Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቅራኔ ምክንያቶችን ከስረ- መሰረቱ የዘጋ ስርዓት!

0 290

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቅራኔ ምክንያቶችን ከስረ- መሰረቱ የዘጋ ስርዓት!

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ስርዓት በህዝቦች መካከል ቅራኔ ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ከስረ-መሰረታቸው መዝጋት የቻለ ነው። ምንም እንኳን እንደ ማንኛውም ጀማሪ ስርዓት አንዳንዴ ሊፈጠሩ በሚችሉ የአፈፃፀም ግድፈቶች ሳቢያ ጊዜያዊ ችግሮች ሊያጋጥሙ ቢችሉም፤ ስርዓቱ ችግሮቹን ከመሰረታቸው ለዘለቄታው እየፈታ የመጣና ከፍተኛ ተሞክሮን ማዳበር የቻለ ነው።

ኢትዮጵያ በምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት አያሌ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለች ሀገር ናት። ህዝቦቿም የውጤቶቹ ተቋዳሽ ለመሆን በቅተዋል። ይሁንና የቀድሞው ሥርዓት ተመልሶ ይመጣ ዘንድ አንዳንድ ወገኖች ሰላሙን አግኝቶ ኑሮውን ለመለወጥ የሚጣጣረውን ዜጋ ወደ ኋላ ለመጎተት የማይቀበጣጥሩት የለም።

አስተማማኝነቱን በተግባር በማረጋገጥ ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጥቆር ስራ የተጠመዱት እነዚህ ፅንፈኞችና ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ዕድገትና አንድነት ሰላም ነስቷቸው የማይወረውሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም። ይሁንና ሃቁን ይበልጥ ገላልጦ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ሀገርን አዋርዶና ህዝብን አሸማቅቆ ዜጎችን ለተመፅዋችነት የዳረገው ብሎም ለዘመናት ከጫንቃቸው ላይ አልወርድ ብሎ ከኖረውና ድህነት ከተሰኘው ክፉ ጠላት ጋር ግልፅ ውጊያ ገጥመው ውጤት እያስመዘገቡ ያሉት በዚሁ ሥርዓት ውስጥ ነው።

በስርዓቱ ውስጥ ዜጎች በመንግሥት በተነደፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል። ከድህነት አዙሪት ተላቀው ወደ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገትም ተሸጋግረዋል። ውጤቱን ከማጣጣም ባለፈ የህዳሴያቸውን ፈር ቀዳጅ መንገድ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገርና የመጻፍ፣ ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በነፃነት የመግለፅ መብቶቻቸን እንዲጎናፀፉ አድርጓቸዋል። ርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ በመሆኑ ይህ ውጤት ከተገኘ 26 ዓመታትን ተሻግረዋል።

በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አይመስለኝም—የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠው እንጂ። ያም ሆኖ ግን እነርሱ ያሻቸውን ቢሉም የሆነው ሃቅ አሁን ከ26 ዓመት በኋላ ያለው ዓለም ያደነቀው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ነው።

ለነገሩ የሀገራችን ህዘቦች የሚከተሉት የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

ከዚህ ዕውነታ የሚነሳው የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ- መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው።

ይህ የሀገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለዚህም ይመስለኛል— ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችብን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

ይህ ውሳኔያቸውም ለዛሬው እነርሱነታቸው ያበቃቸው ከመሆኑም በላይ፤ የፌዴራል ስርዓቱ አንዳንድ ወገኖችና ፅንፈኞች ሃቁን ካለመገንዘብ አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሚሉት ዓይነት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አለመሆኑንም አሳይተዋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ አንድነታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ ስለተገነባ ነው።

ለነገሩ አንዳንዶቹ ይህን ሃቅ እያዩ እንኳን በማንኛው በማደግ ላይ በሚገኝ ሀገር ውሰጥ እንደሚፈጠረው በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ነባራዊ ክሰተቶችን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ በሚሉ የፌዴራል ሥርዓቱ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ከሽፏል እስከማለት ደርሰዋል። በድፍረት መፃፋቸውንም አስታውሳለሁ።

ያም ሆኖ ግን በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ የማይችል ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ይመስለኛል። እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየጎለበተ እና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት በእኛ ሀገር ውስጥ ቀርቶ፤ በስልጣኔ በገፉ ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ግጭት መኖሩ ነባራዊ ክሰተት ነው።

በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚመላለሰው የሰው ልጅ ቀርቶ ህይወት የሌላቸው ግዑዛን ነገሮችም በተፈጥሮ እንቅስቃሴ ሳቢያ ሊጋጩ ይችላሉ። ይሁንና ስርዓቱ እንዲህ ዓይነት ነባራዊ ግጭቶችን የሚፈታበት አሰራር ያለው ነው።

ከዚህ አኳያ በቅርቡ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የድንበር ውዝግብ ሁለቱ ክልሎች ስራዐቱ በሚፈቅደው መርህ መሰረት ችግሮቻቸውን መፍታታቸውን ማንሳት ይቻላል። ይህም ስርዓቱ ማናቸውንም ችግሮች መፍታት የሚችለበትን አቅምና ተሞክሮ ማዳበሩን የሚያሳይ ነው።

ርግጥ ከሰው ልጅ ግጭቶች አኳያ በዓለማችን ላይ የተፈጥሮ ሃብት እጥረት መኖሩ እንደ መንስዔ የሚታይ ነው። በየትኛውም ሀገር ውስጥ የተፈጥሮ ሃብት እጥረት መኖሩ አሌ አይባልም። ሀገራችንም ከዚህ የተፈጥሮ ዕውነታ ልትርቅ አትችልም— እንደ ማንኛውም የዓለማችን ክፍል የተፈጥሮ ሃብት እጥረት ያለባት መሆኑ አይካድም።

በመሆኑም ግጭት ትናንትም ይሁን ዛሬ እንዲሁም ነገ መኖሩ ያለና የሚኖር ጉዳይ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል። ዋነኛው ጉዳይ ግጭቱ የሀገርንና የህዝብን ሰላማዊ ህይወት የማይበርዝ መሆኑን መገንዘቡ ላይ ነው። በአፋጣኝም መፍትሔ መሰጠቱ ላይ ነው።

ከዚህ አኳያ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ማድረግ ችሏል።

ይሁንና ያለፉት ስርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሚቀየሩ አይደሉም። ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን የሚጠይቁ ናቸው። ታዲያ መንግስት ይህን ዕውን ለማድረግ የህዝቦች አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ ተመርኩዞ ተግባሩን በብቃት እየተወጣ ነው።

ስርዓቱ ላለፉት 26 ዓመታት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በአስተማማኝና በሰከነ ሁኔታ በመፍታት ተሞክሮን አዳብሯል። አንዱ ክልል ከሌላው ጋር በወሰን መካለል ሳቢያ የሚፈጥራቸውን ችግሮች እየፈታ መጥቷል። ከዚህ አኳያ በኦሮሚያና በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል፣ በአማራና በትግራይ…ወዘተ. ክልሎች መካከል የነበሩ የወሰን መካለል ችግሮችን መፍታት መቻሉን መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ እውነታዎች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር፤ ስርዓቱ የሚከተላቸው አሰራሮች የቅራኔ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዩችን ከስረ-መሰረታቸው የዘጋ መሆኑን ነው። እናም ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ለቅራኔ በር የማይከፍት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy