Artcles

የአንድ ህዝብ ስኬት የሁሉም ህዝብ ነው!

By Admin

October 03, 2017

የአንድ ህዝብ ስኬት የሁሉም ህዝብ ነው!

ዳዊት ምትኩ

የኢትዮጵያ ህዝቦች በህገ መንግስታቸው በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተሳሰረ አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህም የአንዱ ህዝብ ስኬት የሌላኛውም ስኬት፣ እንዲሁም የአንዱ ጉዳት የሌላኛውም ጭምር መሆኑን የሚያሳይ ነው። አገራችን ውስጥ ያለው ስርዓት ሁላችንም ተያይዘን የምናድግበት እንጀ የምንጎዳበት አይደለም። በመሆኑም ለአንድ ዓላማ የተሰለፈ ህዝብ ይህን ሀገራዊ ራዕይ ከማሳካት አኳያ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ህገ መንግሥቱ አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል። ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የመቀየስ ኃላፊነት ወድቆበታል።

በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ህገ መንግሥቱ በማያሻማ መልኩ ደንግጓል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና እድገት የማዋል ኃላፊነት እንዳለበትም እንዲሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ደንግጓል። በደርግ ሥርዓት ወቅት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ሃብት ባለቤት የመሆን መብት በመሠረቱ ተንዷል። ዛሬ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ ተረጋግጦለታል። የግል ንብረት ማፍራት በድምሩ በአገራዊ እድገት ላይ የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

ግለሰቦች ካለገኙ ከእነርሱ ጋር ተያያዥ ስራ ያላቸው ሌሎች ግለሰቦች ተጠቃሚ አይሆኑም። ህዝቦችም እንዲሁ። አንድ ህዝብ ካገኘ በድምር ውጤቱ የአገርን ኢኮኖሚ ያሳድጋል። ሌላኛው ካላገኘ ደግሞ ያገኘው ላላገኘው በመስጠት የነበረውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መጎተቱ አይቀርም።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት ተረጋግጦለታል። በህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረትም ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው በተግባር እየታየ መጥቷል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸውም በገሃድ እየታየ ይገኛል።

የልማት እንቅስቃሴው ዋና ዓላማም የዜጐችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት በመሆኑ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ስለመሆናቸው ከጋራ መግባባት ላይ  ተደርሷል። ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው።

የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል። እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትንም ይጨምራል።

የግንቦት ትሩፋቶች የሆኑት የህገ መንግሥቱ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ድንጋጌዎች ተጠቃለው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሣኝነትን የሚያመለክቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን የሚያመለክቱ ናቸው። የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ መሆናቸውንም ያሳያሉ። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የልማት እንቅስቃሴዎች ዋና ዓላማ መሆን እንዳለበት ከህገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለመረዳት የሚከብድ አይመስለኝም።

የክልሎችን እኩል የመልማት እድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። በራስ አቅምና በራስ ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ወሳኝ መሆኑን የህገ መንግሥቱ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው። ህገ መንግሥቱ ልማት የመብት ጉዳይ መሆኑን ይገልጻል። የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል መሆኑ ተደንግጓል።

እንደሚታወቀው የልማት አጀንዳ ለአገራችን እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በዚህ ድንጋጌ መሰረትም የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ “የሞት ሽረት” ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ርብርብ እያደረገ ነው። ከአንዴም ሁለቴ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን በመንደፍ “የሞት ሽረቱን” ጉዳይ ወደ መሬት አውርዶ እየሰራ ነው።

በዚህም አብዛኛውን ህዝብ መሰረት ያደረገ ዕቅድ ነድፎ የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በማሳለጥ ላይ ይገኛል። በሀገራችን በተዘረጋውና በተመረጡ ጉዳዩች የመንግስት ጣልቃ ገብነት ያለበት የነፃ ገበያ ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓትም፤ የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ አገሪቱን ከነበረችበት ፈታኝ የድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማው አድርጎ እየሰራ ነው።

ይህ ዓላማም የትኛውንም የህብረተሰብ ክፍል ሳይለይ ሁሉንም ህዝቦች የሚጠቅም ነው። በዚህ ዓላማ ስር የተሰባሰቡት የአገራችን ህዝቦች አንዱ ሲያገኝ ሌላውም የሚያገኝ እንጂ በአንዱ ማጣት የሚደሰቱ አይደሉም። ስርዓቱ ዜጎች ተባብረው በመስራት አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብን የሚገነቡበት ነው።

በዚህም አንድ ህዝብ ሲያገኝ ሌላውም ተጠቃሚ ይሆናል። አንደኛው ሲጎዳም ሌላኛው ተጎጂ መሆኑ አያጠያይቅም። በአንድ የጋራ ጣራ ስር የሚኖሩ ሰዎች ቤቱ ሲያፈስ ሁሉንም እንደሚያረጥበው ሁሉ፤ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ጥላ ስር ተሰባስበው በአዲስ መንፈስ በድህነት ላይ የዘመቱ ዜጎች አንዱ ሲጠቀም ሌላውም ተጠቃሚ መሆኑ አይቀርም።

ከዚህ አንፃር ባለፉት ዓመታት በኤልኒኖ አማካኝነት በአገራችን በተፈጠረው ድርቅ ሳቢያ በአገሪቱ ውስጥ የምግብ ሰብል እጥረት እንዳይከሰት ትረፍ አምራች አካባቢዎች በድርቅ የተጎዱትን አካባቢዎች ኮታ መሸፈናቸው አስረጅ ነው ማለት ይቻላል። ትርፍ አምራቾች የአገሪቱ የምገብ ሰብል ኮታ እንዳይስተገስጎል ከማድረጋቸውም በላይ፤ ለድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር እናስታውሳለን። በመሆኑም ይህን መሰሉ ማስረጃ የአገራችን ህዝቦች ዕጣ ፈንታ በፌዴራላዊ ስርዓቱ ስር ተያይዞ ማደግ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።