Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት

ስሜነህ

 

የግሉ ዘርፍ የኦኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሃገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈሩ ተደርጓል፡፡ በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ የመወዳደር አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች በመደረጋቸው በርካታ አስመጪዎችና ላኪዎች ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ሀብት እንዲያፈሩ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ ለልማቱ የሚያስፈልገውን ሀብት በማመንጨት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማበርከት አስችሏል፡፡  

የንግድ አሠራሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሸቀጦችና የጉልበት ነፃ ዝውውር እንዲኖርና የሸቀጦች ዋጋ በአቅርቦትና ፍላጎት ህግጋት መሠረት በውድድር እንዲመራ በመደረጉና የመንግስት ሚናም ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ዘርፎች ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን በማድረግ በርካታ ለውጦች እንዲመጡ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል የገበያ ጉደለት በሚያጋጥምበት ወቅት በተመረጠ አግባብ እና ለተወሰኑ ጊዜያት በመግባት ጉድለቶችን የመሙላት ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የኑሮ ውድነቱ በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ መሰረታዊ ሸቀጦችን በድጎማ ለህብረተሰቡ በማቅረብና በማሰራጨት እንዲሁም በጅምላ ንግድ ስርአቱ ውስጥ የሚታየውን የገበያ ክፍተት ለመሸፈን የኢትዮጵያ የንግድ ድርጅት ወይም አለ በጅምላን በማቋቋም ዋጋን በማረጋገት ረገድ ክፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

የንግድ ግንኙትንና ድርድርን በማጠናከር ገበያ በማፈላለግ የውጭ ባለሀብቶች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት፤ የሥራ ማስኬጃ ችግርን ለማቃለል የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፤ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ፤ የቫውቸር ሥርዓት የመዘርጋት፣ የማይቀረጥ የዕቃ ማከማቻ መጋዘንና የተመላሽ ቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓቶች መተግበር፤ የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል እቃዎችና ግብአቶች ያለቅድመ ሁኔታ የሚገቡበትን መንገድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መሬት  የሚያገኙበትን ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ ተሰርቷል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም የወጪ ንግድ ዘርፉ ወጥ በሆነ አቋም ላይ የማይገኝ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በማሽቆልቆል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ስለሆነም እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት ሲባል የኢትዮጵያ ብር ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች በ15 በመቶ ቀንሶ ግብይት እንዲፈጸምበትና ባንኮች ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ወደ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከረቡዕ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ በአሁኑ ወቅት በባንኮች በ23.88 ብር የሚመነዘረውን ዶላር ወደ 26.96 ብር ከፍ እንዲል ማድረጉም ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱን የምንዛሪ ለውጥ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ   ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የአገሪቱ ምርቶች በዓለም ገበያ ዋጋቸው እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የግድ የወጪ ንግዱን ማሳደግ ስለሚገባ ዕርምጃው መወሰዱን አመልክቷል፡፡የግብርና ምርት የወጪ ንግድን ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ይህ ዕርምጃ ተገቢ በመሆኑ የተወሰደ እንደሆነም በተመሳሳይ፡፡  

የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግና ኤክስፖርተሮችን ለማበረታታት የምንዛሪ ለውጡ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድ ለማዳበርም እንደሚረዳም እየገለጹ ነው፡፡

የመስከረም 2003 ዓ.ም. የብር ምንዛሪ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በተከታታይ ለተገኙት የወጪ ንግድ ገቢ እመርታዎች መነሻ እንደነበር የሚታወስ መሆኑን፣ በጥቅሉ የብር የምንዛሪ ዋጋ መቀነስ የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ ምርቶች ርካሽ በማድረግ የወጪ ንግድ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላውም ዓለም ቢሆን የምንዛሪ ለውጡ ዕርምጃ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በመጨመር ረገድ ተመራጭ እንደሆነም በማስታወስ፡፡ ያም ሆኖ ግን እንዲህ ዓይነት የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ለወጪ ንግዱ ሊሰጥ ከሚችለው ጠቀሜታ ባሻገር አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም እነዚሁ ጠበብቶች ይመሰክራሉ ። ይህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያስከትል መሆኑ ነው፡፡  በእርግጥም እርምጃው ከተወሰደ በኋላ ቢያንስ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪው ሊከሰት የሚችለው ከሁለት ወራት በኋላ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም አስቀድመው በነበረው ዋጋ በገቡት የውጭ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሬው ወዲያውኑ ተከስቷል።በዚህ ሳያበቃ ደግሞ የሃገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ይጠቅማል የተባለው ክለሳ ተቀልብሶ በሃገር ውስጥ ምርቶች ላይ ይልቁንም ከዋጋ ጭማሬው ጋር ምንም ተያያዥነት በሌላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ጭማሬው ታይቷል።መንግስት ሰው ሰራሽ የሆነ የኑሮ ውድነት በሚፈጥሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም አንዳንዶቹ የመንግስት ድርጅቶች መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ ግራ ገብ ያደርገዋል። አንድ ምሳሌ እናንሳ። የመንግስት በሆኑ ስኳር ድርጅቶች ተመርቶ የሚወጣ ስኳር እስከ 80 ብር፤ ከውጭ ምንዛሬ ጋር ምንም ዝምድና በሌለው የቄራዎች ድርጅት የእርድ አገልግሎት ላይ ክፍያውን በማናር ስጋን ማስወደድ፤ ወዘተ ሊታዩና ለፈተሹ ከሚገባቸው የምንዛሬ ለውጡን ዓላማ ከሚያስቱ ማሳያዎች መካከል ለጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው።  

በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነት የምንዛሪ ለውጥ ሲኖር አስመጪዎችን ብዙም የሚያበረታታ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህም ዜጎች ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት በአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ ሊያበረታታ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ የአገር ውስጥ ጫማን ለአብነት ብንወስድ፤ የአገር ውስጥ ጫማን በጥሩ ሁኔታ ማምረትና ጥራቱን መጨመር ከተቻለ  ተጠቃሚው ይበዛል፡፡ ይህም ከውጭ የሚገባውን ጫማ መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የአገር ውስጥ የጫማ አምራቾችን ያበረታታል ፡፡

ሁለት ወዶ ስለማይቻል ለጠቀሜታው መላቅ ሲባል እርምጃውን መውሰድ ግድ ይለናል እንጂ ሌላም ተጽእኖ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም የሚሉት የዘርፉ ልሂቃን፤ እንዲህ ያለው የምንዛሪ ለውጥ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ይሉናል። ትልልቅ ግንባታዎች ይገነቡበታል ተብሎ ከተያዘላቸው በጀት በላይ ወጪ እንዲጠይቁ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ሜጋ ለሚባሉ ፕሮጀክቶች የሚሆኑ ግብዓቶች አብዛኛዎቹ ከውጭ የሚገነቡ በመሆናቸው፣ ከዚህ በኋላ የሚፈጽሙት ግዥ ደግሞ በአዲሱ የምንዛሪ ዋጋ በመሆኑ የመገንቢያ ወጪያቸው ስለሚጨምር፡፡  

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለባንክ አስቀማጮች የሚታሰበው የወለድ ምጣኔ እስካሁን ከሚሠራበት አምስት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ ውሳኔ ከገንዘብ ምንዛሪ ለውጡ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ብሄራዊ ባንኩ ገልጿል፡፡ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጡና ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው የወለድ መጠን ተያያዥ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የገቢ ንግዱ በአብዛኛው ተመሠረተው በባንክ ብድር ላይ ነው፡፡ የብድር መጠኑ ከፍ እያለ ከመጣ የገቢ ንግድ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስቀማጮችን ለማበረታታትና፣ የባንክ ተጠቃሚዎችን ለማበራከትና የተቀማጭ ገንዘብ መጠንን ለማሳደግ እንደሚረዳ ታምኖ ተግባራዊ ሆኗል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የንግድ ባንኮች ከዚህ በኃላ ከኤክስፖርት ውጪ ላሉ ብድሮች ጣሪያ እንደሚቀመጥላቸው ታውቋል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ ባንኮች በሚቀመጥላቸው የብድር ጣሪያ መሠረት ብድር እንዲሰጡ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው የወጪ ንግድን ለማበረታታት ነው ፡፡

የብር የመግዛት አቅም በአንድ በመቶ እንዲቀንስ ሲደረግ፣ በዕቃዎቹ ዋጋ ላይ የሁለት በመቶ ጭማሪ እንደሚያስከትል እየተስተዋለ ነው።  በዚህ ስሌት መሰረት የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ በመደረጉ በዕቃዎች ዋጋ ላይ የ30 በመቶ ጭማሪ እንደሚያስከትል የሚጠበቅና በተግባርም እየተስተዋለ ነው። ስለሆነም የአሰራር እና የህግ ጥበቃው ሊጠናከር ይገባል። በሌላ በኩል የምንዛሪ ማስተካከያው በነዳጅ ግዥ ላይ የተወሰነ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል የሚለውም ስጋት አይሏል፡፡ መታወቅ ያለበትና መንግስትም በተደጋጋሚ እንዳለው ግን ነዳጅ ስትራቴጂካዊ ምርት በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት መሆኑን ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ምርት የሚታይ አይደለም፡፡ በግዥ፣ በተመን አወጣጥና በማከፋፈል ሥራ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት የተለየ ምርት ነው፡፡ ዛሬ የምንዛሪ ለውጥ በመደረጉ ነገ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ይደረጋል ማለት አይደለም።እንደምንግዜውም መንግሥት የነዳጅ ተመን ማስተካከያ በሚያደርግበት ወቅት በርካታ የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት እንደሚያስገባ መገንዘብ ይገባል እንጂ መደናበር እና ለሰው ሰራሽ ግሽበት እራስን ማመቻቸት አይገባም፡፡

መንግሥት የነዳጅ ውጤቶችን ራሱ ገዝቶ የሚያመጣቸው በመሆኑ ያለውን ወቅታዊ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ዋጋ ተንተርሶ የዋጋ ተመን እንደሚያደርግ አስቀድሞም ይታወቃል። ይህም ብቻ ሳይሆን የምንዛሪ ለውጥ በሌለበትም ጊዜ የዋጋ ማስተካከያ ሲያደርግ የነበረ መሆኑንም ማስታወስ ይገባል፡፡ይህ ለውጥ ሲደረግ መንግስት  በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይጎዳ በተቻለ መጠን  ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን ታሳቢ ያደረገ ግንዛቤ እና ተሳትፎ ያስፈልጋል።  

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰሞኑ ዕርምጃዎች ውስጥ የአገሪቱ ባንኮች ከወጪ ንግድ ባሻገር ላሉት ዘርፎች የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ ገደብ እንደሚያስቀምጥ ማስታወቁ አንዱ ነው፡፡ ይህ አሠራር ባንኮች በዓመት ከምትሰጡት ጠቅላላ ብድር ውስጥ እንደሚወሰነው መጠን ለኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲያውሉ የሚጠይቅ ነው፡፡ይህም ለወጪ ንግድ ዘርፍ የሚሰጠው ብድር ከፍ እንዲልና ላኪዎች እንዲበረታቱ ለማድረግ ተስቦ የሚተገበር አሠራር ነው ። ስለሆነም የንግድ ባንኮች ከዚህ በኃላ ከኤክስፖርት ውጪ ላሉ ዘርፎች የሚሰጡት ብድር ላይ ገደብ ይጣልበታል፡፡ ባንኮች በሚቀመጥላቸው የብድር ጣርያ መሠረት ብድር እንዲሰጡ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው የወጪ ንግድ እንዲሻሻል ለማበረታታት ነው ፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የገቢ  ዕቃዎች ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ከሚያራምዱ አገሮች አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህ በመሆኑም አሁን የተደረገው የምንዛሪ ለውጥ ጫና መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡በሃገር ውስጥ ምርቶች ላይ ሆን ተብሎ በሚፈጠር ደባ በስተጀርባ ያለውን ሃይል መጀመሪያ ልክ ማስገባት የመጀመሪያው ነው።በተለይ ምንም አይነት ከውጭ የሚገባ ጥሬ እቃ በማይጠቀሙ ምርቶችና ከምንዛሬ ለውጡ ጋር ተያያዥነት በሌላቸው አገልግሎቶች ላይ ለሚፈጠሩ የዋጋ ጭማሬዎች መንግስት የማወላዳ እርምጃ ካልወሰደ በስተቀር ለጤናማ እና ዘላቂነት ላለው እድገት ሲባል የተወሰደው እርምጃ አላማውን ስቶ ከመስመር ያስወጣናል። የወጪና ገቢ ንግዱን በተመለከተ ግን መፍትሄው ቀላል እና ሳይንሳዊ ነው። አብዛኛው የገቢ ንግድ በባንኮች በተፈጠረው የውጭ ገንዘቦች አቅርቦት እጥረት ምክንያት፣ ለግብይት ሲቀርብ የነበረው ገንዘብ ከጥቁር ገበያ እየተገዛ ነው፡፡ ከጥቁር ገበያ ሲገዛ የነበረው ገንዘብ፣ ከመደበኛው የባንኮች ምንዛሪ ጋር ሲነፃፀር የአሁኑን ጭማሪ ያህል ልዩነት የነበረው መሆኑም ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ይህ የጥቁር ገበያው ልዩነት የአስመጪው የትርፍ ህዳግ ውስጥ ሲንጸባረቅ እንደቆየ ይታወቃል የሚሉት ተንታኞች፣ አበዳሪ ተቋማት ወደፊት ከወጪ ንግዱ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ልክ የባንክ መተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) በተገቢው መጠን በመፍቀድና የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ የማድረግ ዕርምጃ ከወሰዱ ጫናው ሁሉ ተወግዶ እንደተባለውም የውጪ ንግዱን በማበረታታት የኢትዮጵያን ህዳሴ ማረጋገጥ ይቻላል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy