Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብር ምንዛሪ መቀነስና አንድምታው

0 282

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብር ምንዛሪ መቀነስና አንድምታው

ዳዊት ምትኩ

መንግስት በቅርቡ የብር ምንዛሪ ከዶላር ጋር ያለው ለውጥ በ15 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል። መንግስት ይህ እንዲሆን ያደረገው በቀጣይ የአገሪቱን ዕድገት ማስቀጠል እንደሚቻል በማመኑ ነው። ምንም እንኳን የብር ምንዛሪ መጠን እንዲቀንስ በመደረጉ የኑሮ ውድነት ሊከሰት ቢችልም፣ መንግስት በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ህዝቡ እንዳይጎዳ የማድረግ ስራዎችን ከምንግዜውም በላይ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚተገብር ገልጿል።

አሁን ባለው መረጃ መሰረት ቀደም ሲል አንድ ዶላር በባንክ በአማካይ ሲመነዘርበት የነበረው 23 ነጥብ 4177 ብር ወደ 26 ነጥብ 93 ብር ከፍ ብሏል። ይህ የዶላር መግዣ ዋጋ መነሻው ነው። ሲሸጥ ደግሞ 27 ከ48 ገደማ ሆኗል።

መንግስት ይህንን እርምጃ ሲወስድ በዋነኝነት እየተዳከመ ያለውን የኤክስፖርት ገበያ ለማጠናከር መሆኑ ይታወቃል። በአንድ አገር ውስጥ ኤክስፖርት ምርት ሊጠናከር ካልቻለ በውጭ ምንዛሬ ረገድ ችግር መግጠሙ አይቀርም። ይህም አገሪቱ ለልማት ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከውጭ እንዳታስገባ ያደርጋል። በተለይ አገራችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የያዘችውን ትልም ለማሳካት እንዲህ ዓይነቶቹን እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ፈጣን ዕድገታችን፣ የመሠረተ ልማት ኘሮግራሞቻችንና የግል ኢንቨስትመንትና ንግድ ሥራዎች የሚፈልጉትን የውጪ ምንዛሪ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማቅረብ እና በውጪ ዕርዳታና ብድር ያለን ጥገኝነት ለመቀነስ እንዲቻል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን እቅድ ተይዟል፡፡

ኤክስፖርት ላይ ለመረባረብ የታቀደው ኢኮኖሚያችን በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይታጠር በሰፊው የዓለም ገበያ ላይ ተመስርቶ በፍጥነት እንዲያድግ ለማድረግም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዓለም ገበያ ገብተን ምርቶቻችንን በስፋት ለመሸጥ ያቀድነው ተወዳዳሪነታችንን ማጐልበት ያስፈልጋል፡፡ እስቲ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑትን በጥቂቱ እንመልከታቸው፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ በ2002 በጀት ዓመት መጨረሻ 2 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የሸቀጦች የኤክስፖርት ገቢ በ2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ከ5-8 ቢልዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ግብ ይዘን ተንቀሳቅሰናል፡፡ በዕቅዱ የመጀመሪያው ዓመት በዋናነት የዓለም የሸቀጦች ዋጋ በመጨመሩ ሳቢያ የሸቀጦች ኤክስፖርት ገቢያችን ከ37 በመቶ በላይ ሲያድግ በ2004 ደግሞ በ15 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ይሁን እንጂ የኤክስፖርት ገቢው በ2005 በ3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በ2006 በመጠኑ አገግሞ በዓመቱ 3.2 ቢልዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ተገኝቷል፡፡ የ2007 የኤክስፖርት አፈፃፀምም ከሸቀጦች ኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ በ2006 ከተገኘው ገቢ እንደማይዘል ይገመታል፡፡

በመሆኑም የሸቀጦች የኤክስፖርት አፈፃፀም በዕቅድ ተይዞ ከነበረው እጅግ ያነሰ እንደሆነ በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡ ከሸቀጦች ኤክስፖርት የተገኘው ገቢ የኢምፖርት መጠን የመሸፈን አቅምም እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በ2006 ከኤክስፖርት የውጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሸቀጦች ገቢ ንግድን የውጪ ምንዛሪ ፍላጐት መሸፈን የቻለው ከ20 በመቶ በታች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢኮኖሚያችን በፍጥነት እያደገ ባለበት በኤክስፖርትና በኢምፖርት መካከል ክፍተት መኖሩ የሚጠበቅ ቢሆንም ጉድለቱ እየሰፋ መጥቶ የተጠቀሰው ደረጃ ላይ መድረሱ ግን አሳሳቢ ነው፡፡ በእነዚያ ዓመታት የታየው ደካማ የኤክስፖርት አፈፃፀም አስተማማኝ የውጪ ምንዛሪ ግኝት በማረጋገጥ ለፈጣን ዕድገታችን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችና ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ዕድገታችን ለማስቀጠል አና ከውጪ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ ማነቆ ሆኗል፡፡

በግሉ ዘርፍ የሚካሄዱ ሰፋፊ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደዚሁም በመንግስት የሚካሄዱ ትልልቅ የመሠረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የማህበራዊ ልማት ኘሮግራሞች ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የሚፈልጉ በመሆናቸው የኤክስፖርት መዳከም እየተፋጠነ ያለውን ልማት ሊያደናቅፍ እነደሚችልም ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

እርግጥ ይህ የሆነው ለኤክስፖርት ገቢ አፈፃፀም መዳከም ዋናው ምክንያት የማምረት አቅማችን በሚፈለገው ደረጃ አለማደግና በዚህም ምክንያት የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ሸቀጦች በከፍተኛ መጠን፣ በተለያየ ዓይነትና በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ነው፡፡

ሆኖም አንዳንድ የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ሸቀጦች የተወሰነ የመጠን ጭማሪ ያሳዩ ቢሆንም ታቅዶ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዕቅድ ዘመኑ ወደ 200ሺ ቶን የሚጠጋ ቡና ኤክስፖርት ለማድረግ የተቻለ ቢሆንም በ2007 ይደረስበታል ተብሎ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ሲሶ ያህል ብቻ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የአበባ ምርት ኤክስፖርት ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ተይዞ የነበረው ግብ እና አፈፃፀሙ ፍፁም የማይቀራረቡ ነበሩ፡፡

በግብርናው ዘርፍ የኤክስፖርት ሰብሎች የሆኑት አበባ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡናና ሰሊጥ እንዲሁም የጥራጥሬ ሰብሎች ኤክስፖርት የተደረገው መጠን ይደረጋል ተብሎ ከታቀደው በእጅጉ ያነሰናበማኑፋክቸሪንግ ነባሮች ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ አቅማቸውና በጥራት እንዲያመርቱና በተጨማሪምአዳዲስ ኢንቨስትመንትን በስፋትና በጥራት መልምሎ ወደ ሥራ ማስገባት በታቀደው ልክባለመቻሉ ለኤክስፖርት የማምረት አቅማችን ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በግብርናም ምርታማነቱ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ ለኤክስፖርት የምናቀርባቸው የግብርና ውጤቶች በመጠን፣ በጥራትና በዓይነት ውሱን ሆነው ቆይተዋል፡፡

እናም እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር ያስፈልጋል፡፡ የኤክስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም የዕድገታችንን ዘላቂነት መረጋገጥ የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ለኤክስፖርቱ የሚደግፉ ግብዓቶችን ከውጭ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የብር መጠንን በመቀነስ ኤክስፖርትን ማበረታታት ይገባል፡፡

በመሆኑም በሁለተኛው ዘመን በኤክስፖርት ዘርፍ እመርታ ማምጣት ተደጋግሞ እንደተባለው የሞት ሽረት ጉዳይ ተደርጐ የተያዘ እቅድ በመሆኑ ማናቸውንም ዓይነቶች መስዋዕተነት መክፈል ይገባል፡፡

በእቅዱ ላይ የተቀመጡትን የመፍትሔ ስትራቴጂዎች ሳያንጠባጥቡ ለመፈፀም የሚቻለው ኤክስፖርት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው በሚል መንፈስ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው፡፡ ስለሆነም የብር የምንዛሬ ለውጥ ማድረግ የዚህ መፍትሐሔ አንዱ አካል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy