Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውነቱ ይነገረን

0 351

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውነቱ ይነገረን

ኢብሳ ነመራ

ለዘመናት በጉርብትና የኖሩት የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ግንኙንት ድንገት ያለአመሉ ካልሻከርኩ እያለ ነው። በስተደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ጉጂና ቦረና ዞኖች፣ በስተምስራቅ ምዕራብና ምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች በሺህ ኪሎሜትሮች የሚለካ ወሰን ላይ የሚኖሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ከኢትዮጵያ ሶማሌዎች ጋር ድንበር ይጋራሉ። ሁለቱ ህዝቦች ድንበር ብቻ አይደለም የሚጋሩት፤ ባህልም ተጋርተዋል፣ ተዋልደው በደም ተዋህደዋል። አብኞቹ በተዋሳኝ ድንበር ላይ የሚገኙ ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች አንዱ የሌላውን ቋንቋ አቀላጥፈው ይናገራሉ። አርብቶ አደርነትንም ይጋራሉ። ባለፉት ሥርአቶች ሲደርስባቸው የነበረውን ተመሳሳይ የብሄራዊ ጭቆና ታሪክም ይጋራሉ።

ሁለቱ ተዋሳኝ ብሄሮች በአመዛኙ አርብቶ አደር በመሆናቸው አልፎ አልፎ በግጦሽ ሳርና በውሃ ሽሚያ ግጭት ውስጥ የሚገቡባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸው ባይካድም፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው ባህላዊ የሽምግልናና የእርቅ ሥርአት እየፈቱ አብሮነታቸውንና ሰላማቸውን አጽነተው መዝለቅ ችለዋል። አሁን ይህ የዘመናት አብሮነት ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ፈተና እንደገጠመው እየሰማን ነው።

እነዚህ የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወሳኛ ህዝቦች አንዱ ሌላው ላይ ተነስቶ ሜንጫ መሰንዘሩን፣ ክላሽንኮቭ መተኮሱን የሚረጋግጥ ተጨባጭ አስረጂ ባይኖርም በሁለቱ ብሄሮች መሃከል ግጭት ተቀስቅሷል እየተባለ ነው። ከድንበር ማዶ የሚኖሩት የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄር ተወላጆች ተኩሰው ገደሉን የሚሉ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች አላጋጠሙኝም። ይሁን እንጂ በሁለቱም በኩል የሞቱና የተፈናቀሉ አሉ፤ በታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ህይወታቸውን ያጡ፣ ተሳድደው መኖሪያቸውን ለቀው የተፈናቀሉ ሰዎች። ነገሩ ግራ አጋቢ ነው።

አሁን በሁለቱ ክልሎች ውስጥና መሃከል ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስና የሰላም መደፍረሱ ላስከተለው የመፈናቀል ቀውስ መፍትሄ ለማበጀት በፌደራል መንግስት ደረጃ አንድ ኮሚቴ ተደራጅቷል፤ በፌደራል ጉዳዮችና በአርብቶ አደር አካባቢዎች ልማት ሚኒስቴር የሚመራ ኮሚቴ።  ይህ ኮሚቴ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት፣ የጸጥታ አካላትና የኢኮኖሚ ልማት መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት ነው።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መቀስቀሱን፣ በዚህም ከአዋሳኝ አካባቢዎች ውጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ላይ ጭምር ጥቃት መሰንዘሩንና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉን ተከትሎ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መግለጫቸው፣ ግጭት የተቀሰቀሰባቸውን የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች የሰላም ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ ዋና ዋና መንገዶች በመከላከያና በፌደራል ፖሊስ ሃይል ጥበቃ ሥር እንዲሆኑ፣ እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ሃይሉ የሰው ሕይወት በማጥፋትና አካላዊ ጉዳት በማደረስ የሚጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ መተላለፉን አስታውቀዋል። በሁለቱ ክልሎች መካከል የሰብዓዊ መብት በመጣስ የሰው ሕይወት ያጠፉ የፀጥታ ኃይል አባላትም ይሁኑ ሌሎች አካላት ህግ በሚያዘው መሰረት እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መበት ጥሰትን እንደሚያጣራም አስታውቀዋል።

የአካቢውን ሰላም የማሰከበር ሃላፊነት የተጣለበት የደቡብ ምስራቅ እዝ ሰሞኑን እንዳስታወቀው አሁን ግጭት ተቀስቅሶ በነበረባቸው የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላም ሰፍኗል። በግጭቱ ውስጥ መሳተፋቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራም እየተከናወነ ነው።

ከወሰን ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በዜጎች ላይ የተፈፀሙና የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ለመፈተሽ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አጣሪ ቡድን መላኩም ታውቋል። የሰብአዊ መብት ሁኔታ አጣሪ ቡድኑ ምርመራውን አጠናቆ እንዳበቃ የችግሩን ስፋትና ምክንያት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል።

በሌላ በኩል ለተፈናቃዮች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየተደረገ ነው። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከ50 ሺህ በላይ ለሆኑት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች የእርዳታና መልሶ ማቋቋሚያ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጥሯል። ይህ ህዝቡ ወገኖቹን ለመርዳት ከዳር እስከዳር ያሳየው መነቃቃት በስነልቦና ተጎድተው የነበሩትን ተፈናቃዮች ተስፋ አለምልሟል።

እንግዲህ፣ በሁለቱ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት መንስኤ ወሰን እንደሆነ ነው የሚነገረው። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ግጭቱ አዋሳኝ አካባቢ በሚኖሩ የሁለቱ ብሄሮች መሃከል የተፈጠረ አለመሆኑ፣ በሌላ በኩል ጥቃቱ በአካባቢው ነዋሪነት በማይታወቁ በተደራጁ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ በታጠቁ፣ በሰለጠኑ ሰዎች የተፈጸመ መሆኑ የግጭቱ መንስኤ የወሰን አለመገባባት የመሆኑን ነገር ጥያቄ ላይ ይጥለዋል። በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት ከወሰን ጋር በተያያዘ መጠነኛ ግጭቶች ተቀስቅሰው ጉዳዩ በህዝበ ወሳኔ እልባት ተበጅቶለት እንደነበረ ይታወሳል። ይህ በህዝበ ውሳኔ የተረጋገጠው ወሰን በመሬት ላይ ሳይካለል መቅረቱ እንደመንግስት ችግር የሚወደሰድ ቢሆንም፣ አለመካለሉ በራሱ በዚህ ደረጃ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል ተብሎ አይገመትም።

ወሰን መሬት ላይ አለመካለሉ ትናንሽ መንደሮችና ጎጆዎች ወደየትኛው ክልል እንደሆኑ መለየት ያስቸግር እንደሆን እንጂ ቀበሌዎች ወደየትኛው ክልል እንደሚገኙ ጥያቄ አያስነሳም። በመሆኑም ግጭቱ በምንም አግባብ ወሰንን መነሻ ያደረገ የህዝቦች ግጭት ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። እናም ግጭቱ ለምን ዓላማ በማን እንደተቀሰቀሰ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ መደረግ አለበት። በዚህ ላይ የሚደረግ ማድበስበስ ግጭቱን በማዳፈን ወቅት እየጠበቀ እንዲያያዝ ከማድረግ ያለፈ የሚያስገኘው ጥቅም እንደሌለ መታወቅ አለበት። እውነተኛው የችግሩ ምንጭና ፈጻሚ ካልታወቀ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የሚደረገው እንቅስቃሴ የይስሙላ ነው የሚሆነው። ወይም ግቡን ሳይመታ የሚቀጭ የአንድ ሰሞን ወሬ ከመሆን አይዘልም።

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አለማበጀት በሁለቱ ህዝቦች መሃከል የተፈጠረውን በጥርጣሬ ወደመተያያት እያመራ ያለ መደናገር ያባብሰዋል። ይህ ደግሞ በችግሩ ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን አሁን እንደሚወራው ወደነበሩበት የመመለሱን ተግባር የማይቻል ያደርገዋል። የተፈናቀሉትን ሰዎች ወደነበሩበት መመለስ ዳግም ተመሳሳይ ችግር እንደማይፈጠር ዋስትና ማረጋገጥን ይሻል። አሁን የምንመለከተው በሁለቱ ህዝቦች መሃከል የሚታይ አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ የመመልከት አዝማሚያ ካልተወገደ አንዱ ህዝብ በሌላው ክልል በሰላም የመኖር ዋስትና ሊያገኝ አይችልም። እናም እውነቱ ፍርጥ ብሎ መውጣት አለበት። እውነቱ የሚመር እንኳን ቢሆን፣ የሚመር መድሃኒት ያድናል እንዲሉ፣ በማንኛውም ጊዜ የሚያመረቅዝ በሽታ ይዞ ከመኖር መራራውን እውነት ተጎንጭቶ መዳን ነው የሚሻለው። እውነቱ እስካልወጣ ደረስ መሬት ላይ ወሰን ማካለል በራሱ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣም መታወቅ አለበት።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት በአጠቃላይ የሃገሪቱን ፖለቲካ ወደአለመረጋጋት ውስጥ ሊከት እንደሚችልም መታሰብ አለበት። ሰሞኑን እንደምንመለከተው የአሃዳዊ ሥርአት ተስፈኞች ከተቀበሩበት አፈራቸውን እያራገፉ እየተነሱ ነው። እትግጥ ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ ወደአሃዳዊ ሥርአት ልትመለስ አትችልም። አሃዳዊ ሥርአትን የመመለስ ጉዳይ ከህልም የተለየ አይደለም። ካሁን በኋላ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ዕውቅና የነፈገ ማንኛውንም አይነት የመንግስት ሥርአት መመስረት የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታም የለም። በመሆኑም የአሃዳዊ ስርአት ተስፈኞች ህይወት የመዝራት አቅም ባይኖራቸውም፣ የብሄሮች ግጭት ገጽታ ያላቸው ሁኔታዎች እስካሉ ደረስ በተለይ በከተሞች አካባቢ ውዥንብር መፍጠር የሚያስችላቸው እድል ሊያገኙ መቻላቸው እውነት ነው። ይህ ደግሞ ለሁከትና ግርግር በር ይከፍታል። ሙታኑ የአሃዳዊ ፅርአት ተስፈኞች ወደመቃብራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ችግሩ ከፌደራላዊ ስርአቱ ያልመነጨ መሆኑን በግልጽ በሚያሳይ ሁኔታ በችግሩ ዙሪያ ያለው እውነት ፈርጦ መውጣት አለበት።

በሌላ በኩል ግጭቱ የተመራው የፌደራል መንግስት ነው የሚሉ በህዝብ ዘንድ የመደመጥ እድል እያገኙ የመጡ ድምጾች መኖራቸውን ማስተዋልም ተገቢ ነው። የፌደራል መንግስቱ የኦሮሞን ህዝብ ለማጥቃት፤ ኢህአዴግ ውስጥ እየጎለበተ አልታዘዝ እያለ መጣ ያሉትን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ለማዳከም ያደረገው ነው፤ ጥቃቱን የፈጸመው ሃይል በፌደራል መንግስት ብቻ የሚታዘዝ አካል ነው የሚለው ወሬ ተሰሚነት እያገኘ መምጣቱን ማስተዋል ብልህነት ነው። ይህ ውዥንብር እውነቱ ካልወጣ በስተቀር ጉልበት የማግኘት እድል ይኖረዋል። እናም እውነቱ ሳይሸሸግና ሳይድበሰበስ መውጣት አለበት።በአጠቃላይ፤ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሃከል የተፈጠረው ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል። ዘላቂ መፍትሄ የማበጀቱ ጉዳይ ግን የችግሩ ምንጭና ግጭቱን የመሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ማንነት ምንም ሳይድበሰበስና ሚዛናዊ ለመሆን በሚል ስሌት ተቀንሶና ተጨመሮ ሳይደበዝዝ ይፋ እንዲወጣ ይሻል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy