NEWS

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ

By Admin

October 17, 2017

ከትናንት ጀምሮ መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ የቆየው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልሉ መንግስትን ከ836 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማፅደቅ ተጠናቀቀ።

ተጨማሪ በጀቱ ለመደበኛ፣ ለካፒታል፣ ለገጠር ወረዳዎችና ለከተሞች የተደለደለ መሆኑ ነው የተገለፀው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ የክልሉ መንግስትን የ2010 በጀት ዓመት እቅድን ለምክር ቤቱ አቅርበው ነበር።

በዚህም ወቅት 2010 በጀት ዓመት በትግራይ ክልል 11 ነጥብ 3 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ መታቀዱን ነው የገለፁት።

ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ለማሳካትም የግብርናው ዘርፍ 36 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ 24 ነጥብ 7 በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፍ 38 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ ተመርተው ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በእቅዱ የተቀመጠውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ሁሉም በተሻለ መልኩ ጠንክሮ እንዲሰራ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የክልሉ መንግስት በእቅዱ በከተሞች አካባቢ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ትኩረት እንደሚሰጥ አስቀምጧል።

በገጠር የመስኖ ልማትም 416 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ለማልማት የታቀደ ሲሆን፥ በዚህም ከግማሽ ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

አቶ አባይ እንደገለፁት፥ የክልሉን የድህነት መጠን በዚህ ዓመት ወደ 18 በመቶ ለማውረድ ታቅዷል።

ስራ አጥነትን ደግሞ ወደ 13 በመቶ ለመቀነስ እንደሚሰራ ነው የጠቆሙት።

በሙሉጌታ አፅበሓ