Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአዲሱ ትውልድ ኃላፊነት

0 455

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዲሱ ትውልድ ኃላፊነት

አሜን ተፈሪ

አዲሱ ትውልድ ‹‹በፌዴራላዊ – ሪፐብሊካዊ›› ስርዓት ውስጥ ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ የአዲሱ ትውልድ ኃላፊነት ‹‹ፌዴራላዊ – ሪፐብሊካዊ›› ስርዓቱን የመጠበቅ እንጂ፤ የመፍጠር ሥራ አይደለም፡፡ ይህን ስርዓት ሊያበላሸው ወይም ጸንቶ እንዲቆም ሊያደርገው የሚችለው ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከአገር ግንባታ አኳያ ያሉበትን ኃላፊነቶች ለመወጣት ራሱ የሚገኝበትን የታሪክ ምዕራፍ በውል መረዳት ይኖርበታል፡፡ የአዲሱ ትውልድ የመጀመሪያው ኃላፊነት፤ ያለፈው ትውልድ ሰርቶት ያለፈውንና የተረከበውን መልካም ስራ ጠብቆ ማቆየት፣ የተደረሰበት ዕድገት ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ የትላልቅ ወንድሞቹና እህቶቹ ድካምና መስዋእትነት መና ሆኖ እንዳይቀር በታላቅ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ነው፡፡

 

ያለፈውን ትውልድ አኩሪ ታሪክ ጥላሸት ለመቀባትና የተገነባን አገር ለማፍረስ የሚደረግን ማናቸውንም ጥቃት በመመከት የተረከበውን አደራ በብቃት የመወጣት ኃላፊት ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም አዲሱ ትውልድ ያለፈው ትውልድ ጀምሮ ያልጨረሳቸውን መልካም ነገሮች የማጠናቀቅ እና የፈፀማቸውን ስህተቶችም መርምሮ የማስተካከል የቤት ሥራ አለበት፡፡ በርግጥ አዲሱ ትውልድ ባለፈው ትውልድ ድክመትና ስህተት ተጠያቂ ባይሆንም፤ ጎደሎዎቹን ከመሙላትና የተጣመመውን ከማቃናት ወደ ኋላ ሊል በጭራሽ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ጎደሎዎቹና ጠማማዎቹ የሚያስከትሉት ችግር ሰለባ የሚሆነው ያለፈው ትውልድ ሳይሆን አገር ተረክቦ የሚገኘው አዲሱ ትውልድ ነው፡፡ በመሆኑም አዲሱ ትውልስ ይህን ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረግም እሱን ለሚተካው ቀጣይ ትውልድ የሚያወርሰውን ታሪካዊ ቅርስ በጥንቃቄ እና በብቃት ማከናወን ይገባዋል፡፡

 

አዲሱ ትውልድ ካለፈው ትውልድ የተረከበውን መልካም ሥራ በመጠበቅ፣ የተጓደሉትን ደግሞ በማሟላትና የተሳሳቱትን በማረም በኩል የሚያከናወናቸው ተግባራት በራሳቸው ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት ሆነው ያገለግሉታል፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ ለአዳዲስ ሁኔታዎችና መድረኩ ለሚጠይቃቸው ጉዳዮች ብቁና ትክክለኛ መልስ በመስጠት የአገር ግንባታውን ወደ ከፍታ ማሸጋገር ይጠበቅበታል፡፡ ቀጣዩ ትውልድ እሱ በተጓዘባቸው አስቸጋሪ መንገዶች እንዳይጓዝ፣ እሱን የፈተኑት ችግሮች በተተኪውም ላይ እንዳይደርሱ፣ እሱ ታላቅ ወንድሞቹና እህቶቹ ያጓደሉትንና የተሳሳቱን የማስተካከለ ኃላፊነት እንደተረከበው ሁሉ፤ ለታናሽ ወንድሞቹና እህቶቹ የቤት ስራ ትቶ እንዳያልፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎችን በንቃት ማከናወን ይኖርበታል፡፡

 

አዲሱ ትውልድ ወይም ወጣት የምንለው ከታላቆቹ የተረከበውን አደራ በብቃት የሚወጣውም ሆነ ለታናናሾቹ መልካም ነገር ለማስተላለፍ መሰረት የሚጥለው ዛሬ በሚያከናውናቸው ተግባራት ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ የሚፈፅማቸው መልካም ነገሮች ነገ እሱን ለሚተኩት ታዳጊዎች ጠንካራ መሰረት ይሆናቸዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የሚያበላሻቸው ነገሮችና የሚፈፅማቸው ስህተቶች በታዳጊዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዲሁም ወደፊት የሚጋፈጡት የቤት ስራ ይፈጥርባቸዋል፡፡ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ወጣት በዚህ መሰረተ ሃሳብ ላይ የተሟላ ግልፅነት መያዝና አገር ተረካቢነት ሚናውን በብቃት ለማከናወን መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡

 

ለዛሬው የኢትዮጵያ ወጣት አገር ያስረከቡት የትናንት ወጣቶች ከታላቆቻቸው የተረከቧት ኢትዮጵያ ጭራሹን መልካም የሚባል ነገር አልነበራትም ባይባልም ህልቆ መሳፍርት ችግሮች የተደራረቡባት ሐገር እንደነበረች ግን የማይደበቅ የትናንት ታሪካችን ነው፡፡ ሰፊው የአገራችን ህዝብ የእለት ጉርሱን አሟልቶ ማግኘት የማይችልባት፤ ለጥቂቶች መሳፍንትና መኳንንት ምድራዊ ገነት ለብዙሃኑ ደግሞ ሲኦል የሆነች፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች የተረገጡባት፤ ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስ›› የሚል ይትባህል የሰፈነባት፣ የብሄሮችና ብሄረሰቦች እስር ቤት የሆነች አገር ነበረች፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚደርስባቸውን አስከፊ ብዝበዛና ጭቆና ተቃውመው ያደረጉትን ትግል ርካብ በማድረግ በስልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠው የደርግ መንግስት በህዝቦች ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና ብዝበዛ በአዲስና በከፋ መንገድ ያስቀጠለ መንግስት ነበር፡፡

 

ስለሆነም ለዛሬው ወጣት አገር እያስረከበ የሚገኘው ትውልድ አገራችንን የወደቀችበትን አስከፊ ሁኔታ የመቀየርና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የማስረከብ ኃላፊነት ተሸክሞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ የደርግ መንግስት የመጨረሻዎቹ ዓመታት በመላ አገሪቱ የጦርነት ነዲድ የሚንቀለቀልበት፣ ሁሉም ነገር ወደ ጦርነት በሚለው የደርግ አዋጅ የተነሳ የአገሪቱ ወጣቶችና ቁሳዊ ሃብት ለጦርነቱ የሚገበሩበት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ የወደቀበት ህዝቡ የዛሬን ካልሆነ በቀር ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ርግጠኛ ያልነበረበት፤ አገሪቱ ዛሬ ወይም ነገ እንደነ ሶማሊያ ትበታተናለች ተብሎ የሚሰጋበት ብቻ ሳይሆን የማያጠራጥር ፍፃሜ ተደርጎ ተወሰደበት፤ በአጠቃላይ አገራችን በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠችበት ወቅት ነበር፡፡ የያኔው ወጣት ይህንን ጨለማ ለመግፈፍ መከፈል የሚገባውን የህይወት መስዋእትነት ከፍሎ የዛሬ 25 አመት ብሩህ ተስፋ የናኘበት አዲስ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት መድረክ ከፍቷል፡፡

 

እነሆም ባለፉት 25 አመታት በአገራችን ተአምር የሚባሉ ለውጦች መጥተዋል፡፡ በማያቋርጥ ማሽቆልቆል ወደ ውድቀት በማምራት ላይ የነበረችው አገራችን በማያቋርጥ አኳኋን ማንሰራራትና ወደ እድገት መሸጋገር ችላለች፡፡ በሰላምና ዴሞክራሲ መታጣት ምክንያት የመበታተን ስጋት ተጋርጦባት የቆየችው አገራችን በህዝቦቿ ፈቅዶ መዋሃድ ጠንካራ አንድነት የፈጠረች አገር ሆናለች፡፡ በፈጣን እድገት እየገሰገሰች የምትገኘውን አገር የተረከበው የዛሬው ወጣት አዲሱ መድረክ የዛሬ 25 አመት ሲከፈት በአብዛኛው ያልተወለደና ነፍስ ያላወቀ የነበረ ቢሆንም የሚረከባት ኢትዮጵያ ታላቅ ወንድምና እህቶቹ ባለፉበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲያልፍ የማይጠየቅባት፣ የተሻለ እድልና ተስፋ የሚያገኝባት፣ ቀጣይነት ባለው እድገት ወደፊት የሚራመድበት እንጂ ባለበት የማይቆምባት ወይም ደግሞ ወደኋላ የማይመለስባት፣ ሰላም የሰፈነባትና መብቱ የተከበረባት እንድትሆን የተደረገውንና በመደረግም ላይ ያለውን ጥረት እያስተዋለ እንዳደገ ይታመናል፡፡

 

ይህ ወጣት ከታላቆቹ እየተረከባት ያለችውን በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝና ታላቅ ተስፋ የፈነጠቀባትን አገር በጀመረችው ብቻ ሳይሆን በላቀ ፍጥነት ወደፊት እንድትገሰግስ ሌት ተቀን መትጋት፤ ወደ ኋላ ሊመልሳት የሚችልን ማናቸውም አይነት አፍራሽ ድርጊት በንቃት መጠበቅ ይገባዋል፡፡ መላው የአገራችን ወጣቶች ሁኔታውን ከዚህ መሰረተ ሃሳብ አኳያ በጥሞና መገምገምና ባለፈው ዓመት የታየው ሁከት ዳግም የሚከሰትበትን አጋጣሚ ዝግ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy