Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ የግለሰቦች ፓርቲ አይደለም!

1 443

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ የግለሰቦች ፓርቲ አይደለም!

                                                         ደስታ ኃይሉ

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዩታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከፍተኛ አመራሮች መልቀቅ እየተሰማ ነው። በዚህም ሳቢያ የተለያዩ መላ ምቶች ሲሰነዘሩ እየሰማን ነው። ሆኖም ኢህአዴግ አንዳንዶች እንደሚያስቡት የእንቧይ ካብ አይደለም። በግለሰቦች መኖርና አለመኖር ችግር የሚገጥመው ፓርቲ አይደለም። በግለሰቦች መልቀቅ ሳቢያ የሚፈረካከስ ድርጅት አይደለም።

ምንም እንኳን ግለሰቦች በፓርቲው ውስጥ የራሳቸው አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም ድርጅቱ ግን ጠንካራ መስመር ያለውና በህዝብ ድጋፍ የቆመ ስለሆነ የግለሰቦች መልቀቅ በፓርቲው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ይኖራል ብዬ አላስብም።

እንዲያውም ድርጅቱ በመተካካት መርህ የሚያምን በመሆኑ ከታች ጀምሮ ይዞት የመጣው ባህሪ አለው። ይኸውም ጠንካራ መስመር፣ ግልፅና ውጤታቸው በገሃድ የሚታዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ባለቤት እንዲሁም የህዝብ ፓርቲ በመሆኑ ህልውናው በግለሰቦች ላይ የተመሰረተ ሊሆን አይችልም።

እርግጥ ግለሰቦች በድርጅቱ ውስጥ የራሳቸው ሚና አላቸው። ግለሰቦቹን የፈጠራቸው ግን በህዝቡ ትግል የተፈጠረው ፓርቲ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። የግለሰቦች ሚና በአንድ ድርጅት ውስጥ ቢኖርም ኢህአዴግ ግን የህዝብ ድርጅት በመሆኑ ከግለሰቦች ጋር መቀያየር ጋር የሚዋዥቅ ፓርቲ አይደለም። የሚያጋጥሙትን ጉዳዩች ሁሉ እየፈታ ዛሬ የደረሰ ድርጅት ነው። ጥቂት ያለፉ ጉዳዩችን ከዚህ አኳያ መመልከት አንችላለን።

ኢህአዴግ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ጊዜያዊ ተግዳሮቶች እየፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ኢህአዴግ ከአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለመጣል ርብርብ ለማድረግ ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትነት ሀገሪቱም መምራት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ተግዳሮቶች ድርጅቱን የተፈታተኑት ቢሆኑም፤ ከህዝብና ከመላው አባላቱ ጋር በመሆን አያሌ ችግሮችን በብቃት መሻገር ችሏል።

በደርግ ውድቀት ማግስት ድርጅቱን ካጋጠመው ተግዳሮት ልነሳ። እንደሚታወቀው የአምባገነኑን ስርዓት መውደቅ ተከትሎ በ1983 ዓ.ም ከ17 የማያንሱ የታጠቁ የብሔር ቡድኖች ነበሩ። እነዚህ ቡድኖች የተለያዩ ዘውግ ያላቸው ናቸው።

የተወሰኑት ጠባቦችና ትምክህተኞች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ በፅንፈኛ አክራሪነት የተሰለፉ ነበሩ። በወቅቱ ደርግን ገርስሶ ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ እነዚህ ቡድኖች ለሀገራችን የጋራ መፍትሔ እንዲሹ ባቀረበላቸው ጥሪ መሰረት የሽግግር መንግስቱን ለመቀላለቀል ከያሉበት ቦታ ወደ አገራቸው መምጣታቸው ይታወሳል።

ለኢህአዴግ የእነዚህን የማይጣጣም ፍላጎት ያላቸውን ቡድኖች ፍላጎት ማቻቻል አንድ ተግዳሮት ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ የቡድኖቹን የተበታተነ ፍላጎት የተመለከቱ አንዳንድ ተንታኞች ‘ኢትዮጵያ ትበታተናለች’ የሚል ሟርትን ሲያቀርቡ ነበር። ይሁንና ኢህአዴግ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት የራሱን መንገዶች ተከትሏል። በተለይም ድርጅቱ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዓመታት የተሸጋገረው በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሰላምና ማረጋጋት ስራዎችን ወደ ማከናወኑ ነበር።

በዚህም በውድ የህዝብ ልጆች አኩሪ መስዕዋትነት የተገኘውን ድል ለመንጠቅ የሚሯሯጡ ፀረ ሰላም፣ ፀረ- ልማትና ፀረ-ዴሞክራሲ ኃይሎችን የማፅዳት ተግባሮችን ፈፅሟል። በወቅቱ ኢህአዴግና ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ለሀገራዊ ሰላም ሲሯሯጡ “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ አበው፤ ራሱን “ኦነግ” እያለ ይጠራ የነበረው የጠባቦች ቡድን ይህንን የተቀደሰ ዓላማ አልቀበልም በማለት የጦረኝነት አቅጣጫን በመምረጥ ማፈንገጡ የሚዘነጋ አይደለም።

ሆኖም ኢህአዴግ ከፍተኛ ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ ኦነግን ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጣ ከመለመን ባለፈ መስዋዕት እየሆነም ጭምር የሰላም እጁን ቢዘረጋም፤ ጠባቡ ቡድን ግን በእንቢተኝነቱ መፅናቱ የሚታወስ ነው። ኦነግ ለሰላም ሲታሰብ በየአካባቢው ሰው መግደልና ንብረት ማውደምን ስራዬ ብሎ ተያያዘው።

ኢህአዴግ ለዚህ ሰላማዊ ተግባሩ በወቅቱ የተሰጠው ምላሽ ጦረኝነት መሆኑን በመገንዘቡ፤ ከብዙ ትዕግስትና ልመና በኋላ ሁሉም የሰላም መንገዶች ተሟጥጠው ሲያበቁ የኦነግ ሠራዊት በመረጠው መንገድ ርምጃ ለመውሰድ ተገድዷል። ይህ ተግባሩም በህዝብ የተደገፈ በመሆኑ ኦነግ ያራምድ የነበረውን የእብሪት ጠብ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረግ ተችሏል።

ይህ የድርጅቱ ችግሮችን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደ አመጣጣቸው የመፍታት ጥንካሬ በደርግ ውድቀት ማግስት ‘ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው’ በማለት ሲያሟርቱ የነበሩ ተንታኝ ተብዬዎች ጥንቆላ መና እንዲቀር ያደረገ የሰላም መስመር ነው። እናም ኢህአዴግ ያኔ የተከተለው ትክክለኛ መስመር ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ ከብተናም እንድንድን ያደረገን ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህም በኋላ ቢሆን በልማትና በዴሞክራሲ መንገዶች 10 ዓመታትን ከተሸጋገረ በኋላ፤ ድርጅቱ ሌላ አደጋ ገጠመው—በ1993 ዓ.ም። ይህ ወቅት ህወሓት ለሁለት የተከፈለበትና ኢህአዴግም እንደ ድርጅት የውስጠ-ድርጅት ትግሉ የጠነከረበት ጊዜ ነበር። ክፍፍሉ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችንም ጭምር የነካካ በመሆኑ ድርጅቱ ሁለንተናዊ አቋሙን የፈተሸበት ነበር። በዚህም የኪራይ ሰብሳቢዎች ጎራ የሆኑ የድርጅቱ አባላት ተንጓለው ወጥተዋል—በህዝቡ እውቅና። ወቅቱን እዚህ ላይ በመጠኑ ላስታውስ።

በወቅቱ “አንጃው” ተብሎ የተሰየመው የጥገኝነት አቀንቃኝ ቡድን በማዕከላዊ ኮሚቴ 13 ለ15 በሆነ ድምፅ ሲሸነፍ ዴሞክራሲዊ መንገድን በመርገጥ አሻፈረኝ ብሎ ውይይቱን አቋርጦ ወጣ።  ተሰብሳቢው “በሰማዕታት አጥንትና ስጋ ይዘናችኋል እባካችሁ ተቀመጡና ተወያዩ” ቢባሉም፤ እምቢኝ፣ አሻፈረኝ በማለት ውይይቱን ረግጠው ወጡ። የድርጅቱን ህገ-ደንብም በግላጭ ጣሱ።

ሆኖም ውይይቱ “አንጃውን” አግዶ ባሉት አባላት እንዲቀጥል ተደረገ። የ“አንጃው” አንዳንድ አባላት በወቅቱ በኦህዴድና በደህዴን ውስጥ የነበራቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በሁለቱ ድርጅቶች ውስጥ ያልተገባ አካሄድን ለመከተል ሞከሩ። የ“አንጃው” አባላት ደቡብና ኦሮሚያ በእኛ ስር ስለሆኑ ምን ያመጣሉ ሲሉም ታበዩ።

እንዲያውም የ“አንጃው” የዝቅጠት አስተሳሰብ በብአዴን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በመመታቱ ሳቢያ ጥቂት አምሳያዎቹን በመያዝ በፓርላማ ውስጥ የራሱን መንግስት ለመመስረት ተሯሯጠ። ዳሩ ግን አብዛኛው ተወያይ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን በመደገፉ ምክንያት ይህ የ“አንጃው” ቀቢፀ-ተስፋ እንደ ጉም በንኖ ጠፋ። ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩ የበላይነትን በመያዙም ድርጅቱም ከብተና፣ ሀገራችንም የህዳሴዋን ጉዞ የምታሳልጥበት መንገድ ታያያዘችው። እነዚህ ማሳያዎች ኢህአዴግ የሰዎች መልቀቅም ቢኖር እንዴት ችግሩን ከህዝብ ጋር በመሆን እንደሚያልፍ ማረጋገጫዎች ናቸው።

 

  1. Mulugeta Andargie says

    ማንም ሞኝ የለም፣ ስልጣኑን የሚለቅ። ቆይ፣ ለቀቀ እንበል፣ ለናንተ እንዲተውላችሁ ነው?? የበፊቱ ይበቃናል!!! ይህቺ እስክስታ ለመሳሳም እንዳይሆን እለች አሉ ድንቢጥ እይጥን። ቀሺሞች!! በየ ጠላው ቤት ካወራችሁ ይበቃል!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy