የሰላምና መረጋጋቱ ጉዳይ
የሰላምና መረጋጋቱ ጉዳይ
ይልቃል ፍርዱ
ኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው የድንበር ወሰን ግጭት መነሻነት ሁኔታው መልኩን እየቀየረ ሄዶ ያልተጠበቁና ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ድርጊቶች መፈጸማቸው ሕዝብና መንግስትን ከልብ ያሳዘነ ክስተት ሆኖአል፡፡ በመሰረቱ ጉዳዩን በእንጭጩ ለመቅጨት እንዲቻል በፌደራል መንግስቱ በኩል በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገው ነበር፡፡
ሰላም ይሰፍናል ሲባል ግጭቶቹ ወደባሰ ደረጃ በመሄዳቸው ከሚጠበቀው በላይ የዜጎችን ከቤትና ንብረታቸው መፈናቀል፣ ሞትንና ስደትን አስከትሎአል፤ ሁኔታው በሕዝቡ በኩል ከፍተኛ ቁጣ እንዲቀሰቀስም ምክንያት ሆኖአል፡፡ በዚህ አካባቢ የተከሰተው ችግር የሁለት ክልሎች ችግር ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ክልሎች የፌደራል መንግስቱንም በከፍተኛ ደረጃ የሚነካና የነካም ችግር በመሆኑ በልዩ ትኩረት የሚታይ ነው፡፡
የውጭ ንግድ ገቢና ወጪ የሚካሄድበት ከፍተኛ መተላለፊያ መስመር በመሆኑ በአካባቢው ያለው ሰላም መደፍረስ በኢኮኖሚውም ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮአል፡፡ አሁንም ቢሆን ሁኔታውን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ የመመለሱ ስራ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ በሁለቱም ክልሎች ያሉትን ሕዝቦች የሚወክሉ የሀገር ሽማግሌዎች ታዋቂ ሰዎች የኃይማኖት መሪዎች በጋራ በተዘጋጀ ኮንፈረንስ በጉዳዩ ዙሪያ መክረዋል፡፡ የሰላም መፍትሔም አስቀምጠዋል፡፡
የችግሩን መነሻ በመፈተሽ በግልጽ አውጥቶ በቀጣይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ማስቀመጥ ለሁሉም ይጠቅማል፡፡ አካባቢው ከጥንት ጀምሮ የጸጥታና የደሕንነት ስጋት የሚከሰትበት ቀይ መስመር ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በሁለቱ ክልሎች ድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ግዜያዊ አለመግባባት በመጠቀም ሌሎች የኢትዮጵያን ብሔራው ጥቅም የሚጻረሩ ሰላምና መረጋጋትዋን የማይፈልጉ ድንበር ዘለል ኃይሎች በውጭ ኃይሎች በመታገዝ መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኙ መስራት ግድ ይላል፡፡
እነዚህ ኃይሎች ዜጎችን እርስ በእርስ በማጋጨት የግጭቱ መጠንና ደረጃ እንዲሰፋ መልኩን ቀይሮ ወደአልተጠበቀ አቅጣጫ እንዲሄድ በዚህም ቀጣናው አጠቃላይ ትርምስ ውሰጥ እንዲወድቅ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም እንደሚሰሩና በሽፋን እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡
ይህ ጉዳይ የሁለቱ ክልሎች ጉዳይ ብቻ ተደርጎ ሊታይ አይችልም፤ አይደለምም፡፡ ጉዳዩ የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮና መረጋጋትን በማደፍረስ ሕዝቡን እርስ በእርሱ እንዲጋጭ በዚህም ወደከፋ ሁኔታ እንዲለወጥ በማድረግ ብቻ አያበቃም፡፡ በተጨባጭ እንደታየው የሀገሪቱን አጠቃላይ የወጨና የገቢ የንግድ መስመር ከውጭ ሀገራት ወደሀገር ቤት የሚገቡት የተለያዩ ሸቀጦች የውጭ ምርቶች የግንባታ እቃዎች ማሽነሪዎች ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ሌሎችም ከውጭ ወደውስጥ የሚገቡበት የሀገር ውስጥ ምርቶችም ወደውጭ ገበያ እንዲደርሱ የሚተላለፉበት ዋነኛ መስመር ነው፡፡
ግጭቱን የበለጠ ለማቀጣጠል በስውር የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች ከድንበር ግጭቱ ሌላ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የማሽመድመድ፣ ዝውውሩን፣ ግብይቱን፣ የገቢና ወጭ ንግዱን ለመግታት በዚህም ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ሙሉ በሙሉ ሽባ ለማድረግ አቅደው አስቀድሞ በተነደፈ ስትራቴጂ የሚመሩ ስለሆነ ሀገርና ሕዝብን በከፍተኛ ደረጃ የመጉዳት ሴራ ከጀርባው እንዳለም የሁለቱም ክልሎች ኃላፊዎች ሕዝቡና መንግስትም በውል ሊረዳው ይገባል፡፡ እስከአሁን ግልጽ ሁኖ ካልተነበበልንም በዚህ መልኩ ማየቱም ተገቢ ነው፡፡
ቀጣናው የኢኮኖሚ ቁልፍ መስመር ስለሆነ ግጭቱን ለማስፋትና በቀጣይነት መልኩን እየቀየረ እንዲሄድ የማድረጉ ስራ ከክልሎቹ ውጪ ባሉ ኃይሎች ጭምር የሚመራ ነው የሚል የበርካቶች አስተያየትና ስጋት አለና መንግስት ይህን ታሳቢ ያደረገ ስራም መስራት አለበት፡፡ ሕዝቡ ውሰጥ ተመሳስለው በመግባትና በመመሸግ የጥፋት ስምሪት ወስደው የሚሰሩ የግብጽና የአስመራው ተላላኪዎች እንደሚኖሩበት ፍንጭዎች በመታየት መሆናቸውም እንደዛው፡፡
ቀጠናው የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ ከቀድሞ ጀምሮ ሲንቀሳቀሱበት የነበረ አደገኛ ቀጣና መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዚህ ቀጠና ሰርገው በመግባት በሕዝቡ ውስጥ መሽገው ጥፋት ሲያደርሱ የነበሩ የኦብነግና የኦነግ ኃይሎችን እንዲሁም የአልኢትሀድ፣ አልኢስላሚያና የአልሻባብ ኃይሎችን ከአካባቢው ጠራርጎ ለማስወጣት አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፍል ነው አካባቢውን የሰላም ቀጣና በማድረግ ወደልማት እንዲገባ ያደረገው፡፡
የኦሮሞውና የኢትዮጵያ ሶማሌው ሕዝብ በጋራ ወሰናቸው አካባቢ ዛሬ ሳይሆን ለብዙ ሺህ ዘመናት አብረው በፍቅር በጋራና በሕብረት ኖረዋል፤ የአንዱን ቋንቋ ሌላው ይናገራል፤ ተጋብተዋል፤ ተዋልደዋልም፡፡ አልፎ አልፎ በድንበሩ አካባቢዎች ይፈጠሩ የነበሩ አለመግባባቶችም በሽማግሌዎችና በመንግስት በቀላሉ ይፈቱ እንደነበር ነው የሚታወቀው፡፡ የአሁኑ ግጭት እንዴት ተፈጠረ፣ ለምንስ ይሄን ያህል ገዘፈ፤ እንዴትስ አድማሱን አሰፋ፤ ለምንስ፣ ጥቃቶች፣ ወረራዎችና የተኩስ ልውውጦች ተካሄዱ፣ ሕዝቡንስ የጋራ ከሆነው ሀገሩ በድንበር አለመግባባት ስም አካባቢውን ለቀህ ከነቤተሰብህ ውጣ ለማለትስ እንዴት ታሰበ፣ ተደፈረስ? የሚሉት ጥያቄዎች ሁሉ ገፊ ምክንያታቸው በአስቸኳይ ተጠንቶና ተመርምሮ መታወቅ አለበት፡፡
የሁለቱ ክልሎች ኃላፊዎች ሊፈቱት ይችሉት የነበረው ችግር አድማሱን ያሰፋበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? የሚሉትን ጉዳዮች መንግስት እየፈተሸው እንደሚገኝ ይሰማል፡፡ ጥሩ ነው፤ ግን የፍጥነቱስ ጉዳይ። በእርግጥ ጉዳዩ የውስጥ ችግር ስለሆነ በቀላሉ ይፈቱታል በሚል ለክልሎቹ ቀደም ሲል ሙሉ በሙሉ አልተተወም፡፡ በፌደራል ደረጃ መንግስት ባለስልጣናትን በመላክ አነጋግሮአል፤ አወያይቶአል፡፡ ጉዳዩም እልባት ያገኘ መስሎ ነበር፡፡ አገረሸበትና መልኩን በመቀየር አሁን ያለበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደረሰ እንጂ፡፡
በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሶማሌውና ኦሮሞው ለረዥም ዘመናት አብረው የኖሩ፣ የተዋለዱ፣ የተጋቡ፣ ብዙ ትውልዶችን ያሳለፉ፣ የሚጋሩት ብዙ ነገሮችም ያሉዋቸው ናቸው፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ የተፈጠረው አስደንጋጭ ክስተት፤ ሕዝብን ከመኖሪያ ቀኤው የማፈናቀል ድርጊት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስቆጣና ከልብም ያሳዘነ ድርጊት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ በሚገባ ሊያጤነው ይገባል፡፡ በሁለቱም ወገን ተጎጂ የሆኑት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ሁኔታው መፈጠርም ሆነ መሆን የሌለበት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ግጭቱን ከማረጋጋት ይልቅ የበለጠ ጥፋት እንዲከሰት ሲቀሰቅሱ የነበሩ ክፍሎችንም በገሀድ ማየት ተችሎአል፡፡
ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ከመስራት ይልቅ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናቆር በተለያየ መልኩ ሲሰሩ የነበሩትን ክፍሎች የጎሳ ግጭት እንዲፈጠር የሚያራግቡ ብሎገሮችና የፌስቡክ ቅጥረኞችን ሕዝቡ በስፋት አይቶአል፡፡ የእነዚህ ክፍሎች አራጋቢነት ለሀገር፣ ለህዝብና መንግስት አይበጅም፡፡ ለእስከአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ሕዝብና መንግስት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡
የሁለቱንም ክልሎች ታዋቂ ሰዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ የሕዝቡን ተዋካዮች ያካተተ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ተካሂዶአል፤ ተግባራዊ ለውጥ እንደሚያመጣም እንጠብቃለን፡፡ ፍጹም ሰላም የሰፈነበት መፍትሄ እንደሚያስገኝ አምነን ተግባራዊነቱን እንጠብቃለን፡፡ ተወያይተውበት በጋራ በመምከር ዘላቂነት ያለው ሰላም እንደሚያሰፍኑ፤ የክልሉ ሁኔታዎችም ቀድሞ ወደነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ እንደሚመለሱ ሁሉም ዜጋ ይጠብቃል፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያ!!!