እንደተፈጠረ መረጃዎች ያመለክታሉ።ስለሆነም ከዚሁ  ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ግዙፍ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ይግኛሉ።  በአሁኑ ወቅት በድምሩ ከ 8,464 ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት ከሚችሉት ውስጥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (6,454 ሜጋ ዋት)፣ የኮይሻ ኃይል ማመንጫ (2160 ሜጋ ዋት)፣ ገናሌ ዳዋ 3ኛ (254 ሜጋ ዋት) ረጲ የደረቅ ቆሻሻ (50 ሜጋ ዋት) ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው። ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ የማመንጨት አቅማችን ከ12,800 ሜጋዋት በላይ እንደሚደርስ ይታወቃል።በዚህም የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ለጎረቤት ሐገሮች በመሸጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይረዳል። ከሃድሮ ኢነርጂ ልማት ጎን ለጎን የጂኦተርማል ኢነርጂን በአሉቶ ላንጋኖ አካባቢ በሙከራ ደረጃ 7 ሜጋ ዋት ብቻ ለብዙ ጊዜ ሲያመነጭ የቆየውን የማመንጨት አቅም ወደ 77 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

ያም ሆኖ ግን ከአጠቃላይ የሃገሪቱ የማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከከፊል በላይ የማመንጨት አቅም ያለውን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አስመልክቶ የተለያዩና አፍራሽ የሆኑ ዘገባዎች ዛሬም በሃገር አፍራሾች እየወጡ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ስራው ሲጀመር ከ300 ያልዘለሉ ሰራተኞች የነበሩ መሆኑ የሚታወስና የግዙፍ ግንባታ ፕሮጀክቶች ባህሪ ነው። አስፈላጊ መሰረተ ልማት ባልተሟላበት እና የግንባታው ስራ ከሚጠይቀው ጊዜ አስቀድሞ ቅጥር መፈጸም ኪሳራና የማይቻል ነው።ለምሳሌ የሃይድሮ ሜካኒካል ስራው ሊጀመር የሚችለው የሲቪል ግንባታው ከፊል አካባቢ ሲጠናቀቅ መሆኑ አያከራክርም። ስለሆነም ግንባታው በተጀመረ ወቅት የሃይድሮ ሜካኒካል ሙያተኞች እና ቁሳቁሶች በቦታው ላይ ሊኖሩ አስፈላጊ አይሆንም ማለት ነው። በአንጻሩ የግንባታ ስራው እየተጋመሰ በሚመጣ ሰአት ደግሞ የሁሉም የግንባታ ዘርፎች አብረው የሚከናወኑ ስለሚሆን የሰራተኛው ቁጥር የሚበዛ ምናልባትም የመጨረሻው የሰው ሃይል በስፍራው ላይ እንደሚኖር አያጠያይቅም።

በዚሁ አግባብ ከ300 የጀመረው የሰው ሃይል 1000፤ 2000፤ 4000፤ 6000፤ እያለ አምና ላይ ከ10, 000 ሺህ ሰራተኞች በላይ ስራው ላይ ሊሰማሩ ግድ ብሎ ነበር። አሁን ከ60 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው ግንባታ ልክ ከላይ በተመለከተው አግባብ ከ10ሺህ ተነስቶ 9ሺህ 7ሺህ 5ሺህ እያለ መጨረሻ ከ300 በታችም እንደሚሆን የሚጠበቅና የስራው ባህሪ ነው።

በዚህ አግባብ እየሄደ ባለው ስራ ሲጀምር ከ300 መነሳቱን እና ከላይ በተመለከተው አግባብ የሆደውን የሰው ሃይል ያላወሱ ሃይሎች ባላዋቂ ሳሚ አግባብ የመውረዱን ተፈጥሯዊ ጉዳይ ከሰራተኞች መባረር ጋር በማያያዝ የግንባታውን መቆም አዋጅ እያስነገሩ ነው። ጉዳዩ ግን ከላይ የተመለከተው የምህንድስና ጉዳይ ነው። አንድ ተራ ግለሰብ እንኳ ለሚገነባው ቤት መሰረት ሲቆፈር እና በአርማታ ሙሌት ጊዜ የሚፈልገውን የሰው ሃይል በማጠናቀቂያው ጊዜ የማይፈልግ እንደሆነ በሚታወቅበት አመክንዮ የሰራተኞችን ቅነሳ ከግንባታ መቆም ጋር ማያያዝ የሚሆነው አላዋቂ ሳሚነት ነው።

ሌላውና ለዚሁ ቀሽም ዘገባቸው የቀረበው ምክንያት የሽፍት ጉዳይ ነው። ግንባታው ሲጀመር ቀድሞ ነገር ሽፍት ያልነበረ እና ሊኖርም እንደማይችል ይታወቃል። ስራው ወደሩብ ሲጠጋ በሁለት ሽፍት እያለ ሲፋፋም ወደ3 ሺፍት እንደሚሄድም መገመት አይከብድም። ከዚያ እየተጠናቀቀ ሲመጣ ደግሞ ከላይ በተመለከተው የሰው ሃይል አመክንዮ ሸፍቱም ሊቀንስ የሚችል መሆኑ እውነትና የስራው ባህሪ ነው። ከዚህ እውነታ ጋር ተጣርሶ ዘራፍ ማለት አላዋቂ ሳሚነት ነው።

እናውራው ከተባለ ደግሞ ግንባታው የማይቆምባቸው ብዙ አመክንዮዎችን ማውራት ይቻላል። ለማቆም ይገዳደራሉ ተብለው የተፈሩ ምክንያቶችንም ከተሻገርን 6 አመታትን ባስቀጠርንበት ሰአት ላይ ይህ አይነቱ ጨዋታ በእርግጥም አላዋቂ ሳሚነት ነው የሚሆነው። ከነካነው አይቀር ጥቂቶቹን የማይቆምበትን ምክንያቶች ብናነሳ ተገቢ ይሆናል።

በከፍተኛ የህዘብ መነሳሳትና ተሳትፎ የታጀበው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እየተከናወነ ለመሆኑ ለማንም ክፍት በሆነው የግንባታ ስፍራ ተገኝቶ መመልከት ይቻላል። እስካሁን ከ300ሺህ በላይ ዜጎች ከ300 በላይ የውጭ ሚዲያዎችን ጨምሮ ዲፕሎማቶችና ተመራማሪዎች የጎበኙት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ክፍት ለመሆኑ ምስክሮች ይሆናሉ። ሌላው ቀርቶ እንኳንስ ስለመቆሙ እየተጠናቀቀ ለመሆኑ ከመሰከሩቱ ውስጥ የግብጽ ጋዜጠኞች መሆናቸውንም ማስታወስ ተገቢ ነው።

ሃይተም ሞሐመድ ባለፉት አምስት ዓመታት ለዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የሠራ ግብፃዊ ጋዜጠኛ ነው። በእነዚህ አምስት ዓመታት ሃይተም ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ስለ ግብፅ የፖለቲካ ሁኔታ ዘግቧል። የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪውና ጋዜጠኛው ሃይተም  ‹‹ናይል የግብፅ ሳምባና ልብ ነው፤›› ብቻ ብለው ከሚዘምሩት ጋር አብሮ ለ 5 አመታት የዘመረ እንደሆነ ገልጾ ከጉብኝቱ በኋላ የነበረው ስሜት ስለመለወጡና በትብብር የመልማትን ዋጋ በሚገባ ማጤኑን እንዲህ አረጋግጧል።

‹‹አሁን ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ የአገሪቱን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሁኔታ በሚገባ ካየሁና ወደ ግድቡ መጥቼ ጉብኝት በማድረግ የግድቡን ማኔጀር ኢንጂነር ስመኘውንና ሌሎች ግድቡ ላይ የሚሠሩ ሰዎችን ካዋራሁ በኋላ ያለኝ የግል ድምዳሜ የተለየ ነው። ጉብኝቱ በጣም ጠቃሚ ነበር። ግልጽነት የተሞላበትም ነበር። አሁን በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የመተባበር ዕድልን ማየት ችያለሁ፤ሁለቱም አገሮች ጉዳዩን በጋራ ዓይን ማየት ቢችሉ የተሻለ ዕድል መፍጠር ይቻላል። ኢትዮጵያ በኃላፊነት ከሠራችና ግብፅም ከተባበረች ግድቡ ሥጋት አይሆንም። ይህ ከሆነ ግድቡ ለኢትዮጵያና ለግብፅ ብቻ ሳይሆን ለናይል ተፋሰስ ወንድሞቻችን ሁሉ የሚተርፍ ነው የሚሆነው፤›› በማለት የግድቡን እውንነትና ሃገራችን ስትሄድበት የነበረው መንገድ ሁሉ ትክክል መሆኑን እግረ መንገዱን አረጋግጧል።

እንዲህ ሲልም ሃይተም ይጨምራል። “በኢትዮጵያ በነበረኝ የስድስት ቀናት ቆይታ ያገኘሁት ትምህርት ይህ ነው። ይህን መልዕክት ነው ለግብፃዊ ታዳሚዎቹ የማደርሰው፡፡ ውኃ ተፎካክረን የምናገኘው ዕቃ አይደለም። የሕይወት መሠረት የሆነ፣ ለማደግና ኢኮኖሚያችንን ለማበልፀግ፣ በሕይወትም ለመቆየት የሚያስፈልግ ነገር ነው። ሚዲያ እውነተኛውን መረጃ ለሕዝቡ በማድረስ ውሳኔ እንዲሰጡ ማድረግ አለበት።”  

ላለፉት 6 አመታት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ስትዘግብ እንደነበር የምትጠቅሰው ሌላኛዋ ግብጻዊት ጋዜጠኛ አያህ አማን “ባለፉት ስድስት ዓመታት ስለ እነዚህ ጉዳዮች የምዘግበው ወይም  ዋነኛ ጉዳይ የሆነውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተለይ ስጽፍ ሳላይ ነበር፤ ግድቡን በአካል ማየት፣ ፎቶ ማንሳትና ስለታዘብነው ነገር ለሕዝብ መናገር ለምትጽፈው ነገር ተአማኒነት ይገነባል። ሕዝባችን ያለውን ቁጣና ፍራቻም ሊቀንስ ይችላል። ሁሉንም ነገር በአንዴ መቀየር አይቻልም። ነገር ግን አሁን ቢያንስ የግድቡን እውነታ መቀበል ይቻላል። ግድቡ ጉዳት እንደማያመጣ በማመን ሁለቱንም አገሮች አሸናፊ የሚያደርግ አሠራር ቢተገብሩ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፤” በማለት የግድቡን መቆም በተመለከተ ስጋት ከሆነችው ሃገረ ግብጽ የመጣችው አያህ አማን የግድቡን እውንነት በተቀበለችበት አግባብ ሳያዩ ሊያሳዩን መሞከር ሳያዩ የሚያምኑ ብጹአን ናቸው በሚል ቅኝት ሳይሆን የሚታየው ባላዋቂ ሳሚነት ነው።

በእርግጥ በዚህ የግንባታ ሂደት በርካታ እና ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ከውስጥም ከውጭም የገጠሙትና ምንም እየገጠመው መሆኑ አይተባበልም።ያም ሆኖ ግን በራስ አቅም ለሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያውያንም ምናልባትም ከአቅማቸውም በላይ ለማለት በሚያስደፍር መልክ በንቃት እየተሳተፉ ነው። በሌላ በኩልም በግድቡ ግንባታ ላይ ቅሬታና የተበሻቀጠ አቋም ይዘው ከነበሩ ሃይሎች መካከል ዋና የሆነችው ሃገረ ግብጽ ወደትክክሉ መስመር ገብታለች። እንደሚታወሰው ባሳለፍናቸው 6 አመታቶች ሁሉ በግብፅ በኩል የተለያዩ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ተደምጠዋል። የግድቡ መገንባት በግብፅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር እና ይልቁንም ህልውናቸውን እንደሚፈታተን ጭምር በመግለጽ ተቃውሟቸውን  በተደጋጋሚ ማሰማታቸውም ይታወሳል። እውነታው ደግሞ የዚህ ተቃራኒ መሆኑ በተጨባጭ መረጃዎች ቀርቧል። ግድቡ የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በባለሙያዎች ጥናት ተረጋግጧል። ፍትሃዊ የአባይ ውሃ ክፍፍልን መሰረት ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑም ተወስቷል። የግድቡ መገንባት በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ አለመኖሩ በኢትዮጵያ በኩል ቀድሞ የታወቀና በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።

ይህም የተከናወነው ኢትዮጵያን ጨምሮ ቅሬታ አለን ሲሉ በነበሩት ሀገራትም ነው። በሶስቱ የተፋሰሱ አገራት (ኢትዮጵያ፤ግብፅና ሱዳን) ትብብር  የተመራው ይህ የአዋጭነት ጥናት በነሱ ይሁንታ ከተመረጡና ከየአገራቱ የተውጣጡ ስድስት ባለሙያዎችና በሶስቱ አገራት በጋራ የተመረጡ አራት ዓለም ዓቀፍ ባለሙያዎችንም ያካተተ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የጥናትና የዲዛይን ሰነድ በመመርመር ፣በግንባታው ቦታ በመገኘትና ሂደቱን በመቃኘት፣ በሶስቱ አገሮች ውስጥ ለስድስት ጊዜ ያህል በመሰባሰብና በተነሱ ጉዳዮች ላይ በመወያየት እንዲሁም ከግድቡ የግንባታ ተቋራጮችና አማካሪዎች ጋር በመመካከር የደረሰበትን የመጨረሻ የጥናት ውጤት ለሶስቱም  ሃገራት ማቅረቡ ይታወሳል።

በዚህም የኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የዲዛይን ስራ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ የዲዛይን መመዘኛና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ፤ ለሶስቱም አገራት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ፤እንዲሁም በሁለቱ ተጋሪ አገራት (ግብፅና ሱዳን) ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ቡድኑ በጥናቱ አረጋግጧል።

ይህ ብቻ አይደለም በተፋሰሱ አገራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያስከትል፤ በአንፃሩ ልማትን የሚያፋጥን ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑም ተመልክቷል። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት  የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት የጀመረችው ጤናማ አካሄድ አንዱ አካል መሆኑንም ጭምር ያረጋገጠ ጥናት ነው። የዓለማችን  ትልቅ ስጋት እየሆነ የመጣውን  የአየር ብክለትን ለመዋጋት አገሪቷ እየሄደችበት ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስኬትም ያረጋገጠ ነው። በእነዚሁ  እና ቅሬታ ሲያቀርቡ በነበሩ  ሃገራትም የሚኖረው ጠቀሜታ እጅጉን የላቀ መሆኑ አሁን ታምኖበታል። እነዚህ ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በቀላሉ የሚያገኙበት ዕድል በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሚፈጠር መሆኑም ላይ ግልጽ እምነት መያዛቸው ተገቢ ነው። በተለይም የተፋሰሱ የታችኛው አገራት ለሆኑት ሱዳንና ግብፅ ጥቅሙ ቀላል እንዳልሆነም ተረጋግጦ ሃገራቱ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።  

በሌላ በኩል የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በ1984 በጀት ዓመት የነበረው 3,578 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመርና 82 የማከፋፈያ ጣቢያዎች  በአሁኑ ወቅት ከ 18 ,018  ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመርና 140 በላይ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ደርሰዋል። ከዚህ ውስጥ በአለም ደረጃ የመጨረሻው የሆነው ባለ 500 ኪሎ ቮልቱ የሃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ተጠናቋል። እኒህና መሰል የግንባታ እና የስምምነት ሂደቶች በተጠናቀቁበትና ይልቁንም ግንባታው እውን እንደሆነ ስጋት የነበሩ ሃገራት እየመሰከሩ ባሉበት ሁኔታ የምህንድስና የስራ ተፈጥሮን ተከትሎ የሚደረጉ የሰራተኛ ቅነሳዎችን ከግንባታ መቆም ጋር ማያያዝ ያላዋቂ ሳሚነት ብቻ ነው የሚሆነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy