Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የበርካታ ልዩነቶቻችን ማስቻያ መስመር

0 428

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የበርካታ ልዩነቶቻችን ማስቻያ መስመር

                                                           ዘአማን በላይ

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት በሀገራችን ውስጥ ያሉትን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ልዩነቶች አቻችሎና አክብሮ በጋራ በአንድነት ለአንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ዓላማዎች እንዲኖሩ ያደረገ ነው። ልዩነቶቹን በማስተናገድ ለጋራ ዓላማ ተባብረው እንዲቆሙ የሚያስችላቸውም ነው። ስርዓቱ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም፤ በጋራ ይሁንታና ፈቃድ ባቋቋሙት ፌዴራላዊ ስርዓት ልየነቶችን የማስቻያ መስመር ሆኖ እያገለገላቸው ይገኛል።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በጋራ መኖር የሚችሉበትን ባህል እያዳበሩ መጥተዋል። በብዙ ቋንቋዎች መናገር ሳያስማማ እንደሚቀር ይመስላቸው ለነበሩ ሰዎች አሁን በ75 ቋንቋዎች እየተነጋገሩ መግባባት እንደሚቻል በኢትዮጵያ ታይቷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ብዙ እምነቶችና የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት የሚከተሉ ሆነው ሲያበቁ በተግባር ግን ተከባብረው መኖር እንደሚቻል ያሳዩ የፌዴራል ስርዓቱ ልዩ መለያ ሆነዋል ማለት ይቻላል።

እርግጥም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የሰፈረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት 25 ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ ያሳየ ይመስለኛል።

ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ብዝሃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ሆኗል። ይህም ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዝሃነትን አስመልክተው ይራመዱ የነበሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውሰጥ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሊሆኑ ችለዋል። አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

ዛሬ በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፤ የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል—በጊዜ ሂደት የነበሩት አስተሳሰቦች ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ እየተመዘኑ በመክሰም ላይ መሆናቸውን መናገር የሚቻል ይመስለኛል።  

እርግጥ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በወደቀበት ማግስት የነበሩት የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳንዶቹ ያነገቡት ዓላማ መገንጠልን እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም አብሮ በመኖር ሂደት የተገኘ ጥቅም እያደገና እየሰፋ ስለመጣ የመገንጠል አስተሳሰብ ማኅበረሰባዊ መሰረት አለው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም። ለነገሩ አንድ ህዝብ መብቶቹ ተከበረው በጋራ ተጠቃሚነት ውስጥ እስካለ ድረስ ስለ መገንጠል ማሰቡ ሚዛናዊ ዕይታ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

ያም ሆኖ የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው አፈ ታሪክ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ህዝቦች ብዝሃነት ከግምት ውስጥ ያላስገባም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብዝኃነት የሀገራችን ጉልበትና አቅም ሆኗል። ሀገራችን ውስጥ ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በተናጠል ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ በጋራ የላቀ ጥቅም እንደሚያገኙ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ማረጋገጥ ችለዋል።

ህብረታቸውን የሚፈታተንና ሰላማቸውን የሚያናጋ ኃይል በጋራ ታግለው ማሸነፋቸው የዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅ ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የታየውን የብዝሃነት ህብረትን እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነት ብቻ መጥቀሱ ከበቂ በላይ ማሳያዎች ይመስሉኛል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ነገር ግን እንደ አንድ ማኅበረሰብ በአንድነት ለልማትና ዕድገት የሚነሳ ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። አዎ! ብዝሃነታችን ሀገራችን በዓለም ፊት ያላትን ገፅታ እየቀየረ ነው።

ምንም እንኳን አንዳንዶች በብሔርና በጎሣ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም፤ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን ከእነርሱ ምልከታ የተለየን ሁኔታ ነው። ብዝሃነት የመጪው ዘመን ዕድላችን በር መክፈቻ ሆኗል። ሆኖም በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል።

በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝሃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል። በዚህም ብዝሃነት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ሊሆን ችሏል።

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የብዝሃነት መሰረቶች የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሶሶና ማገር ናቸው። መሰረቶቹም በስርዓቱ የፖለቲካ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ናቸው።  በኢፌዴሪ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አካሄድም ይህንኑ ሃቅ የሚደግፍ ነው።

የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት በብዝሃነት ውስጥ ላሉ ማንነቶች የሰጠው መብት ከብዙ ፌዴሬሽኖች ጋር ሲነጻጸር የላቀና ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል።

የስርዓቱ የማንነቶች አያያዝ ‘ብዝሃነት ዕድል ነው’ ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ ይመነጫል። ይህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አጠቃላይ መንፈስና በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ እንዲደነገግ ተደርጓል።

እርግጥ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የህገ መንግስቱ መግቢያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በብዝሃነታቸው ውስጥ ያሏቸውን ልዩ ልዩ የማንነት መገለጫዎች አምነውና አክብረው ለመኖር፣ ካሳለፉት ታሪክ የወረሱትን መልካም ትስስር ተጠቅመው ለወደፊት አንድ የጋራ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቃል መግባታቸውን እያረጋገጡ ነው።

ርግጥ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መበት አለው። እንዲሁም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዲረጋገጥለት ተደርጓል።

የማንነታችን ልዩነት በብዝሃነታችን ውስጥ የምንደምቅበት አውድ እንጂ ለመለያየታችን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል በግልፅ ተቀምጧል። ስርዓቱ የህዝቦችን ብዝሃነት በማክበር ልዩነቶችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው።

በዚህ መነሻነትም የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ተደርጓል። ልዩነቶች ተቻችለው አንዱ ሌላኛውን በማክበር፣ የህዝቦች ባህላዊ ትውፊቶች የሌላውም መድመቂያ መሆናቸውን በማመን የጋራ ቤትን በጋራ ተጋግዞ የማቆም ስራዎችን ገቢራዊ ማድረግ ችለዋል።

ይህ ህብረ-ብሔራዊነት የህዝቦች ጌጥ ከመሆን በዘለለ፤ ሀገራቸው ለጀመረችው የህዳሴ ጉዞ መሳለጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። እናም ስርዓቱን አክብሮ በእርሱ ሰር መሰባሰብ ጠቀሜታው ይህን ያህል መሆኑን በመገንዘብ ለስርዓቱ ዘብ መቆም ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ይመስለኛል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy