Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የልማት ማስፈፀሚያ ዋነኛ መሳሪያችን

0 331

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የልማት ማስፈፀሚያ ዋነኛ መሳሪያችን

                                                 ቶሎሳ ኡርጌሳ

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው የትምህርት ተሳትፎና ተደራሽነት፤ትምህርት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደጃፍ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በመሳካት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ካሳኩ ጥቂት የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።

ይህም የትምህርቱ ዘርፍ የልማታችን ዋነኛ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ሆኖ እየቀጠለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ እውነታም ለዚህች ሀገር ህዳሴ እውን መሆን በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት ዜጎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲጫወቱ የሚያስችል እንደሆነም ለመረዳት አይከብድም።

እንደሚታወቀው በትምህርቱ ዘርፍ በመጀመሪያው የልማት ዕቅድ የተገኙትን ውጤቶች ከሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር ስራው እየተሳለጠ ነው። በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትምህርቱ ዘርፍ የህፃናትንና የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ የሚገድቡ ችግሮች ለመቅረፍ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ከሀገራችን የትምህርት ግቦች ጋር የሚጣጣሙ የድህረ 2015 ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የልማት ግቦች የዕቅዱ አካል ተደርገው ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው።

ትምህርትን በተመለከተ ቁልፉ ጉዳይ ጥራት ቢሆንም፤ ቀጥሎ ትኩረት የሚያሻቸው ከሽፋን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ይህንኑ ጉዳይ ለማሻሻል እየተሰራ ነው። የመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን የማስፋፋት ጉዳይ ነው።

በያዝነው የዕቅድ ዘመን ይህን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለቅድመ መደበኛና የጐልማሶች ትምህርት ትኩረት በመስጠት ስራው እየተሳለጠ ነው። እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የመምህራንና የትምህርት ቤቶችን ጥራትና ቁጥር ለማሳደግ የሚወሰዱ ርምጃዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

ርግጥ እቅዱ ከተጀመረ ሶስተኛውን ዓመት ቢይዝም፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት በየደረጃው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ፕሮግራም ዘርግቶ እየሰራ ነው። ለኢኮኖሚ እድገቱና ለማህበራዊ ልማቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ ዜጋ ማፍራት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ መጠን፤ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ በማጠናከር ተገቢውን ተግባር እየተወጣ ነው።

በተለይ የግል ባለሃብቶች በትምህርቱ ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ ድጋፍ መስጠትና ስታንዳርዱን የጠበቀ ለመሆኑ ተገቢው ክትትልን የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ነው። በመንግስት የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ።

ያም ሆኖ ግን በመንግስት ጥረት ብቻ የትምህርት ጥራት ሊጠበቅ አይችልም። በመሆኑም ህብረተሰቡ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በመደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል።

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። በትምህርት ጥራቱ ዙሪያ ዛሬም ልክ እንደ ፈተናው መሰረቅ ዓይነት ያሉ ተግዳሮቶችን ማስወገድ ይገባልና።

እስካሁን ድረስ ባለው ሂደት ህብረተሰቡ የመማር ማስተማሩ አካል እንዲሆን በማድረግ ከጥራት አኳያ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት እየተደረገ ነው። ይህ ሁኔታም በቀሪዎቹ የዕቅዱ ዓመታት ተጠናክሮ ከቀጠለ በትምህርት ጥራት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከተሳትፎና ከተደራሽነት አኳያ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ጥቅል ተሳትፎን በ2ዐዐ7 ዓ.ም ካለበት 43 ነጥብ 2 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 80 በመቶ ለማድረስ፣ የአንደኛ ደረጃ (ከ1ኛ-8ኛ ክፍሎች) ንጥር ተሳትፎን አሁን ካለበት 92 በመቶ ወደ 100 በመቶ ከፍ ለማድረግ፣ የሴቶችንና የወንዶችን የትምህርት የተሳትፎ ልዩነትን  በሁሉም እርከኖች ወደ 1:1 (አንድ ለአንድ ምጣኔ) ለማድረስ፣ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸውን የ1ኛ ደረጃ (1-8) ትምህርት ህፃናት ጥቅል ተሳትፎን ካለበት 4 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 15 በመቶ ከፍ ለማድረግ ታስቦ እየተሰራ ነው።

የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን አሁን ካለበት 39 ነጥብ 3 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 74 ነጥብ 2 በመቶ ለማድረስ በማሰብ ስራው እየተከናወነ ሲሆን፤ በከተማ በገጠርና በክልሎች መካከል ያለውን የአጠቃላይ ትምህርት ተሳትፎ ምጣኔ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተሳትፎ ምጣኔን ወደ 95 በመቶ ለማድረስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን ለማስፋፋት በመንግስት፣ በግል ዘርፍና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተቋማትን የማስፋፋት ስራ ገቢራዊ በመሆን ላይ ይገኛል። በዚህም የተቋማቱን ቁጥር አሁን ካለበት አንድ ሺህ 329 ወደ 1 ሺህ 778 ለማሳደግና በዚህም በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ቢያንስ አንድ ተቋም እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ ነው። በውጤቱም የመደበኛ ሰልጣኞችን ቅበላ አሁን ካለበት 408 ሺህ 838 ወደ 598 ሺህ 729 ከፍ ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው።

የከፍተኛ ትምህርትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ቀደም ሲል ከነበሩት በተጨማሪ አስራ አንድ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን በመገንባት በቅድመ-ምረቃ መደበኛ ፕሮግራም 600 ሺህ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም እንዲኖራቸው ይደረጋል።

የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ብዛትም ወደ 63ሺ ከፍ እንዲል ግብ ተጥሎ ስራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ ነው። ይህም የሴት ተማሪዎች ተሳትፎን በቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 32 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 45 በመቶ ከፍ እንዲል፣ በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 22 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 35 በመቶ እንዲያድግ እንዲሁም በሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በ2007 ዓ.ም ከነበረበት 11 በመቶ በ2012 ዓ.ም ወደ 20 በመቶ እንዲያሳድግ ታስቦ መሰረታዊ ስራዎች ገቢራዊ እየተደረጉ ነው።

እነዚህ ጥረቶች በርግጠኝነት እንደሚሳኩ ሀገራችን ካለፈችባቸው ተሞክሮዎች ለመገንዘብ የሚያዳግቱ አይደሉም። ተሞክሮዎቹ ትናንት የነበረውን እጅግ አናሳና ጥቂቶች ብቻ የሚቋደሱትን የትምህርት ሽፋን ዛሬ ላይ ከሀገራችን ሶስት ሰዎች ውስጥ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ ያደረገ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ስር ነቀል ለውጥ ለሀገራችን ህዳሴ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ተማሪዎች ሀገራችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የልማት ስትራቴጂ ለምታደርገው ሽግግር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።

ትምህርት በተስፋፋና ተደራሽነቱም ባደገ ቁጥር ችግር ፈቺና የልማታችን ዋነኛ መሳሪያ መሆኑ አይቀርም። በአዲሱ ዓመት በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ተማሪ የሀገሩ ልማት ተስፋና ፋና ወጊ መሆኑን ተገንዝቦ በትምህርቱ ላይ በመበርታት የሀገሩን ራዕይ ለማሳካት መጣር እንዳለበት እንደ ዜጋ ለማሳሰብ እወዳለሁ። መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆን በመመኘት ጭምር።

 

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy