ethiopian news

Artcles

ወቅቱ የሚጠይቀው ወሣኝ ተግባር…

By Admin

October 17, 2017

ወቅቱ የሚጠይቀው ወሣኝ ተግባር…

አባ መላኩ

የኢትዮጵያ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል።  ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ካልታከለ ደግሞ መልካም አስተዳደር አይሰፍንም ብሎም ኪራይ ሰብሳቢነት አይወገድም። እናም መላው ሕዝብ  ተባብሮ መታገል ይኖርበታል።

መልካም አስተዳደር እስካልሰፈነና ኪራይ ሰብሳቢነት እስካልተወገደ ድረስ የቱንም ያህል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አገራዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ቢጤኑ ውጤት አልባ መሆናቸው እርግጥ ነው።  የህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን መነሻ አድርገው የተዘጋጁ ወርቃማ ህግጋት፣ የልማት ፖሊሲዎችና የዕድገት ስትራቴጂዎች ቢወጡም መልካም አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ይሰፍናል ብሎ ማሰብ ከቶ አይቻልም። በመሆኑም ኪራይ ሰብሳቢነትን የማስወገድና መልካም አስተዳደርን የመገንባት ጉዳይ ይዋል ይደር ሊባል የሚችል ተግባር አይደለም፡፡

በዚህ ረገድ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው የሚባሉትን አመለካከትንም ሆነ ተግባር ደረጃ በደረጃ በመለየት ለመፍታት ከምንጊዜውም የተሻለ የሥራ ግምገማ ማካሄድ ይገባል። ራስን ወደ ውስጥ በማየት ብሎም የለውጥ አመለካከት በማስረጽ መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በመድፈን የተጀመረውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማሳካት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ከወዲሁ በእልህና በቁጭት በታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ በሚሰነዘረው ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ጆሮ ነፍጎ በቀጣይ በአገሪቱ ሠላም ሰፍኖና መልካም አስተዳደር ተረጋግጦ ማየት ህልማችን ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት በመናድ የልማታዊ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

በገጠር የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ መሠረት ለመናድ የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወቃል። በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ሰው በላውን የደርግ መንግሥት ገርስሶ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት በከተማም ሆነ በገጠር ኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የተንሰራፋበትና ልማታዊ አስተሳሰብ የሚባል ነገር ያልነበረበት ሁኔታ ነበር።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በገጠር የመሬት ክፍፍል የተደረገ እና አርሶ አደሩ መሬት ያገኘበት ሁኔታ ቢኖርም አንዳንድ የፍትሃዊነት ችግሮችን የማስተካከል ሥራ በመከወንና በአንዳንድ አካባቢ የነበሩ በተገቢው መልክ ክፍፍሉ ያልተደረገባቸው አካባቢዎች ብቻ የማስተካከያ ተግባሮችን በመፈፀም ባለበት እንዲሄድ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዞ በአርሶ አደሩ ዘንድ የነበረ ኋላ ቀር አስተሳሰብን ለመቅረፍ ያላሳለሰ ጥረት ተደርጓል።

አርሶ አደሩ በላቡ ሰርቶ ጥሮና ግሮ አኗኗሩን መቀየር የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸትና የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወነው ተግባር በገጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ዋስትና ለማረጋገጥ የጎላ ድርሻውን መወጣት እየቻለ ያለበት ሁኔታ መፈጠሩም የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ለመዝጋት የተደረገው ጥረት አጋዥ ሚና እንደነበረው ለማየት ይቻላል።

አርሶ አደሩ በተሰጠው የእርሻ ቦታ ላይ የራሱንና የቤተሰቡን ላብ አፍስሶና በመንግሥት ከሚመደቡ ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እያገኘ ሰርቶ ከድህነት መላቀቅ የሚቻል መሆኑን በተግባር በመገንዘቡ ልማታዊነቱ ባደገ ቁጥር በገጠር የኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት እየተናደ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

በአሁኑ ወቅት ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቨስተርነት የተቀየሩ አርሶ አደሮች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በገጠር ሞዴል አርሶ አደሮች ሌላውን እየመሩና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመሰባሰብ ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው ተነስተው ልማታቸውን እያረጋገጡ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢነት መሠረት መናድ ሌላው ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በዚህ መልክ ልማታዊነት እየተረጋገጠና ኪራይ ሰብሳቢነትን ነቅሎ ለመጣል እየተናነቀ ይገኛል። በከተማም በተመሳሳይ መልኩ የኪራይ ሰብሳቢነትን የበላይነት ለመድፈቅና ልማታዊነትን ለማንገስ ቀላል የማይባል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

እንደ መሬት፣ የመንግሥት ግዥና ንግድ የመሳሰሉ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ምንጭ ተደርገው የሚወሰዱ ዘርፎች ተለይተው በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ጥረት እየተደረገ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና ልማታዊነትን ለማጠናከር መልካም አስተዳደርን ማስፈን ወሣኝ ነው።

መልካም አስተዳደርን ማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነትን አንድ መንገድ መዝጋትና የአገሪቱን ልማት ማፋጠን መሆኑን የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት ለመልካም አስተዳደር መስፈን የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን መልካም አስተዳደርን የማስፈን ሥራ የአንድ ጀምበር ተግባር አይደለም። ጊዜን የሚጠይቅና በሂደቶች የሚከወን እንደሆነ ይታወቃል።

በአገሪቱ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዕድገት የሚወሰነውንና በየጊዜው መሻሻል እያሳየ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር ክንዋኔን በአንድ ጀምበር እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉ አንዳንድ ወገኖች በአገሪቱ መልካም አስተዳደር የለም እያሉ በተደጋጋሚ ከማስተጋባትም ባሻገር በየጊዜው የተለያዩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችን በማምጣትና በአገሪቱ የተረጋገጠውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማያግዝና ለማጠናከር በማይጠቅም መልክ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።

የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ፅንፈኞቹ ስለዘመሩ ሳይሆን መንግሥት በአገሪቱ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባር ልማታዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከሚኖረው ሚናና የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ቀዳሚ አጀንዳውን አድርጎ የያዘው ጉዳይ በመሆኑ ነው። መልካም አስተዳደር የህልውና ጉዳይ ነው። ምክንያቱም መልካም አስተዳደርን ማስፈን ካልተቻለ ኪራይ ሰብሳቢነትን ደፍቆ ልማታዊነትን ማረጋገጥ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ስላለው ነው። ይህን ጉዳይ ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ መግለጼን ማስታወስ እፈልጋለሁ።

መልካም አስተዳደር በማስፈን ከፊታችን የተጋረጠውን ኪራይ ሰብሳቢነት ለበርካታ አገራት የልማት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት የደረጀ ማህበራዊ ሥፍራ እንዳይዝና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዳይረጋገጥ አፍራሽ ሚና የሚጫወት ክስተት መሆኑን የተገነዘቡ የለውጥ ኃይሎች ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር ትግል የገጠሙበትም ጊዜ ሩቅ መሆኑን የሚያመለክቱ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ብዙ ናቸው።

በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ የሰመረ ጉዞ ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ኪራይ ሰብሳቢነት ሥጋት አይደለም ብሎ መከራከርና ማድበሰበስ የሚቻል አይሆንም፡፡ አገሪቱ ያላትን ውስን ጥሪት፣ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና ማሣ የህዝቦቿን የመሥራት አቅም ተጠቅማ ከዘመናት ድህነት ለመውጣት የጀመረችውን ፈጣን የልማት ሩጫ በስውር ገመድ ጠልፎ በግልጽ የሚጥል የዕድገት ጋሬጣ ስለሆነ አምርራ እየታገለችው ትገኛለች፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት በዘላቂ ዴሞክራሲና በልማት አስተሳሰብ ንቅናቄ ውስጥ ገብተው በህዳሴ ጉዞ ላይ የሚገኙ ህዝቦችን ጥረት ለማምከን የሚፈታተን እፍኝ የማይሞሉ ጮሌዎች ተሰርቶ ባልተገኘ ሀብት እንዲሞላቀቁና ብዙሃን በድህነት ታጅለው እንዲቆዩ የሚደረግ አስተሳሰብና ድርጊት ስለሆነ የማስወገዱ ጉዳይ ይዋል ይደር የሚባል አይሆንም፡፡ ወደ ድህነትና ኋላ ቀርነት አረንቋ ዞሮ መመለስ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ስለማይታሰብ የልማት ርምጃን ማፋጠን ይጠበቃል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት ደግሞ የልማት ርምጃን የሚያደናቅፍ እንቅፋት ስለሆነ ከስሩ እየተመነገለ ወደ ዳርቻ ሊጣል ይገባል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አረምም እየተነቀለ በምትኩ መልካም አስተዳደርን በማስፈን አገርን ለማልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ማብቃት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው፡፡