Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢሬቻ ጥቅመኞች እንዳሰቡት ሳይሆን ህዝብ እንዳሰበው በሠላም ተከብሯል

0 628

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢሬቻ ጥቅመኞች እንዳሰቡት ሳይሆን ህዝብ እንዳሰበው በሠላም ተከብሯል

ብ. ነጋሽ

የ2010 የኢሬቻ በዓል በሰላም ተከብሯል። ከአባገዳዎቹ እንደሰማነው በሚሊየን  የሚቆጠሩ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢ የመጡ የኦሮሞ ተወላጆችና የሌሎች ብሄሮች በተሳተፉበት ሥርአት ነው ኢሬቻ የተከበረው። የኢሬቻ በዓል በድምቀትና በሰላም፣ ባህልና ወጉን በሚያንጸባርቅ አኳኋን መከበሩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አስደስቷል። ትላንት ከቀትር ጀምሮ በአዲስ አበባ የነበረውን የህዝብ ስሜት መመልከት ለዚህ በቂ አሰረጂ ነው። እናቶች የበአሉን በሰላም መከበር ሲሰሙ እሰይ ብለው ስሜታቸውን ገልጸዋል፤ በየቤቱ።

የኢሬቻ በአል የምስጋና በአል ነው። ከብቶች እንኳን እንደልብ እንዳይንቀሳቀሱ አግዶ ይዞ የነበረው የጨለማው ክረምት ጭቃ፣ ወዳጅ አለያይቶ የከረመ የወንዝ ሙላት፣ ዝናብና ብርድ ተሰናብቶ የጸደይ ብርሃን በመፈንጠቁ ነው አምላካቸውን የሚያመሰግኑት፤ baga duukkana gannarraa gara booqa birraa ceetani (እንኳን ከክረምት ጨለማ ወደጸደይ ብርሃን ተሻገራችሁ) እየተባባሉ። ኦሮሞዎች ኢሬቻ ላይ፣ ክረምት ዘንቦ ምድር አዝርዕት አብቅላ በመኸር ተስፋ እንዲሞሉ፣ መስክ ሳር አብቅሎ እንስሳት ጠገበው ወተትና ቂቤ እንዲሰጡ፣ እንዲሰቡ፣ . . . ላደረገ አምላክ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። ከርሞም እንዲሁ እርጥብ ዓመት እንዲሆንላቸው በምርቃት ይማለዳሉ፤ ይመኛሉ።

ስለኢሬቻ ካነሳን ላይቀር አንድ ነገር ልጨምርልችሁ። ኤሬቻ በዓመት ሁለቴ ነው የሚከበረው። አንደኛው ሰሞኑን በመከበር ላይ የሚገኘው በውሃ ዳር የሚከበረው የምስጋና ኢሬቻ ነው። ይሄ፣ የውሃ ዳር ወይም የምስጋና (Irreecha malkaa/ Irreecha galata)  ኢሬቻ ይባላል። ሁለተኛው በልግ ከመግባቱ በፊት የሚከበረው የምልጃ ኢሬቻ ነው። ይህኛው ውሃ ዳር ሳይሆን ጋራ ወይም ኮረብታ ሥር ነው የሚከበረው። የጋራ ወይም ምልጃ ኤሬቻ (Irreecha gaara/Irreecha kadhaa) ይባላል። ሁለተኛው ኤሬቻ አምላክ መጪውን በልግና ክረምት እንዲያዘንብ፣ ምድር አዝርዕት እንድታፈራ፣ መስክ ሳር እንዲያበቅል፣ ከበቶች እነዲፋፉ፣ የሚጣፍጥ ወተትና ስጋ እንዲሰጡ ምልጃ ማቅረቢያ ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ የዘንድሮውን የውሃ ዳር ኢሬቻ በሰላም አክብረናል። ኢሬቻ ለኦሮሞዎች አዲስ አይደለም። ለሺህ ዓመታት አምላካቸውን ሲያመሰግኑና ሲማለዱ የኑሩበት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርአት ነው። ይሁን እንጂ ኢሬቻ በተለይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ጀምሮ የተዛባ ምንነት ተለጥፎበት፣ ልከ እንደሌሎቹ የኦሮሞ የማንነት መገለጫዎች እየደበዘዘ የአጥቢያ ክንውን በሆነበት ደረጃ እንዲዋረድ ተደርጎ ነበር። ይህ የኤሬቻን ምንነት ለሚያውቁ ሁሉ የሚያሳዝን አጋጣሚ ነበር።

ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ህገመንግስታዊ ዕውቅና ሲያገኝ፣ ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ ባህላቸውን የማጎልበትና የማስተዋወቅ፣ ታሪካቸውን የመንከባከበ . . . መብታቸው ሲረጋገጥ፣ ኢሬቻ እንደቀደሞው ትክክለኛ ገጽታውን ይዞ በይፋ ይከበር ጀምሯል። ኢሬቻ ዳግም ተወለደ። ኦሮሞዎች ሳይሸማቀቁ በይፋ ኢሬቻን ማክበር ጀመሩ። የሌሎች ብሄሮች አባላትም ኢሬቻን እንደ አንድ ድንቅ የህዝብ ባህል ዋጋ ሰጥተውት ሁነቱ ላይ መሳተፍ ጀመሩ። ኢትዮጵያውያን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊትና አሁን ስለኢሬቻ ምንነት ያላቸው ግንዛቤ እጅግ የተለያየ ነው። ድሮ ኢሬቻ ክፉ አምልኮ ተደረጎ የሚወሰድበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ግን ኢሬቻ መልካም ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት ነው። በዚህ ሁሉም ኦሮሞ ረክቷል። ኢሬቻን በመሸማቀቅ ሳይሆን በጉጉትና ተስፋ መጠበቅ ጀምሯል።

የባለፈው ዓመት ኢሬቻ ግን መሰናክል ገጥሞታል። የኢሬቻን በዓል ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርአቱ ከሚያዘው ውጭ ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ እንደመልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የሞከሩ ቡድኖች ነበሩ ኢሬቻን ያሰናከሉት። በበዓሉ መሃል ለማክበር የታደሙትን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችና ሥርአቱን የሚመሩትን በኦሮሞ ባህል የሚከበሩትን አባገዳዎች፣ አባመልካዎችና ቃሉዎች በመናቅ የኦነግን፣ የኦፌኮን ወዘተ አርማ የያዙ ሰዎች እጅብ ባለው ታዳሚ መሃል እየተራወጡ ትርምስ ፈጥረው ነበር። በዚህ አልተገደቡም፤ አባገዳዎቹና አባ መልካዎቹ ያሉበት መድረክ ላይ በመውጣት ማይክራፎን በመቀማት የሁከት ቅስቀሳ አካሂደዋል። በዚህ ሁኔታ የምስጋናው በዓል ወደፖለቲካ ሁነትነት ተቀየረ። የመጀመሪያው ጥፋት ይህ ነበር።

ኢሬቻን መናቅ ኦሮሞዎችን መናቅ ነው። አባ ገዳዎችንና አባመለካዎችን መናቅ ኦሮሞዎችን መናቅ ነው። እናም ሁከቱን ያሴሩትና የቀሰቀሱት ቡድኖችና ግለሰቦች የራሳቸውን የፖለቲካ ዓላማ ከማሳካት ውጭ ለኦሮሞ ህዝብ ግድ የሌላቸው መሆናቸውን አሳይተዋል።

እንግዲህ ሁላችንም እንደምናስታውሰው፣ ከምስጋና በዓልነት በድንገት ወደፖለቲካ ሁነትነት የተቀየረው የአምናው ኢሬቻ ታዳሚውን ግራ አጋባው፤ አስደነገጠው። ታዳሚው በድንገት ዓላማውን ከሳተው የበዓል ስፍራ ለመውጣት ባገኘው አቅጣጫ በሙሉ መንቀሳቀስ ይጀምራል። ይህ ሁኔታ ከስፍራው አመቺ አለመሆን ጋር ተዳምሮ ሰዎች ወድቀው እንዲረጋገጡ አድርጓል። በተለይ በስፍራው አንድ አቅጣጫ ተገፍተው ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ የተደረጉ ሰዎች ገደል ውስጥ ወድቀው እርስ በርስ ተረጋገጡ፣ አፈር ተደረመሰባቸው። በዚህ በርካቶች የአካል ጉዳት ደረሰባቸው፣ 52 ሰዎች ሞቱ።

ይህ እጅግ አሳዛኝ ነበር። ይሁን እንጂ ትርምሱን ለጠነሰሱትና ላካሄዱት ሰዎች ድል ነበር። ከሟቾቹ መሃከል አንድም በጥይት ተመቶ የሞተ ወይም የቆሰለ ባይኖርም፣ ሰዎች የሞቱት በጥይት ተመተተው መሆኑን ነገሩን፤ የሁከቱ ጠንሳሾች። አንዳንድ ታዋቂ የሚባሉ የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ጭምር የሟቾቹን ቁጥር በአስር እጥፍ እያባዙ ለሁከት አጋፋሪ ሚዲያዎች የገለጹበት ሁኔታ እንደነበረ ይታወሳል። የማቾቹን ቁጥር 6 መቶ ያደረሱም ነበሩ።

ይህን ያደረጉት የመንግስትን ገጽታ በማበላሸት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው። በንጹሃን ደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ አሳዛኝና ዘግናኝ አካሄድ ነው። በሁከቱ ሰዎች መጎዳታቸውን ተከትሎ በሻአቢያ የሚመሩና ሌሎች የሁከት አጋፋሪ ሚዲያዎች በስፍራው የነበረውን ሁኔታ በፍጹም የማይገልጹ ዘገባዎችን አሰራጩ። የሚገርመው በአምናው ኢሬቻ ላይ የተዛባ ዘገባ የማቅረቡ ተግባር አሁንም አልተቋረጠም። ያገኟትን ሲሳይ አሁንም ነክሰው እንደያዙ ናቸው።

የዘንድሮው ኢሬቻም ላይ ሁከት በመቀስቀስ ሰዎች እንዲሞቱ በማደረግ በንጹሃን ኦሮሞዎች ደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያለሙ ቡድኖችና ቅጥረኞቻቸው ነበሩ። ከኢሬቻ በዓል ቀደም ብሎ ሀዝብ ባደረገው ጥቆማ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተቀጣጣይ ቁሳቁሶች፣ የስለት መሳሪያዎች ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ይህ ብቻ አይደለም። በተለይ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማበላሸት ሳይሰለች በመስራት የሚታወቀው ሂዩማን ራይትስ ዎች ነሃሴ መገቢያ ላይ ኢሬቻን መነሻ በማድረግ ተቆርቋሪ መስሎ በሃሰተኛ መረጃ ብሶት በመቀስቀስ የሁከት ስነልቦናዊ ሁኔታ ለመፈጠር ሞክሯል። የሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ፣ መንግስትና የጸጥታ ሃላፊዎች በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ ራሳቸውን እንዲቆጣጠሩና የሞትና የአካል ጉዳት አደጋ እንዳያጋጥም እንዲያደርጉ ያሳስባል። ይህን ያደረገው እውነት ሊሞቱና ሊጎዱ ለሚችሉ ሰዎች በማሰብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ባለፈው ዓመት ለሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ሁኔታ በመንግስት የተፈጠረ ነው የሚል መልዕክት እያስተላለፈ ነው።

ሂዩማን ራይትስ ዎች 50 ያህል ሰዎችን አነጋግሮ፣ የባለፈው ዓመት የኢሬቻ በአል ላይ የተቀረጹ በርካታ ፊልሞችን ተመልክቶ በጸጥታ ሃይል በተተኮሰ ጥይት የሞተ ሰው መኖሩን የሚያሳይ አንድም ማሰረጃ አላገኘም። ይህን በይፋ ተናግሯል። የሁን እንጂ ያነጋገራቸው ሰዎች፣ ሰዎች የሞቱበት ሁኔታ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ጭፍጨፋ ነው ማለታቸውን ገልጿል። ፖሊሶች ጥይት ወደሰው በመተኮሳቸው በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ ሰዎች እንዲሞቱ መደረጉንም ይጠቅሳል።

በመሰረቱ በበዓሉ ላይ የተተኮሰ ጥይት አልነበረም። በጥይት ተመትቶ የሞተም ሰው አልነበረም። የሞቱት ሰዎቸ አስከሬን በሙሉ ሆስፒታል ተወስዶ የሞቱበት ምክንያት ተረጋግጧል። አስከሬኖቹን የመረመሩት ሃኪሞች ይህን በወቅቱ በይፋ በሚዲያ ተናግረዋል። ይህ እውነት በሆስፒታሉ ሪከርዶችም ላይ ሰፍሯል። ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህን ተጨባጭ ማስረጃ መጥቀስ አልፈለገም። ይህ ሁኔታ ሂዩማን ራይትስ ዎች ኢሬቻ አንድ ወር ሲቀረው መግለጫ ያወጣው ከተቆርቋሪነት ሳይሆን ሁከት ቀስቃሽ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ለማመቻቸት መሆኑን ያመለክታል። ሂዩማን ራይትስ ዎች የሟቾቹ ቁጥር ከመቶ በላይ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ቢናገርም፣ ባለፈው ዓመት መንግስት ከገለጻቸው 52 ሟቾች ውጭ የአንድ ተጨማሪ ሟች ስም እንኳን መጥቀስ አልቻለም።

ሁከት በማጋፈር የሚታወቀው የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራምም (ቪኦኤ) ይህን የሂዩማን ራይትስ ዎች መሰረተ ቢስ መግለጫ ሊያራግበው ሞክሯል። ቪኦኤ ኢሬቻ ሊከበር አንድ ቀን ሲቀረው አምና የአንድ ሟች ቀብር ላይ የተቀረጸን የኦሮሚኛ ለቅሶ እንጉርጉሮ፣  ወደአማርኛ ተርጉሞ ልክ ድራማ ላይ እንደሚደረገው በጋዜጠኛ የተንጎራጎረበት ፕሮግራም አቅርቧል። ጋዜጠኛ ዘገባ በድራማ መልክ ሲያቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው በዚህ ፕሮግራም ላይ ይመስለኛል። ይህ እንደ ድራማ የቀረበ የቪኦኤ ዘገባ ዓላማ፣ እውነተኛ መረጃን ለህዝብ ማቅረብ አይደለም። ከመንግስት በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ከመቆርቆር የመነጨም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሁከት እንዲቀሰቀስ በማድረግ የመንግስትን ገጽታ በማበላሸት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚያስችሉ ተጨማሪ ሟቾችን ማግኘት ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ የዘንድሮው ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ምንም የማያሳስባቸው፣ ለባህልና ወጉ ምንም አክብሮት የሌላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች እንደተመኙትና እንደሞከሩት ሳይታወክ፣ በሰው ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ተከብሯል። በኦሮሞ ህዝብ ደም የፖለቲካ ትርፍና የገንዘብ ጥቅም ለመሰብሰብ ያለሙ ሰዎች እንዳሰቡት ሳይሆን፣ ህዝብ እንዳሰበው በሰላም ተከብሯል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy