Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሀገር መገለጫው ሰንደቅ

0 885

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሀገር መገለጫው ሰንደቅ

                                                                                መዝገቡ ዋኘው

ሰንደቅ አላማችን ሀገራዊ መለያችን የማንነታችን መገለጫ ማሳያ ክብራችን ነው፡፡ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ በየትኛውም አለም ታላቅ ክብር ያለው ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብ በብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ይወከላል፡፡ የሀገራዊ አንድነት፣ የነጻነት፣ የማንነት ክብር . . .  ሁሉ የሚገለጸው በሰንደቅ አላማ ነው፡፡

በብሔራዊም ሆነ በአለም አቀፍ መድረክ ሀገር የምትወከለው ከሌላው በሚለያት፣ የእርስዋ ብቻ መገለጫ በሆነው፣ ሕዝቦችዋንና ታሪክዋን በሚገልጸው ልዩ ሰንደቃላማዋ ነው። ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ለሰንደቅ አላማቸው ያላቸው ብሔራዊ ፍቅር የተለየ ነው፡፡ በየትውልዱ ተራም ሲተላለፍ በኖረው ባሕላችንም መሰረት ለሀገርና ለሰንደቅ አላማ ክብር ጸንቶ መቆም መስዋእትነትም መክፈል የክብሮች ሁሉ የላቀው ሀገራዊ ክብር ነው፡፡

ሰንደቅ አላማ ሁል ግዜም ተከብራና ከፍ ብላ እንደትውለበለብ የሚያደርጉዋት የተከበሩና የምትወክላቸው ዜጎችዋ ናቸው፡፡ ሕጻነት ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ሀገራዊ ፍቅራቸው ያድግ፣ ይጎለብት ዘንድ በትምህርት ቤት ስለሰንደቅ አለማ ምንነትና ክብር ይማራሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች ተማሪው ገብቶ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ሁሉም በአንድ ላይ ተሰልፎ ብሔራዊ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ነው ወደ ትምህርት ክፍላቸው እንዲገቡ ይደረግ የነበረው፡፡ ይሀው ባሕል ዛሬም ቀጥሎአል፡፡

ብሔራዊ መዝሙር ዘምረው ሰንደቅ አለማውን ይሰቅላሉ፡፡ የሰንደቅ አላማ ክብርና ታላቅነት በብዙ መልኩ ነው የሚገለጸው፡፡ በወታደራዊ ስነስርአት ከፊት ለፊት ቀድሞ በፊት በሰልፈኛው መሪ ተይዞ ሌላውን የሚመራው ሰንደቅ አላማ ያያዘው ነው፡፡ ትርጉሙ ሁላችንም በሰንደቅ አላማችን ስር ነን፤ ለሰንደቅ አላማችንም ክብር እንቆማለን፤ መስዋእትነትም እንከፍላለን የሚል ነው፡፡

የትኛውም ወታደራዊ ስልጠና ሲጠናቀቅና ተመራቂዎች በስነስርአቱ ላይ ሲሳተፉ ሀገሬን ወገኔን በቅንነትና በታማኝነት እስከ ሕይወት መስዋእትንት ድረስ አገለግላለሁ፤ ለሰንደቅ አላማዮ ታማኝ ነኝ፤ ብለው ቃለ መሀላ የሚፈጽሙት በሰንደቅ አላማው ስር ሸብረክ ብለው በመንበርከክ  ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ሌላው እጁን ከፍ አድርጎ የጋራ ቃለ መሀላውን ይፈጽማል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሲመረቁ ቃለ መሀላ የሚፈጽሙት በብሄራዊ ሰንደቅ አላማው ስር ነው፡፡ ሀገሬን ወገኔን በተማርኩት ሙያ በቅንነት በታማኝነት ላገለግል ቃል እገባለሁ የሚሉት በሰንደቅ አላማው ስር ሆነው ነው፡፡ ሰንደቅ አላማ የድፍን ሀገር የነጻነትዋ የተጋድሎዋ የክብርዋ የመላ ሀገሪቱ ሕዝብ መገለጫ ነው፡፡

አያቶቻችን ከወራሪ ጠላት ጋር ለመፋለም ሲዘምቱ ከፊት አስቀድመው የሚጓዙት የሀገራቸውን ሰንደቅ አላማ ነበር፡፡ ትርጉሙ ከሀገሬ በፊት ልሙት የሚል ነው፡፡ አትሌቶቻችን ጥንት በሮም አደባባይ በኋላም በተለያዩ የአለም አደባባዮች ድል ባደረጉና ባሸነፉ ቁጥር በፍጥነት አይናቸው የሚወረወረው ሰንደቅ አላማቸውን ፍለጋ ላይ ነው፤ የማንነታቸው መለያ መታወቂያቸው ነውና ይህን ማድረጋቸው ትክክል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ሀገሬ ኢትዮጵያ ነች፤ ያሸነፈችውም ኢትዮጵያ ነች ማለታቸው ነው፡፡

ሁሌ እንደምናየው አያቶቻችን ሰንደቅ አላማቸውን ከፍ አደርገው በማውለብለብ ነው ድል አድራጊነታቸውን የሚገልጹት፡፡ ኢትዮጵያም ማሸነፍዋ የሚታወቀው በዚሁ ግዜ ነው፡፡ ሰንደቅ አላማዋ በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ ደምቆ ሲውለበለብ ይህ ልዩ ሰአት፤ በተለይ በሀገር ውስጥ ውድድሩን በሚከታተለውም  ሆነ በውጭ በሚገኙት ዜጎቻችን ዘንድ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ብሎ ሲያዩ በደስታ ሲቃ የሚያነቡበት፤ እንባቸው ኮለል ብሎ የሚወርድበት በርካታ አጋጣሚዎችን አስተውለናል፡፡ የሀገርና የሰንደቅ አላማ ፍቅር በቃላት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ የገዘፈና የጠለቀ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ከወራሪ ጠላቶች ጋር በመጋፈጥና በመዋጋት በታላቅ መስዋእትነት የተከበረ፤ የሚያኮራ ሰንደቅ አላማ ነው ያለን፡፡ ሰንደቅ አላማ ከአንዲት ሉአላዊት ሀገር መገለጫነቱም በላይ በብዙ ሚሊዮኖች፣ ቢሊዮኖ ሕዝብ ያላቸውም  ሀገራት ብቸኛ መገለጫና መወከያቸውም ነው፡፡

የእኛ ሕዝብ ቁጥር ወደ 103 ሚሊዮን ደርሶአል፡፡ እነቻይና 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ሕዝብ ያላቸው ናቸው፡፡ ህንድና ናይጄሪያ ያላቸው የብሄር/ብሄረሰቦች ቁጥር የትየለሌ ነው፤ ይሁን እንጂ፣ ሁሉም በአንድ አገር ወካይ ሰንደቅ አላማቸው አማካይነት ነው የሚወከሉት፡፡ የዘንድሮው የሰንደቅ አላማ ቀን የሚከበረው “ራእይ ሰንቀናል፤ ለላቀ ስራም ተነስተናል” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡

ሀገራችን ጥንትም በአለም ቀደምት ከሚባሉት ጥቂት ሀገራት አንድዋ የነበረች ስትሆን ዛሬ ደግሞ ቀድሞ የነበረውን ታላቅነትዋን በበለጠ መልኩ ለመመለስ ለማሳደግ ቀን ከለሊት ሕዝቦችዋ እየሰሩ ያሉበት ከትላንት ዛሬ በተሻለ ደረጃ የምትገኝበት ከድሕነትና ኃላቀርነት ለመውጣት ታላቅ ተገድሎ እያደረገች የምትገኝበት በርካታ ድሎችም ያስመዘገበችበት ግዜ ላይ ነው የምንገኘው፡፡

ይህንን የተሰነቀ ታላቅ ራእይ ከግብ ለማድረስ ተግቶ መስራት የሀገርን ሰላምና ደሕንነት መጠበቅ በሕዝቦችዋ መካከል ያለውን ፍቅርና ወንድማማችነት መከባበርና መደማመጥ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር በመፍታት የሀገራችን ልማትና እድገት በቀጣይነት እንዲዘልቅ የማድረጉ ኃላፊነት የማንም ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች የጋራ ኃላፊነትና ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡

ሰላምዋን መረጋገትዋን ልማትና እደገትዋን የማይፈልጉት የውጭ ኃይሎች በሕዝቡ ውሰጥ ብጥብጥና ሁከት ግጭት እርስ በእርስ መባላት እንዲነሳ ለማድረግ ለዘመናት ሲሰሩ ሲሞክሩ ሕዝብ ደግሞ ሲያከሽፍባቸው ኖሯል፡፡ ሀገሩን ሲጠብቅ ሰንደቅ አላማውን በታላቅ መስዋእትነት ሲያስከብር አስከዛሬ ዘልቆአል፡፡ ዛሬም የተጋረጡበትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እየፈታ ሀገሩንና ሰላሙን በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን በሕዝቦች እኩልነት ላይ ለተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መሰረትና መገለጫም ነው፡፡ በሕዝቦች ተሳትፎ ፈጣን ልማትና ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማረጋገጥ ሰንደቅ አላማዋን ከፍ እያደረገች ያለች አገር ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ መገንባት ተችሎአል፡፡

በታላቅ ሕዝባዊ ተሳትፎ በደመቀ ስራና ትግል በታላቅ ጥረትና ሕዝባዊ ትጋት የብሩሕ ተስፋ ባለቤት ለመሆን በቅተናል፡፡ ሰላማችን የላቀ ልማታችን ዋስትና በመሆኑ ለውይይትና ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ የሀገር ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ሊኖር አይችልምና በሀገር ሰላምና ደሕንነት ላይ መደራደር አይቻልም፡፡

ብዝሐነታችን ከጥንት እስከዛሬ በአብሮነት ለጸናና ለዘለቀው አንድነታችን ምሰሶና የማእዘን ድንጋይ ሁኖ የኖረ ነው፡፡ የማይናወጥ፣ የማይላላ፣ የማይናጋ፣ የማይሸረሸር አለትም ነው፡፡ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማችንን ማክበር የዜግነት ግዴታም ነው፡፡ በሕዝቦች መካከል መተማመን የፈጠረ አንድነታቸውን ያጸና፤ ለጋራ ሀገር በጋራ እንዲቆሙ፣ እንዲሰሩ፣ እንዲሰለፉ ማድረግ ያስቻለና የሚችል ነው ሰንደቅ አላማ፡፡

በተለያዩ የሀገራችን የታሪክ ዘመናት ዜጎች ለሰንደቅ አላማቸው ክብር ሲሉ ታላቅ መስዋእትነትን ከፍለዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሰንደቅ አላማን ጥልቅ ክብር ትርጉምና ማንነት ከቀደምት አባቶቹ በመማር ሊጠብቀውም ይገባል፡፡ ሀገርና ሕዝብ የሚወከለው በሌላ ሳይሆን በብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ነው፡፡

ሰንደቅ አላማ ሁሉንም ዜጎች በጋራ አስተባብሮ በአንድነት የሚያጸና፣ የሚያቆም፣ ለሀገር ልማትና እድገትም በጋራ የሚያሰልፍ፣ ልዩነቶችን በመቻቻል ለመፍታት የሚያስችል፣ የጋራ ማንነትንና ብዝሀነትን ሀገራዊ ውበትና ድምቀትን ጥንካሬና ብርታትን ጭምር የሚገልጽ በውስጡ የታመቀ ኃይልና ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡

ለሀገር ክብር መቆም ማለት ለሰንደቅ አላማ ክብር መቆም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ትርጉም የለውም፡፡ የዛሬው ትውልድ ሰንደቅ አላማውን በአህጉሪቱም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ አድርጎ ሊያውለበልብ የሚችልበት ሰፋፊ እድሎች አሉት፡፡ በእውቀትና በትምህርት ልቆ በመገኘት ለሀገሪቱ ልማትና እድገት ሰፊ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በመስራትና በማካሄድ፤ የአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ባለቤት በማድረግ፤ ለቴክኒዮሎጂ መስፋፋት በመትጋት፤ ሀገሩንና ወገኑን ከድሕነት አረንቋ ለማላቀቅ ስራን አክባሪ ትውልድ በመሆን፤ ሀገሩን በታላቅነት፣ በልማትና በእድገት ማስጠራት ይጠበቅበታል፡፡ ሰንደቅ አላማው የሚከበረው፣ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ የሚቻለው ታላላቅ ስራዎችን (በውስጥም በውጭም) በመስራት ነው፡፡ ክብር ለሰንደቅ አላማችን !!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy