Artcles

የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ሚና

By Admin

October 03, 2017

የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ሚና

                                                      ደስታ ኃይሉ

የአገራችን የዛሬ ተማሪዎች የነገ ሐብቶች ናቸው፡፡ ተማሪዎች በተለያዩ ወቅቶች በምግባረ ሰናይ ተግባሮች ውስጥ ሲሳተፉ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በክረምቱ ወቅት በበጎ ፈቃደኝነት ካደረጉት ርብርብ መገንዘብ የሚቻለው በሌላው ዘርፍም ተጨባጭ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት ላይ በንቃት ቢሳተፉ ተፈላጊውን ውጤት ማምጣታቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡

ባለፉት ሥርዓቶች ለትምህርት ተቋማት መስፋፋትና ለፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት  የተሰጠ ትኩረት አልነበረም፡፡ ከታች እስከ ላይ ድረስ የነበሩት የትምህርት ተቋማት ውስን ከመሆናቸውም በላይ የተቋቋሙት በከተሞች ብቻ ነበር፡፡

ባለፉት ጊዜያት ህዝቡ ከውጭው ዓለም እንዲቸረው ይጠብቅ የነበረው የእህል አሊያም የገንዘብ ድጋፍና ዕርዳታን ብቻ አለመሆኑን ነው። በሀገራችን በተለያዩ ደረጃዎች በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ውስጥ የእውቀት ድጋፎችንም የሚሻ ነበር። የዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሀገራችን ውስጥ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ በእውቀትና ክህሎት የታነፀ በቂ የሰው ሃይል ሊፈራ አለመቻሉ እንደሆነ አያከራክርም።

እዚህ ላይ በልማቱ መስክ ላይ ተሰማርቶ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት የሚችል የሰለጠነ የሰው ሃይል በጥራትና በበቂ ሁኔታ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ባለፉት ጊዜያት በህብረተሰባችን ውስጥ ይንፀባረቅ ስለነበረው አንድ እውነታ በማሳያነት ላንሳ።

ባለፉት ጊዜያት በሃገራችን በተለያዩ ደረጃዎች ይካሄዱ የነበሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተን አሊያም በመገናኛ ብዙሃን ተከታትለናቸው ይሆናል። ከእነዚህም መካከል በግዙፍነታቸው አልያም በዘመናዊነታቸው እንግዳ የሆኑብን የሚታጡ አይመስለኝም።

ያኔ በአገሪቱ አንድም የግል ዩኒቨርስቲ ሆነ ኮሌጅ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት  የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡

ይህም ዛሬ ከሶስቱ ኢትዮጵያዊ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህፃናት የምግብ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

የወጣቱን የትምህርት እድል ለማስፋት የግል የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ተደርጓል። ይህ አገሪቱ ለልማት የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ የተማረና ብቃት ያለው ባለሙያ በሌለበት አገር ዘላቂ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ነው፡፡ በዚህም አገራችን የሚሊየሙን የልማት ግብ ከማሳካት ባሻገር፤ ለጥራት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው፡፡  

ዛሬ በውጭ ባለሙያዎች የሚከናወን ስራ በእጅጉ እየቀነሰ ነው። በልማቱ ስራ ላይ በወሳኝ ጉዳዮች ዙሪያ  የውጭ ሙያተኞች ዕውቀት ጥገኛ ለመሆን የተገደድነውም በዚሁ ሳቢያ እንጂ፤ ሀገሪቱ ከዓለም ገበያ ዕውቀት ለመግዛት የምታፈሰው የገንዘብ አቅም ስለነበራት አልነበረም።

ይሁን እንጂ ይህ ለረጅም ጊዜያት ከእህልና ገንዘብ ባልተናነሰ መልኩ የእውቀት ጥገኛ ሆነን የተጓዝንበት ምዕራፍ መፍትሄ ሳይበጅለት አልቀጠለም። ሀገራችን ውስጥ ዕውን በሆነው ልማታዊና ዴሞክራሲ መንግስት አማካኝነት ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ ወደ አዲስ አስተሳሰብና የዕውቀት ሽግግር ለመጓዛችን በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም በትምህርት አመራር፣ በመምህራን ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ማሻሻል፣ በት/ቤቶች ማሻሻል እና በአይሲቲ ዙሪያ ሰፋፊ ተግባራት መከናወን ቢችሉም፤ እነዚህን ማሻሻያዎች አጠናክሮ በመተግበር እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት መሻሻል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ መስራትን ይጠይቃል። በትምህርት ጥራቱ ዙሪያ ዛሬም ልክ እንደ ፈተናው መሰረቅ ዓይነት ያሉ ተግዳሮቶችን ማስወገድ ይገባልና።

የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (ከ9-10) ጥቅል ተሳትፎ ምጣኔ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 39.7 በመቶ ወደ 62 በመቶ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ብዙም ለውጥ ሳያሳይ ባለበት መቆሙን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ስለሆነም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት እየጐረፈ ያለውን ተማሪ ለማስተናገድና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ለማሳደግ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ግንባታን ማስፋፋት የግድ ይላል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርት (ከ11-12) ጥቅል ተሳትፎ በ2002 ከነበረበት 7 በመቶ በ2007 ወደ 20 በመቶ ገደማ በማሳደግ ስኬታማ አፈፃፀም መመዝገቡን ያገኘኋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የቅበላ አቅም ከፍ ያለ ሲሆን፤ የባለሙያዎች የብቃት ምዘና በስፋት ተከናውኗል፡፡ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የጥራትና አግባብነት ችግር አሁንም ጐልቶ የሚታይ በመሆኑ በቀጣይ በዚህ ዙሪያ መሠረታዊ መሻሻል ለማምጣት ከፍተኛ ርብርብ መጠየቁ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡

ዛሬ ላይ በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ በተከናወነው የማስፋፋት ሥራ በቅድመ ምረቃ የቅበላ አቅምን ወደ 400 ሺህ እንዲጠጋ አድርጎታል። በድህረ ምረቃም በኩል የቅበላ አቅም ወደ 28 ሺህ ገደማ ከፍ ብሏል። የሴት ተማሪዎች ድርሻ በቅድመ ምረቃ 32 በመቶ፣ በድህረ ምረቃ 19 በመቶ ደርሷል።

እርግጥ ከትምህርት ጥራት አኳያ እየታየ ያለውን ጅምር መሻሻል ይበልጥ ማጎልበት ይገባል። ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የመስኩ ተቋማት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ ኘሮግራም በተገቢው ሁኔታና በዕናት መተግበር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ሃቆች ሀገራችን በትምህርቱ ዘርፍ ምን ያህል ርቀት እንደተየጓዘች የሚያሳዩ ናቸው።

እርግጥ ከዚህ የትምህርት ዘርፍ አፈፃፀም የምንገነዘበው ነገር ቢኖር በየትኛውም መስክ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ሊኖረሩ ይችላሉ። በመንግስት ትኩረት የተሰጠው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ጉዳይ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። ታዲያ ተማሪዎች በዚህ መንግስታዊ ጥረት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ በተጠናከረ ሁኔታ መወጣት ከቻሉ ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት አሻራቸውን ሊያሳርፉ ይችላሉ።