Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አገራችን ያለችበት ሁኔታ ሰላማዊና የተረጋጋ ነው!

0 277

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አገራችን ያለችበት ሁኔታ ሰላማዊና የተረጋጋ ነው!

                                                            ታዬ ከበደ

አንዳንድ የራሳቸው ዓላማ ያላቸው ፅንፈኞች በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መጠነኛ ችግሮችን ሲመለከቱ በመላ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የሌለ በማስመሰል ውዥንብር መንዛት የተለመደ ስራቸው ሆኗል። እነዚህ ሃይሎች በአገራችን ውስጥ የሚከሰቱት ችግሮች ከህዝቡና ከመንግስት አቅም በላይ ስላልሆኑ በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆናቸውን አያምኑም።

ሆኖም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት ሊያስቀር የሚችል መፍትሔም እየተሰጣቸው ነው። ምንም እንኳን ግጭቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ሊከሰቱ ቢችሉም፣ ይህ ሁኔታ ግን አጠቃላይ የአገሪቱን ሰላም አለመሆን የሚያሳይ አይደለም። እንዲያውም ከችግሩ ተገቢ ትምህርት በመውሰድ መቋጫ ሊበጅላቸው የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል ይሆናል።

ግጭት በዓለም ላይ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚከሰት ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ ማህበራዊ መስተጋብር እስካለ ድረስ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ውስጥ መኖሩ አይቀሬ ነው። ለነገሩ የሰው ልጅ ከራሱ፣ ከቤተሰቡ፣ ከማኅበረሰቡ አሊያም ከተፈጥሮ ጋር መጋጨቱ ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለና ነገም የሚኖር ክስተት ነው።

እንኳንስ በአንድ ቤተሰብ፣ ቀዬ፣ መንደር፣ አካባቢ፣ አገር፣ አህጉርና ዓለም ውስጥ የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በጋራ እየተጠቀመ “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” በሚል መተሳሰብ ውስጥ የሚኖረው የሰው ልጅ ቀርቶ፤ ወንዝ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ግዑዛን ድንጋዩችም ቢሆኑ በተፈጥሮ ዑደት መዘውር ሂደት ውስጥ ሊጋጩ ይችላሉ። እናም ግጭት ባህሪያዊ የተፈጥሮ ህግ ነው።

ዋናው ቁም ነገር የግጭቱን መንስዔ አጥርቶ ከማወቁ ላይ ነው። መንስዔው ምናልባትም ዓለማችንን በአያሌው እየፈተናትና እየናጣት ያለው የተፈጥሮ ሃብቶች እጥረት ወይም በህዝቦች መካከል ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን ጥቂቶች ከራሳቸው ጥቅም አኳያ በመመዘን የሚፈጥሩት ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል አያጠያይቅም።

ታዲያ ይህን እውነታ ወደ አገራችን በተለይም ወደ ከሁለቱ ተጎባራች ክልሎች አኳያ ስንመለከተው ግጭቱ የህዝብን ፍላጎት በማይወክሉ ህገ ወጦች አማካኝነት ሊያገረሽ ችሏል።

በዚህም ምክንያት በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ያሉ ትጥቅ የያዙና ጥቂት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሃይሎችና ግለሰቦች በድንበር ማካለል ሰበብ ሰላምን አውከዋል። በዚህም ሳቢያ የፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ ምክንያት ሆነዋል።

ይሁን እንጂ እንደ እኛ ባለ ራሱን በራሱ በሚያርምበትና የአሠራር ስርዓት በተዘረጋበት ፌዴራላዊ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ከድንበር ማካለል ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችል ግጭት ሊኖር አይችልም። ሁሉም ነገር መፍትሔ አለው።

ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓቱ በአጎራባች ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተለው የራሱ መንገድ አለው። አገራችን ለፌዴራላዊ የመንግሥት ሥልጣን አወቃቀር ጀማሪ በመሆኗና ባለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥርዓቶች ውስጥ የግፍ ቀንበር ተጭኖበት የነበረው የአገራችን ህዝብ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለጋነት አኳያ ያለው ግንዛቤ በሚፈለገው መጠን ያልዳበረ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም። ሆኖም ተግዳሮቶቹ ሥርዓቱ ራሱን በራሱ እንዲያርም እንዲሁም ከችግሮቹ ትምህርትና ተሞክሮ በመውሰድ እንዲጎለብት የሚያስችለው ነው።

እርግጥ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓቱ በአጎራባች ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚከተለው የራሱ መንገድ አለው። ለነገሩ አገራችን ለፌዴራላዊ የመንግሥት ሥልጣን አወቃቀር ጀማሪ በመሆኗና ባለፉት ፊውዳላዊና አምባገነናዊ ሥርዓቶች ውስጥ የግፍ ቀንበር ተጭኖበት የነበረው የአገራችን ህዝብ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ ለጋነት አኳያ ያለው ግንዛቤ በሚፈለገው መጠን ያልዳበረ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይቀርም።

ፌዴራላዊ ሥርዓቱ መቼም ቢሆን ለግጭት መንስኤዔ ሊሆን አይችልም። ሥርዓቱ ለአገራችን ህዝቦች የመቻቻልና የአብሮነት ዋስትና እንጂ የልዩነትና የግጭት መንስዔ አይደለም። በራሳቸው ፈቃድ አንድ የጋራ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ቃል ገብተው ህገ መንግሥቱን ዕውን ያደረጉት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው። ስለሆነም የአገራችን ህዝቦች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ የመሠረቱትን ፌዴራላዊ ሥርዓት መልሰው የግጭት ምክንያት ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ ማሰብ ጤናማ ምልከታ አይሆንም።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከግጭት የሚሰንቁት ምንም ዓይነት ተስፋ የላቸም። ተስፋቸው የተመሠረተው ከሠላም፣ ከልማትና ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ነው። ከግጭት የሚጠቀም ህዝብ ባለመኖሩም እነዚህን ተስፋዎች በማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት ላይ ለማኖር አስተማማኝ ሰላም መፍጠር የግድ ነው።

በመሆኑም ለበርካታ ዓመታት በሠላም የኖሩት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝቦችም እንደ ማንኛውም ህዝብ ጥቅማቸው ያለው ከሠላም እንጂ ከግጭት አለመሆኑን ይገነዘባሉ።

ስለሆነም በሁለቱ ክልላዊ መንግሥታት ህዝቦችም መካከል ግጭት የሚፈጠርበት መሠረታዊ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ጥቂት በአመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች አሊያም ታጣቂዎች የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ በድንበር አካባቢዎች ግጭት መፍጠራቸው ለዘመናት በፍቅር አብረው የኖሩትን የሁለቱን ተጎራባች ህዝቦች ፍላጎት የሚወክል አይደለም።

የትኛውም የህበረተሰብ ክፍል ከሚፈጠረው ግጭት ተጠቃሚ አይሆንም። የሚያስከፍለው ዋጋም ከባድ ነው። ግጭት በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግሥት መሪነት በልማት ላይ ሌት ተቀን በመሳተፍ ህይወቱን ለመለወጥ የሚያስበውን የየክልሎቹን ህዝቦች የሥራ ሞራል የሚሰልብ ነው። ኢንቨስትመንታቸው የውጭ ባለሃብቶችን እንዳይስብም ማነቆ ይሆናል።

የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ክልሎቹ ሊወጡት የሚገባቸውን የተናጠልና የአብሮነት ሚናን ያቀጭጫል። በሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ላይም እንቅፋት ይሆናል።

እንዲህ ዓይነቶቹ ከድንበር መካለል ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ጥቅሞችን የሚያኮሰምኑ ግጭቶችን ዘላቂ በሆነ መንገድ መዝጋት ይገባል። አላስፈላጊ በመሆኑም የሁለቱም ክልል ህዝቦችም ይሁኑ የሚመለከታቸው አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት ተገቢ መፍትሔ ለመስጠት ጊዜ ሊወስዱ አይገባም። ታዲያ እዚህ ላይ በጥቂት አካባቢዎች የተከሰተ ችግርን የሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች መገለጫ አድርገው ውዥንብር የሚነዙ ኃይሎችን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማውገዝ አገራችን እንደ ወትሮው ሰለማዊና የተረጋጋች መሆኗን ማሳየት ይኖርብናል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy