Artcles

ከግጭት አትራፊው ማን ይሆን? (ክፍል ሁለትና የመጨረሻ)

By Admin

October 04, 2017

ከግጭት አትራፊው ማን ይሆን?

(ክፍል ሁለትና የመጨረሻ)

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው የህዝብ ንብረት ሠላም ወዳዱን ህዝብ ያሳዘነ ሆኖ አልፏል፡፡ ምንም እንኳን በግልባጩ የጥፋት ኃይሎችን ጮቤ ቢያስረግጥም፡፡ ሁል ጊዜም ቢሆን የጥፋት ኃይሎች ዓላማ ይኸው ነውና፡፡

በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሠላም ወዳድ ነዋሪዎች በፀረ ሠላም ኃይሎች ተንገላተዋል፤ ንብረታቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል፤ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ወድቆ ቆይቷል፡፡ በየአካባቢያቸው ከፍተኛ ዋጋ ያለው የህዝብና የመንግሥት ንብረት በፀረ ልማት ኃይሎች ወድሟል፡፡

በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለአብነት አነሳን እንጂ ከዚህም በላይ የሚገለፁ ጥፋቶች የደረሰባቸው ከተሞችና ተቋማት አሉ፡፡ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ድርጅቶችም ሳይቀሩ ጥቃት ሲደርስባቸው ተመልክተናል።  የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም እንዲሁ አገልግሎት የማይሰጡበት ደረጃ እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ የትራንስፖርት መስጫ ተሸከርካሪዎች፣ ባንኮች፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የህዝብ ሀብት የሆኑ የልማት ማሳለጫ ተቋማት እንዲሁ እንዲዘረፉና እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡

አሁን ሁሉም ነገር በሚፈለገው ደረጃ ላይ ነው ለማለት ባያስደፍርም ውጥረቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መርገባቸውን የየክልሉና የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ ያ ሁሉ ጥፋት እንዲደርስ ያደረጉት የጥፋት ኃይሎችም ምንም ሳያተርፉ ከስረው ወደየሰንኮፋቸው ተከተዋል፡፡ ለጊዜው ህዝብም ሆነ መንግሥት ነቅተውባቸዋልና ለሌላ ሴራ ዝግጅት ሊያደርጉ መሽገዋል፡፡ ተመሽገው ግን የሚቀሩ አይመስሉም፡፡ መንግሥት ከህዝብ፣ ከሚመለከታቸው አካላትና የፀረ ሽብር ትግል ከሚያደርጉ አገራት ጋር በመተባበር ከመሸጉበት እያወጣ በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ነው#።  

የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨትና ህዝብን በማደናገር የሰው ህይወት እንዲጠፋ አቅደው የመሩ አካላት በህጋዊ ፓርቲ ሽፋን የሻዕቢያን ተልዕኮ ለማሳካት የተሯሯጡ ኃይሎች ላይ መንግሥት ህገ መንግሥታዊ ርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል።

ስለምን ፀረ ሠላም ኃይሎች እኩይ ተግባራቸውን ማቆም ተሳናቸው; እንዴትስ መፍጨርጨራቸው በየጊዜው መልኩን እየቀያየረና እያየለ ይመጣል የሚለውን ጥያቄ እያነሳን የመሰለንን ምላሽ እየሰጠን እንቀጥል፡፡

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው በሰሞኑ ግጭት የህዝብ ንብረት ወድሟል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ሠላም ወዳዱ ማኅበረሰብ ተሸብሯል፡፡ ከምንም በላይ ውድ የሆነው የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ በተለይ ፀረ ሠላም ኃይሎች ቀድመው በዘረጉት መረብ በመጠቀም ባመቻቹት አመፅ ተሳታፊ መሆን ያልፈለገውን ገርፈዋል፣ ቤቱን አቃጥለውበታል፣ በአጠቃላይ በጥቅሙና በሚወደው ነገር ለማስገደድ ሞክረዋል፡፡ ብዙዎች ድርጊቱ የተፈፀመበትን ሁኔታ በማስተዋል ከሽብር ተግባር ጋር አመሳስለውታል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አሸባሪነትን ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲባል በሠላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ የወንጀል ድርጊትን ማሰብና መተግበር ሲል ይፈርጃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በ1999 ባሳለፈው ውሣኔ አሸባሪነትን ለፖለቲካዊ ግብ ሲባል በብዙሃኑ ላይ ፍርሃትን ለመፍጠር የሚታሰብ ወይም የሚፈፀም የወንጀል ድርጊት ሲል በይኖታል፡፡

በነዚህ ትርጓሜዎች ላይ ዓለም ይስማማል፡፡ የሌሎች አገራትን ህጎች መሠረት በማድረግ የፀረ ሽብር ህጉን ያወጣው የኢትዮጵያ መንግሥትም ከሞላ ጎደል በዚህ ትርጓሜ ይግባባል፡፡

ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት እንዲሁም ይህን ተከትሎ የታዩት ሁነቶች በሙሉ በዚህ መስፈርት የሚለኩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ድርጊቱን በአጭሩ “የሁከት ተግባር” ልንለው እንችላለን፡፡ ድርጊቱ ሁከት እንደሆነ ከተግባባን የድርጊቱ ፈጻሚዎች እንዴት ይፈጠራሉ የሚለውን ብናይ የበለጠ ሁኔታውን ለመረዳት ያበቃናል፡፡

ብሉም የተሰኘው ፀሀፊ ‹‹አሸባሪዎች የሚፈጠሩት በሁለት መንገድ ነው›› ይለናል፡፡ ቀደም ሲል ሲከተሉት የነበሩት የትግል (የውጊያ) ስልታቸው ሲወድቅባቸው አሊያም የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ እንደሆነ ይኸው ፀሀፊ ይተነትናል፡፡ ከኛው አብራክ የወጡት የራሳቸውን ዜጋ የሚያጠቁ አሸባሪዎቻችንም ከላይ ብሉም በጠቀሰው መንገድ የተፈጠሩ ሽብርተኞች ናቸው፡፡

በ1983 ዓ.ም የሽግግር መንግሥቱ መሥራች አባላት የነበሩት ኦነግና ኦብነግ ጥሩ ምሣሌዎች ናቸው፡፡ በፖለቲካ ትግላቸውም ሆነ በውጊያ ስልታቸው ሲወድቁ ነበር የዴሞክራሲያዊ የትግል መድረክን ረግጠው በመውጣት በምትኩ ወደ ሽብር ተግባር የተዛወሩት፡፡ አልሸባብም ቢሆን በተደጋጋሚ በገጠመው የውጊያ ሽንፈት በመማረር ነበር ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ሽብር ያዞረው፡፡

በአንድ ወቅት አገራችንን ወሮ የነበረው የሻዕቢያ መንግሥትም በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በከፈተው ጦርነት ትርፍ ቢያጣበት ነው ተላላኪዎችን እየላከ ቀጠናውን የሚያምሰው፡፡ እንደ ግንቦት ሰባ ያሉት አሸባሪ ድርጅቶችም ህዝብ በድምፁ ይሁንታውን ሲነፍጋቸውና ያወሩት ሁሉ አልደመጥ ቢላቸው ነው ወደጎራው የተካተቱት፡፡ የሽብር ሥራን ሥራቸው አድርገው ኪራይ የሚሰበስቡና ጥቅም የሚያጋብሱ እንዳሉም ይታወቃል፡፡

አሁን “ዴሞክራሲያዊ ትግል እያደረግን ነው” የሚሉት ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ምቹ ሁኔታ ካገኙ ሐሰተኛ ለምዳቸውን አውልቀው የሽብር ካባን እንደሚደርቡ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ባገኙት መድረክ ሁሉ የነሱ ዜማ አቀንቃኝ ተባባሪዎቻቸውን ይዘው ኢትዮጵያ ያፀደቀችው የፀረ ሽብር ህግ እንዲሻር የሚወተውቱት፤ ሁኔታዎችን እያመቻቹም ሰልፋቸውን ሲቀያይሩ የሚስተዋሉት፡፡

ከላይ ያነሳነው መነሻቸው አንደኛው ገፅታቸው ሲሆን ጠላታችን ብለው የፈረጁት አካል የሚቀዳጀው ድልና ስኬትም በእኩይ ተግባራቸው እንዲሰለፉ ይገፋፋቸዋል፡፡ ይህንን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምደን ብናየው ይበልጥ ይገለጥልናል፡፡ በአገራችን የፖለቲካ ተቃውሞ ጎራ ውስጥ ካሉት የጠባብም ሆነ የትምክህት ኃይሎች አብዛኞቹ እንዳለመታደል ሆኖ ለልማት ግስጋሴያችን ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ በህዝቦች የተባበረ ክንድ እየተገነባች ላለችው አገር ጠጠር ከማቀበል ይልቅ የተገነባውን የመናድ ተግባር ላይ የተሰማሩ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

በርካቶቹ ትናንት ስለዚህች አገር ሲያሰሙት የነበረው ሟርት የከሸፈባቸው ናቸው፡፡ ልማቱም የመጣው እነሱው በኮነኑት፤ በረገሙት ድርጅት (ኢሕአዴግ) በመሆኑ ይህንን መቀበል ለነሱ መርዝ ከመጠጣት በላይ ይሆንባቸዋል፡፡ ሌላው ትናንት አይዟችሁ ይሉናል ሲሏቸው የነበሩት ሁሉ የኢትዮጵያ መስመር ከአገሪቱ አልፎ እነሱን የሚጠቅም እንደሆነ ሲረዱ ፈነገሏቸው፡፡ በዚህም ደስተኛ አልሆኑም፡፡ በተለይ አገሪቱ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ እያገኘች የመጣችው ተቀባይነት የነሱን ሟርት የቀበረ ሆነ፡፡

ሌላው መንግሥት ያቀደውን ሁሉ እየፈፀመ የህዝብን ጥቅም እያረጋገጠና የህዝብ ተሳትፎ በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ እያጠናከረ መሄዱ ሴራቸው ይበልጥ እየተጋለጠ እንዲሄድ አደረገው፡፡ በመሆኑም ሁሉንም የመንግሥት ርምጃ ይቃወማሉ ያጥላላሉ፡፡ የሚያገኙትን ጥቅም ላለማጣትም ሲሉ ይፍጨረጨራሉ፡፡ እንደማያተርፉ ቢያውቁትም የአሸባሪ ባህሪ የታወቀ ነውና ሽብር ይፈጥራሉ፡፡ ከልማት ለመጎተት ያልሞት ባይ ጥረታቸውን ያደርጋሉ፡፡

እንግዲህ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የየራሳቸውን የዜሮ ድምር ፖለቲካቸውን ለማራመድ የተጉት ኃይሎች ከላይ የገለፅናቸው ናቸው፡፡ ባደረጉት ተሳትፎ ቀደም ሲል ከነበራቸው አሰላለፍም የተለየ ሰልፍ ፈጥረው በመታየት ብዙዎቻችንን አስገርመዋል፡፡ ለወትሮው በትምክህት የተወጠሩትና በጠባብነት የታጠሩት ኃይሎች የየቅል መገለጫ ነው የነበራቸው፡፡ ከሰሞኑ እንዳየናቸው ግን የማይዘልቅ ጋብቻ ሲፈፅሙ ታይተዋል፡፡ “ዋናው ወያኔን ማስወገድ ነው፡፡ ለነገ ነገ ያውቃል” ሲሉ ራዕይ አልባ መሆናቸውን ለሚያደነቁሩት ህዝብም አሳውቀዋል፡፡

ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች በሙሉ ላልተቀደሰው ጋብቻቸው መከሰት ተጨባጭ ማሣያዎች ይሆናሉ፡፡ የሞከሩት ሁሉ ከሸፈባቸው፤ በምርጫም ቢመጡ ህዝብ ፊት ነሳቸው፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ የተባሉ ኃያላን አገራት ከጤፍ አልቆጥራቸው አሉ፡፡ ታዲያ ምን ያድርጉ፡፡ ከዓላማ ዓላማ የላቸው፤ ከደጋፊ ወገኔ የሚሉት ህዝብ የላቸው፤ ከአገር አገር የላቸው፡፡ “ህዝብም ሆነ አገር ከፈለገ ይውደም” አሉና ወሰኑ፡፡

ወጣቱን እየማገዱም እነሱ ከውጭ በሪሞት እየተቆጣጠሩ ትግል አካሂደው በትረ ሥልጣን መጨበጥ አማራቸው፡፡ ጠባቡና ትምክህቱ ልጅህን ለልጄ ተባብለውም ተስማምቶ የማያውቅ ወደፊትም የማይስማማ ዝምድናን ሊመሰርቱ ከጀሉ፡፡  

የነዚህ መሰሪዎች ውጥን ሙሉ በሙሉ ከስሯል፡፡ ሟርታቸው እንደተለመደው በኖ ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ተረጋግቶ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሠላማቸው ተመልሰዋል። በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉት ህዝባዊ ውይይቶችም ህዝቡ “ሠላማችንን የነሱትን፤ ልማታችንንና ዕድገታችንን ያደናቀፉትን መንግሥት ልክ ያስገባልን” ሲል ተደምጧል፡፡ “ለማጋለጡ እኛም አለን” ብሏል፡፡

የሆነው ሆኖ ነገሩ ጠባሳ ጥሎም ቢሆን አልፏል፡፡ ለነገ ግን መንግሥትም ሆነ ህዝብ ሊማሩበት የሚገባ አጋጣሚ እንዳገኙ ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ መንግሥት ለእያንዳንዱ የልማት ሥራ ተገቢው የህዝብ ግንኙነት ሥራ በተቀናጀ መንገድ ማቀድ ያስፈልገዋል፡፡

የወጣቱ ሥራ ማጣትና በየደረጃውና በየፈርጁ የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግሮች የየበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት የጀመረው ጥረት ፍሬ ሊያፈራ ይገባዋል፡፡

ህዝብም ልክ ሁሌም እንደሚያደርገው ጥቅሙን ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን መቆሙን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ራሱ የመረጠውን ተወካዩን ራሱ እንደሚሽር መዘንጋ የለበትም፡፡ መጀመሪያ ወደ ሁከትና ግርግር ገብቶ ለሌባ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት በፊት ወኪሎችን ራሱ መጠየቅ አለበት፡፡ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ከመንግሥት ሊነጥሉት የሚፈልጉ ፀረ ሠላም ኃይሎችን በውል ሊለያቸው ይገባል፡፡

ይህ ከሆነ በመሀል ንፋስ ብሎ ነገር አይገባም፡፡ የተጀመረው ህዳሴያችንም ግቡን ይመታል፡፡ አሁን የጀመርነው እንቅስቃሴ እንደ አጀማመሩ ከዘለቀ የዓለም ድንቅ እየተባሉ እንደሚወደሱ ታሪኮች በዓለም ሁሉ እየተነሳ ይኖራል፡፡

 

ለነዚያ በትምክህት ለተወጠሩና በጠባብነት ለታወሩት ኃይሎች በመጨረሻ ይህን ልበላቸው፡፡ ታሪክ ለመሥራት ቆመናል፡፡ ታሪክ መሥራታችን ይቀጥላል፡፡ የታሪክ መሥሪያ ርምጃችንን ለማደናቀፍ በመንገዳችን የሚቆመውን ሁሉ እየዳመጥን፤ የሚካበውን እንቅፋት ሁሉ እየናድን ከግባችን መድረሳችን አይቀሬ ነው፡፡ የናንት ርምጃ የኛን ታሪክ የመሥራት ግስጋሴ አይገታም፡፡ እናንተም ላታመልጡ አትሩጡ!!