HEALTH

ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውሰጥ የሚገኝ መድሃኒቱን እንዲጠቀሙ ለማድረግ የቤት ለቤት ቅስቀሳ በይፋ ተጀመረ

By Eden TG

October 03, 2017

ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውሰጥ የሚገኝ ዜጎች በአፋጣኝ የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት እንዲጠቀሙ ለማድረግ የቤት ለቤት ቅስቀሳና ጥናት በይፋ ተጀመረ።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት የማህበረሰብ አቀፍ የኤች አይ ቪ ተፅእኖ – በኢትዮጵያ የተሰኘ ዐውደ ጥናት ተከፍቷል።

ጥናቱ ተጨማሪ ስልጠና በተሰጣቸው የህክምና ባለሙያዎች የሚከናወን ሲሆን፤ የህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከአካባቢው የጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹም ተገልጿል።

በቤት ለቤት ቅስቀሳ በሚካሄድበት ወቅት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።

የዚህ ዓይነቱ ክትትል አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎችን ቁጥር ለመለየት እንደሚረዳ ተመልክቷል። ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ተከትሎ የሚመጡ እንደ ጉበትና የአባላዘር በሽታዎች ላይ ምርመራም ይደረጋል።

ከሁሉም አካባቢዎች 25 ሺ ዜጎችን የሚያሳትፈው ይህ ጥናት አገሪቷ የኤች አይ ቪ /ኤድስን በመግታት ረገድ ያለችበትን ደረጃ በጉልህ እንደሚያሳይ በዐውደ ጥናቱ ላይ ተገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒቱን በአግባቡ ተከታትለው መውሰድ ይኖርባቸዋል።

መድሃኒቱን በተገቢው መንገድ ተከታትለው መውሰዳቸው ጤናቸውን ከማስተካከሉም በላይ ወደ ሌሎች ሰዎች የማስተላለፍ አቅማቸውን ስለሚቀንስ በአግባቡ መወሰድ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ከዚህ በፊት ሲጠቀሱ የነበሩት “መታቀብ ” መወሰንና መጠቀም” የሚሉት የበሽታው መከላከያ ህጎች በተጨማሪ መመርመርና መታከም የሚሉ ህጎች መካተታቸውን አውስተዋል።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አቀፍ ኤች አይ ቪ ተፅዕኖ ጥናት ፕሮጀክት ኃላፊ ዶክተር ዴቪድ ሁዝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ቫይረሱ በደሙ ከሚገኝባቸው ሰዎች መካከል 60 በመቶ የመድሃኒት ተጠቃሚ ማድረጓን አድንቀዋል።

ኢትዮጵን ጨምሮ  በማህበረሰብ አቀፍ ኤች አይ ቪ ተጽዕኖ ላይ ጥናት ለሚያደርጉ 14 አገሮች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን የሰባት አገሮች መረጃ መሰብሰቡን ተናግረዋል።