Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና መሠረት

0 660

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና መሠረት

                                                      ታዬ ከበደ

የአገራችን ፌዴራሊዝም የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና መሰረት ነው። በዚህም ኢትዮጵያ በእስካሁኑ ሂደት ስኬታማ መሆን ችላለች። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመላ አገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን እንዲኖር፣ ልማትና ብልዕግና እንዲረጋገጥ እንዲሁም የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ ወሳኝ የድል መንገዶችን ተጉዘዋል። እነዚህ ድሎቻቸው የአገራችን ከፍታ አመላካቾች ናቸው።

በፌዴራል ሥርዓቱ አማካኝነት አስተማማኝ ሰላም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸውን ማረጋገጥ ችሏል። ይህም የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ የሆነውን ሰላም በመመለስ ለትግላቸው እውቅና በመስጠት ጥያዌዎቻቸውን መመለስ ችለዋል።

በሀገራችን ዕውን እየሆነ ያለው ስርዓት ሰላምን ማረጋገጥ በመቻሉ፤ በማህበራዊ መስተጋብሮች ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝና የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል።

ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ፌዴራሊዝም የጎላ ሚና እንደሚጫወት እምነትን አስይዞ በአዲስ የአስተሳሰብ መንፈስ ወደ ልማት ጎዳና መትመም እንዲችሉ አድርጓቸዋል።  

እናም ስርዓቱ እነዚህን ሁሉ ውጣ ውረዶችን አልፎ ሰላምን ዕውን ያደረገ፣ ልማትን ያረጋገጠና በዚህም የህዝቦችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ዕውን ያደረገ እንዲሁም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታን መገንባት ችሏል።

ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩት ሁከትና ግጭቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ይመስሉኛል።

ያም ሆኖ ህዝቡ በሰላሙ ላይ ስለማይደራደር ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር እንዳይኖር አድርጓል። ምንም እንኳን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው የሚነቀሳቀሱ ሆነዋል።

በዚህም በመልካም አስተዳደርና በሙስና ህዝቡን ሲያማርሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሃይሎች የፈጠሩት ምሬት ከትምክህትና ከጥበት አራማጆች አጀንዳ ጋር ተዳምሮ የሀገራችንን ሰላም ማወኩ የቅርብ ጊዜ ትውሰታችን ነው።

እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ። የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሔር ብቻ ልዕለ ኃያል ነው ብሎ ያምናል። እንዲሁም ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየነው ብሎ ከማሰብ በተጨማሪ ‘ሁሌም ለመግዛት የተፈጠርኩ ነኝ’ በማለት የሚያምን ነው።

በአንፃሩም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራ እና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ፣ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ የመቁጠር አባዜ የተጠናወተው ነው። የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም የመቀበል ተፈጥሮ የለውም። እናም በተቻለው መጠን ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን ቀዳዳዎችን በሙሉ ሲጠቀምባቸው ተመልክተነዋል።

የትምክህት ሃይሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ ከህዝቦች አንድነት ይልቅ የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው።

የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰው ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖርን የእሬት ያህል ቆጥሮ የሚጎመዝዘው ነው። ኋላ ቀርነት መገለጫ ነው ሊባልም ይችላል።

ያም ሆኖ የአገራችን ህዝቦች የእነዚህን አደናቋሪዎች ልፈፋ ወደ ጎን በማለት ሰላማቸውን ሊያስጠብቁ ችለዋል። የሰላማቸው መረጋገጥ ደግሞ በነደፉት የልማት ዕቅዶች በመጓዝ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትን ማስመዝገብ ችለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል፡፡ መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው፡፡

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡

እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተ ከብረት የጠነከረ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ያሰገኘ ነው፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የትግል ምዕራፍ በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ያጸደቁት ህገ – መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው፡፡

በአገራችን አዲስ ስርዓት ዕውን ከሆነ በኋላ ህገ መንግስቱ ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ሀገራችንና ህዝቦቿ በተለያዩ መስኮች እጅግ ውጤታማ ተግባር አከናውነዋል፡፡ እነዚህን ውጤቶች አቅቦ ከመጓዝና ለአዳዲስ ድሎች ከመብቃት አኳያም፤ በአሁኑ ወቅት መንግስትና መላው ህዝብ በላቀ ቁርጠኝነት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህም የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገፅታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለወጥ ላይ ይገኛል፤ ሂደቱም እጅግ በተጋጋለ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ እነዚህ ከላይ በአጭሩ ለመጥቀስ የሞከርኳቸው እውነታዎች ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት የሰላማችን፣ የልማታችንና የብልፅግናችን መሠረት መሆኑን ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy