Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከጸረ ድህነት ዘመቻው ለሚያናጥቡ ፕሮፖጋንዳዎች ጆሮ መስጠት አይገባም

0 331

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከጸረ ድህነት ዘመቻው ለሚያናጥቡ ፕሮፖጋንዳዎች ጆሮ መስጠት አይገባም

ዮናስ

ኢህአዴግ ስልጣን መያዙ አይቀሬ በሆነበት ዋዜማና እንደተጠበቀውም ሃገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ባዋቀረው የሽግግር መንግስትና ዘመን የብሔር ጭቆናን በማስወገድ በዴሞክራሲ መሰረት ላይ የተዋቀረ አንድነትን ለመገንባት እንደሚሻ በይፋና በተደጋጋሚ አሳውቆ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም። ያም ሆኖ ግን በዚህ ጊዜ የአገሪቱ መበታተን አይቀሬ ይሆናል የሚል ስጋት የገባቸው ወገኖች ትንሽ ያልነበሩ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተለይ ደግሞ የኤርትራ ነፃነት ከመከበሩ ጋር ተያይዞ “ሌላውም የኢትዮጵያ ክፍል አንድ አንድ እያለ ወደዚሁ አቅጣጫ ያመራ ይሆናል” የሚሉና አንድነቱ ለአደጋ ባይጋለጥ እንኳ የአንድ ብሔር የበላይነት መፈጠሩ አይቀርም ብለው የሚሰጉ ምሁራንም ብዙ የነበሩ መሆኑም ስለአጀንዳችን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡

ይህ ተጠራጣሪነትና ስጋት በዚህ ብቻ አላበቃም። ኢትዮጵያ ስጋቶቹን ድል የነሳ አዲስ አቅጣጫ መያዟ ግልጽ እየሆነ በመጣበት የመጀመሪያ ዓመታትም በአገራችን የፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ላይ ከባድ ልዩነትና ተጠራጣሪነት ሰፍኖ የነበረ መሆኑም ይታወሳል፡፡ የኢህአዴግ መንግስት፣ በኢትዮጵያ ብዙኅነትን ከቀደምት አስተዳደሮች በተለየ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመያዝና ለማስተዳደር እንደሚፈልግ ባሳወቀ ጊዜም ሆነ በተግባር እያረጋገጠ መሆኑ በታየበት ሰአት፣ ሰፋ ያለው የከተማ ማህበረሰብ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ልሂቃን አቅጣጫውን በከፍተኛ ጥርጣሬ ከመመልከት አልፈው ጥርጣሬያቸውን ከወደቀው ስርአት ርዝራዦች ጋር ግንባር ፈጥረው ሲያራግቡና መረጋጋት እንዳይኖር ሲተጉ የነበረ መሆኑም የ20 አመታት ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንድትቀጥል ከፍተኛ  ፍላጎት ያላቸው በማስመሰል በመሰረቱ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ብዙህነትን የማያስተናግድ የነበረ መሆኑን ምክንያት በማድረግ ይህን ጥያቄ የሚመልሰውን አዲሱን አቅጣጫ አደጋ የሚጋርጥ አስመስለው  በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ግራ መጋባቶች ፈጥረው የነበረ መሆኑም በተመሳሳይ የማይዘነጋ ነው፡፡ አጀንዳችን አሁንም በተለይ በኦሮሚያና ሶማሊያ ክልሎች  የምናየው ሁከትና ሁከቱን መነሻ ያደረጉ የአመጻ እንቅስቃሴዎች የዚሁ ተቀጥላ መሆናቸውን  ማጠየቅ ነው።

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብዙኅነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዳደር መቻሏና ይህም በብዙሃኑ ህዝቦቿ ላይ የፈጠረው የእርስ በርስ መተማመን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን ጥርጣሬና ስጋት ቀስ በቀስ እያረገበው መሄዱ እሙን ነው፡፡ መብታቸው የተከበረ ማህበረሰቦች በአንድነት ከመኖር የተሻለ አማራጭ ሊወስዱ እንደማይችሉ በተግባር መታየቱን ተከትሎ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል ድረስ መከበሩ የመበታተን ቁልፍ እንዳልሆነ ታይቷል፡፡ በዚህ ላይ ያልተማከለው ፌዴራላዊ አስተዳደር ሁሉም ህዝቦች ያላቸውን ፀጋ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በፌዴራላዊ ስርዓቱ ላይ በጎ አመለካከት እንዲያዳብሩ ያስቻለና ወደፊትም አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑም ላይ ሁሉም ዜጋ ከስምምነት ላይ ደርሷል።

መንግስት ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ፍጥነት እያደጉ፣ ነገር ግን ደግሞ በአቅም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠረውን ያልተመጣጠነ እድገት ለማካካስ በማሰብ የሚሰጣቸው እገዛዎች፣ በተለይ በዳር አካባቢ የሚገኙ ታዳጊ ማህበረሰቦችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ኢትዮጵያዊ ገመድ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ ያደረገ መሆኑን ለመመስከር የግድ ምርምርን አይጠይቅም፤ ያለንበት ሁኔታና ኑሯችን እራሱ ምስክር ስለሚሆን።

አገሪቱን ከጫፍ ጫፍ የሚያስተሳስር የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት መስፋፋቱና ይህንንም በተናጠል ሳይሆን በጋራ ለመጠቀም የሚቻልበት እድል መስፋቱ፣ በዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተውን አገራዊ ገመድ በጠንካራ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አውታር ማጠናከር ተችሏል። ይህ በሆነበት አግባብ  ዛሬም ኦሮሞ፣ አማራ . . . ተጨቆነ፣ ተዘረፈ፣ ተሰደደ፣ ተገደለ … ወዘተ የሚሉ መፈክሮች እየተሰሙ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ባሳለፍናቸው ሃያ ስድስት ዓመታት በተሰሩ ተግባራዊና የአስተምህሮ ስራዎች በአገራችን ህዝቦች ዘንድ በልዩ ልዩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ይቻላል።  

ስለሆነምና ህገ መንግስቱ የዴሞክራሲና የሰላም፣ የፍትህና የእኩልነት ዋስትና እንደሆነ መግባባት ስለተፈጠረ ከውጭ በተልእኮ የሚመጣው አጀንዳ ሁሌም ጭንጋፍ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ስለሆነም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ላይ በመጀመሪያው የግንባታ ምእራፍ እንደነበረው በሻቢያ ተላላኪ ሃይሎች ወደአደባባይ መነዳት አይገባም። አሁን የሚያስፈልገን በምክንያት የሚቃወምና የሚደግፍ ህብረተሰብ ብቻ ነው። እየተገነባ የሚገኘው ሥርዓት የገበያ መሆን እንዳለበትና ሰዎች በሰሩት ልክ የመጠቀም ህጋዊ ዋስትና ያገኙ በመሆናቸውም ላይ ተመሳሳይ መግባባት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ግን የዚህ ስርአት ቀበኛ የሆኑ ጸረ ዴሞክራሲ ሃይሎች በስርአቱ ውስጥ የሉም ማለት አይደለም። እንዲያውም ከነዚህ ሁከቶች በስተጀርባም ስለመኖራቸው መጠርጠር አይከፋም። ስለምን ሲባል ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኞቹ ጠላቶቻችን እንደሆኑ፣ ስለዚህም ደግሞ በፍጥነት መልማትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለብን አጠቃላይ የጋራ ግንዛቤ ስለያዝን እነዚህን የአክራሪና ጽንፈኛ ሃይሎች በመንግስት ጉያ ውስጥ ሆነው ፌደራላዊ ስርአቱ ያጎናጸፋቸውን እድል ተጠቅመው በየክልላቸው ሚዲያ ሃገር ለማሳበድ ያወጧቸውን መግለጫዎች አይተናልና፡፡

ከፈጣኑ እድገት ጋር ተያይዘው የተከሰቱ ነባርም ሆኑ አዳዲስ የስርዓቱ ችግሮችም እንደዚሁ ከሞላ ጎደል የጋራ ስምምነት የተያዘባቸው ስለሆነ ችግሮቹን ለመፍታት ውጭ ከተቀመጠ ተላላኪ ቢያንስ እኛ የችግሩም የውጤቱም ሰለባና ተጠቃሚ የሆነው ቅርብ መሆናችን አያከራክርም፡፡ መቅረብ ብቻ አይደለም ኪራይ ሰብሳቢነት መጥፎ እንደሆነና ብዙኀኑን ህዝብ እንደሚጎዳ ከሞላ ጎደል በብዙኀኑ ህዝብ ዘንድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ዜጎች ከአመፅ ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድና በድርድር መብትና ጥቅሞቻቸውን ማስፋት እንዳለባቸው ከመተማመንም ላይ ደርሰዋል፡፡

በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረ መሆኑ እንደተጠበቀ ይህ ግን በፅኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑ አሁንም የመዋለልና ወደፊትና ወደኋላ የመመላለስ አዝማሚያዎች መታየታቸው የሚጠበቅ መሆኑን ከግምት በመክተት ከጸረ ድህነት ዘመቻው ለሚያናጥቡ ፕሮፖጋንዳዎች ጆሮ መስጠት አይገባም። ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ በህገ መንግስቱና የህግ የበላይነት ማስከበር ላይ፣ በልማትና በህዝብ ተጠቃሚነት አጀንዳዎች ላይ፤ እንዲሁም በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ በተነፃፃሪ የተሻለ ብሔራዊ መግባባት መፈጠሩን ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ ብቻ ነው የሚያስፈልገን።

በሕገ-መንግስቱ መግቢያ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ማህበራዊ ዕድገታቸው እንዲፋጠን፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸውን ተጠቅመው በነፃ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውንና መተማመናቸውን የገለፁበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ መሆኑን ለአፍታም እንኳ ቢሆን መዘንጋት አይገባም።

 

ህገ መንግስቱን የማፅደቁ ሂደት በምልዓተ-ሕዝቡ ሰፊ ውይይትና ተሳትፎ ያለፈ በየደረጃው ከፍ ያለ ትግል የተካሄደበትና ዴሞክራሲያዊ የነበረ መሆኑን ለግጭት መነሻ ተደርገው ከሚቀርቡ ፕሮፖጋንዳዎች ጎን ለጎን ማስታወስ ያስፈልጋል። መሰረታዊ አቋሞቻቸው ተቀባይነት ያላገኘው ወገኖች የመጨረሻ ምሬታቸውን በሂደቱ ዴሞክራሲያዊነት ላይ ለማሳበብ ዛሬም እየሞከሩ መሆኑ በሚገባ ተስተውሏልና።

 

የህዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት በሕገመንግስቱ ከተደነገገ ጀምሮ ከፌዴራል እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የህዝብ ምክር ቤቶች ተደራጅተው በህግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በፌዴራል ደረጃ የተቋቋሙት ሁለቱ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በየአምስት አመቱ በሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ በዜጎች ቀጥተኛና ነጻ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች የሚሳተፉበት ነው።  የተወካዮች ምክር ቤት ፖሊሲና ህግ የማውጣት፣ አስፈጻሚ አካሉን የስራ መርሃ ግብርና በጀት የማጽደቅ፣ ስራ አፈጻጸም የመከታተልና የመቆጣጠር፣ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩን ሹመት የማጽደቅ፣ በክልሎች ሰብአዊ መብቶች ሲጣሱ በክልሉ ጋባዥነት ወይም በራሱ ተነሳሽነት ጣልቃ በመግባት የማረጋጋትና መፍትሄ የመስጠት፣ ወዘተ ሃላፊነት የተሰጠው ሕገመንግስታዊ ተቋም መሆኑንም ከጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዘው ለሚረጩ መርዞች ማጤን ያስፈልጋል።

 

ሌላኛው እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአገራችን ሰላማዊ ሽግግርና በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት እንዲገነባ ያስቻለ ተቋም ነው። ሕገመንግስታዊ መሰረት ያላቸው ሆነው የተገኙ በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡ የማንነት ጥያቄዎች ለምሳሌ የስልጤ፣ የአርጎባ፣ የቅማንት የፌዴሬሽን ምክርቤት በተናጠልና ከክልሎች ጋር በመነጋገር ምላሽ እንዲያገኙ አድርጓል። በሌላ በኩል በተለያዩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎች ሕገመንግሥታዊ መሠረት የሌላቸው ከሆኑ ሕገመንግሥታዊ ያለመሆናቸውን ከህገመንግሰቱ መርሆዎች በመነሳት ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማና የሁለቱ የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈሉበትን ቀመር የመወሰን ሥልጣንና ተልእኮ የተሰጠው በመሆኑ የሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ሚና በመጫወት የሚገኝ መሆኑንም ስለፍትሃዊነት ከሚነሱ ጥያቄዎችና የሚረጩ መርዞች ጋር ማገናዘብና ከጸረ ድህነት ዘመቻው ሊያናጥብ የሚተጋን ሃይል መታገል፤ ብሎም መግታት ይገባል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy