Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከመሪው ድርጅት ብዙ ይጠበቃል

0 357

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከመሪው ድርጅት ብዙ ይጠበቃል

አሜን ተፈሪ

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከጅምሩ ትክክለኛውን የህዝብ ጥያቄ አንስቷል፡፡ መሠረታዊ የሐገሪቱን ችግር ለይቶ ለህዝቡ መሠረታዊ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ የሚችል ትክክለኛውን መስመር በመፍጠር ታግሎ አታግሏል፡፡ በዚህም ለመበታተን እያቃሰተች የነበረችው ሐገር ፈውስ እንድታገኝ እና ሐገራዊ ደህንነታችን ተረጋግጦ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ እንድትቆም አድርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተኣምር የተባለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም አስመዝግቧል፡፡

 

ታዲያ በእስከዛሬው ጉዞው ብዙ ፈታዎችን እያለፈ፤ ገና ከውልደቱ ጀምሮ የገጠሙትን ለድርጅቱ፣ ለኣባላቱና ለህዝቡ ስጋት የሆኑ የተለያዩ ችግሮች እየተራመደ፤ ለችግሮቹም ተገቢውን የመፍትሔ አቅጣጫ በመቀየስ እየፈታ ተጉዟል፡፡ አሁንም ወቅታዊ አደጋ ሆነው ከፊቱ የተጋረጡትን ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጠባብነት እና ትምክህት፤ እንዲሁም እነርሱ የወለዷቸውን ችግሮች ለማስወገድ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን ፈተና ለመሻገርም ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ፤ ሁሉንም ህዝብ ሊያታግል የሚችል የመፍትሄ አቅጣጫ ቀይሶ ትግሉን አቀጣጥሎታል፡፡ ትግሉ እንዴት መመራት እንዳለበት የተብራራ ግንዛቤ ይዟል፡፡ ስለሆነም መስመሩን ይዞ ከታገለ፤ አሁን በተከሰተው ችግር የተሻለ ድርጅታዊ ጥንካሬ ፈጥሮ፤ መላ የድርጅቱን አባላት ይበልጥ አጀግኖ መጓዝ ይችላል፡፡

 

ባለፈው መስከረም ወር የግንባሩ አባል ድርጅቶች አመራሮች በተለያየ ጊዜ ባደረጉት ስብሰባ ወቅታዊውን ሐገራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ ውይይት በማካሄድ፤ የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ በመለየትና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባዔዎቻቸውን አጠናቅቀዋል፡፡  በሐገራችን ለረጅም ጊዜ የበላይነት ይዞ የዘለቀውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከምንጩ ለማድረቅ ቃል ገብተዋል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር እና አመለካከት የሚበረታው በከተሞች አካባቢ መሆኑ አስቀድሞ የሚታወቅ በመሆኑ፣ ትግሉም በዚሁ አካባቢ የሚደረግ ነው፡፡ ስለሆነም የመልካም አስተዳደርን ችግሮች በመፍታት ልማታዊነት የበላይነት እንዲይዝ ለማድረግ በተለየ ትኩረት መሠራት ያለበት በከተማ አስተዳደር ሥር ከሚገኙ መስሪያ ቤቶች እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቀር ነው፡፡ ለዚህ ትግልም ብቃት ያለው አመራር መስጠት ይገባል፡፡ ጠንካራ አመራር የማፍራት ስራውም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ገዢው ፓርቲ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን ይበልጥ ማቀጣጠል እና የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴውንም መረር-ከረር አድርጎ መያዝ ይኖርበታል፡፡

ኢህአዴግ በሚያካሂደው የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል የአመራሩንና የአባሉን ጠንካራና ደካማ ጎኖች፤ በህዝቡ ዘንድ ያሉትንም ክፍተቶች ለይቶ ያውቃል፡፡ በዚህም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የስርአቱ አደጋ መሆኑን ገና በጧቱ የገለፀ ሲሆን፤ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነት ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር ተገንዝቧል፡፡ ይህን ችግር ከስር መሰረቱ ካልተወገደ፤ በህዝቦች መራራ ትግልና መስዋእትነት የተገኘው ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ልማትና ፍትህ ሊቀለበስ እንደሚችል ተረድቷል፡፡ ታዲያ በሰላም፣ በዲሞክራሲ፣ በልማትና በፍትህ ረገድ የተገኘው ድል እንዳይቀለበስ፤ መክሮ እና ዘክሮ ያስቀመጠውን የትግል አቅጣጫ በመከተል ጠንክሮ መሥራት ይገባዋል፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ አባላትና አመራሮችም ምልዐተ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

 

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ የተሃድሶ ንቅናቄ በማቀጣጠል ላለፉት 15 ዓመታት ትግል ያደረግ እንጂ፤ አሁንም ረጅም መንገድ ከፊቱ ተዘርግቶ ይታያል፡፡ በርግጥ፤ ባለፉት ዓመታት ባደረገው ትግል በሐገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ከነበርንበት የድህነት አረንቋ በመላቀቅ አለምን ያስደመመ ስኬትም ማስመዘግብ ችሏል፡፡ በተመዘገበው ተከታታይ እና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም በሽግግር ላይ ያለ ማህበረሰብ መፍጠር ተችሏል፡፡

 

በየደረጃው የሚገኘው የድርጅቱ አመራር በማያቋርጥ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለችው ሐገራችን የድል ጉዞዋን እንድትቀጥል፤ ድርጅቱን ከተለያዩ ብልሽቶች በማዳን ባለው መልካም ዕድል በመጠቀም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡ በጥልቀት በመታደስ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ በየደረጃው የሚገኙት የድርጅቱ አባላትና አመራሮች  የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይገባቸዋል፡፡ ‹‹በጥልቀት በመታደስ ሀገራዊ ሕዳሴያችንን እናረጋግጣለን!!›› ሲሉ የገቡትን ቃል ኪዳን ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡

 

ኢህአዴግ መቼም ቢሆን ለሚያጋጥሙት ችግሮች ውጫዊ ምክንያት ከመስጠት ይልቅ ወደ ውስጥ በመመልከት ራሱን በማረም ላይ የሚያተኩር ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በብቃት በመተንተንና ሁነኛ የመፍትሔ አቃጣጫዎችን በመንደፍ ህዝብን አሳትፎ ለድል መብቃት የሚችል ድርጅት ነው፡፡ ሐገራችን ወደፊት የምትደርስበትን የዕድገት ደረጃ እና በየምዕራፉ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን ችግሮች ጭምር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተንትኖ መፍትሔዎችን በማስቀመጥ የሚታገል እና ቀድሞ የሚዘጋጅ የለውጥ ኃይል ነው፡፡

ኢህአዴግና የግንባሩ አባል ድርጅቶች ገና ከምስረታቸው ጀምሮ ፈታኝና ውስብስብ ሁኔታዎችን በድል መወጣት ብቻ ሳይሆን ተግዳሮቶችንም ወደ መልካም ዕድልነት በመቀየር፤ ፈታኝ ምዕራፎችን በማለፍ ከፍተኛ ድል እየጨበጡ የመጡ ናቸው፡፡

 

ኢህአዴግ እንደ ግንባር ከተመሰረተ ወዲህም ያጋጠሙትን ችግሮች ራሱን ማዕከል አድርጎ ከነምንጫቸው በጥልቀት ሲፈትሽ፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ሲያስቀምጥና መላ ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍም ለመታረም ሲተጋ እናውቀዋለን፡፡ በዚህም በሐገራችን ፈጣን እና ተከታታይ ዕድገት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡ በ2008 ዓ.ም ማገባደጃ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢህአዴግ ምክር ቤት ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት በግንባሩና በአባል ድርጅቶች በሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች እየተካሄደ ያለው ዳግም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄም ለሌላ ድል በሚያበቃው አኳኋን መፈጸም አለበት፡፡

 

በቅርቡ በአንዳንድ አካባቢዎች ለተከሰቱት ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ እየሰጠ፤ ህዝባችንን እያስመረሩ ያሉና ለልማታዊና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ፈተና የሆኑ ዋነኛ ችግሮችን እያስወገደ፤ የድርጅትንና የመንግስትን ስልጣን ለህብረተሰባዊ ለውጥ በማዋል ፈንታ፤ ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌን በማስወገድ መራመድ ይኖርበታል፡፡ ድርጅቱ ይህ ችግር ስር እየሰደደ መሆኑን ለይቷል፡፡ ይህም ችግር አሁኑኑ የማያዳግም መፍትሄ ካልተሰጠው በስተቀር የጀመርነው የሕዳሴ ጉዞ የሚቀለበስበት ዕድል ዝግ አለመሆኑን ገምግሟል፡፡ ስለሆነም፤ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉን ከውስጡ፣ በተለይም ደግሞ ከበላይ አመራሩ ጀምሮ እንዲቀጣጠል በማድረግ ሁሉም የድርጅቱ መዋቅር ራሱን በጥልቀት እየፈተሸ የሚታደስበትን አቅጣጫ ተከትሎ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይገባዋል፡፡ እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄው መጠናከር ይኖርበታል፡፡

 

ይህን በመሰለው ሁኔታ ከአመራር የሚጠበቅ ኃላፊነት መልካም ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም፣ ፈተናዎችን ደግሞ በጥበብና በፅናት በማለፍ፣ ተግዳሮቶችንም በማሸነፍ አገራችን በማያቋርጥ የዕድገት ሂደት እንድታልፍና ህዝቦቿን በሙሉ እየጠቀመች እንድትጓዝ ማድረግ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት ከአመራሩ ብዙ ይጠበቃል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy