የኢትዮጵያና ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደቡብ አፍሪካ ከሚገኙት የተቃዋሚ ሃይሉ መሪ ሪክ ማቻር ጋር በደቡብ ሱዳን ሰላምን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ተመካክረዋል፡፡
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የሱዳኑ አቻቸው ኢብራሂም ጋንዱር ከቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ውይይቱን ያካሔዱት በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት አስመልክቶ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የደረሱትን ስምምነት ለመተግበር ይቻል ዘንድ ከፍተኛ የተሃድሶ ፎረም ለማካሄድ የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው፡፡
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መግለጫ ዋቢ አድርጎ ሱዳን ትሪቡን እንዳስነበበው ስብሰባው በደቡብ ሱዳን ሰላምን የማረጋገጡ ጉዳይ አጣዳፊና አስፈላጊ መሆኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ፍሬያማና አወንታዊ ነበር፡፡
መግለጫው ሁለቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ሪክ ማቻር የተወያዩባቸውን ዝርዝር ጉዳዮችና የደረሱበትን ስምምነት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ አለመስጠቱንም ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት የሱዳን ሰላም ልዩ መልዕክተኛ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ፕሬዝዳንት ጋርም ኢጋድ የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት ማደስ በሚቻልበት ዝርዝር ሁኔታ ላይ መምከራቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
ባለፈው ሃምሌ የኢጋድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አዲስ አበባ ባካሔደው የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት የተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባው ሁሉም ተቀናቃኝ ኃይሎች በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለመፍታት የደረሱትን ስምምነት እንዲያከብሩ፣ ከጸብ ጫሪነት እንዲታቀቡና በተሃድሶ ፎረሙ ትኩረት እንዲሰጣቸው የሚፈልጓቸውን ጉዳዮች የተመለከተ ተጨባጭ ፕሮፖዛል እንዲያስገቡ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡