የህንዱ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪንድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

By Admin

October 04, 2017

የህንዱ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪንድ ለሶስት ቀናት ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ከቀትር በኋላ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የፕሬዝዳንት ኮቪንድ ጉብኝት የኢትዮጵያና ህንድን የሁለትዮሽ ግንኙነትን በሚያሳድጉ ጉዳዮች ለመምከር፣ በንግድና ባዛር ለመታደምና በኢትዮጵያ ከሚገኙ የህንድ ማህበረሰብ አባላት ጋር ለመገናኘት ያለመ መሆኑ ተነግሯል።

በፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፕሬዚዳንቱ ከ54 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን የጎበኙ የመጀመሪያው የህንድ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

ህንድ ከ40 በላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከተሳተፉበት የ2015 የሕንድ-አፍሪካ ጉባኤ ወዲህ ከአፍሪካ ጋር ያላት ትስስር እየጎለበተ ነው።

ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት እንደተጀመረ የሚነገርለት የኢትዮጵያና ህንድ ምጣኔ ሃብታዊና የንግድ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2015 ድረስ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል።

ኢትዮጵያ 7 ነጥብ 4 በመቶ የገቢ ምርቶችን ከህንድ የምታስመጣ ሲሆን፥ ይህም ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛዋ አገር ያደርጋታል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ከ584 በላይ የሕንድ ኩባንያዎች ከ2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ በጨርቃጨርቅ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና መሰል ዘርፎች መሰማራታቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ምንጭ፦ ኢዜአ