NEWS

የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ላለፉት ሰባት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ አጠናቀቀ

By Admin

October 12, 2017

በትግራይ ክልል ባለፈው አመት በተጀመረው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ በህዝብ ተደግፎ ውጤት እያሳየ መሆኑን የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ገለጸ።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ከመስከረም 22 ቀን እስከ መስከረም 28 ቀን ያካሄደውን ስብሰባ አጠናቋል።

በቆይታውም በ2009 ዓ.ም የነበረውን የመንግስትና የድርጅቱን የስራ አፈጻጸም ገምግሟል።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን በተካሄደው ጥልቅ ተሀድሶ ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎና ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማዕከላዊ ኮሚቴው አሳስቧል።

በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ፀገዴ እና ጠገዴ አካባቢ የነበረው የወሰን ማካለል ጥያቄ የሁለቱን ክልል ህዝቦች ትስስር በሚያጠናክር መልኩ መፈታቱን ማዕከላዊ ኮሚቴው አድንቋል።

በኦሮሚያ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድንበር አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት፥ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ህውሃት፣ የክልሉ መንግስት እና ህዝቡ የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል ብሏል በመግለጫው።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ችግሩን ከሌሎች እህት ድርጅቶች ጋር በመሆን፥ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣም ጠቁሟል።

ህገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓቱን ለማፍረስ መልኩን እየቀያየረ እየተከሰተ ያለውን የትምክህት እና ጥበት አደጋ ለመመከትም፥ ህወሃት ከእህት ድርጅቶቹ ጋር ተባብሮ ይሰራልም ብሏል ኮሚቴው።

 

በዛይድ ተስፋዬ