Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የእምቦጭ አረም በዝዋይና ቆቃ ሀይቆች ላይ መከሰቱ ተነገረ

0 1,793

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የእምቦጭ አረም ከጣና ሀይቅ ውጭ በዝዋይ እና ቆቃ ሀይቆች እና በጅማ ከተማ የሚገኘው የቦዬ ወንዝ ላይ በአሳሳቢ ደረጃ መከሰቱ ተነገረ።

ሀይቆቹ እና ወንዙ ከግብርና በተጨማሪ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች አገልግሎት ላይ የሚውሉ እንደመሆናቸው የአረሙ መከሰት ስጋት ፈጥሯል።

የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የብዝሃ ህይወት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሀኑ ኢደቲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የቆቃ ሀይቅ ከ800 ሄክታር መሬት በላይ የውሃ ክፍል በአረሙ ተወሯል።

እንዲሁም የዝዋይ ሀይቅ 50 ሜትር ስፋት እና ከ1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የውሃ ክፍል ላይ አረሙ መከሰቱንም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በጅማ ከተማ የሚገኘው የቦዬ ወንዝም ለእምቦጭ አረም የተጋለጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲቱዩት አስታውቋል።

አረሙ የወንዙን 50 ሄክታር ክፍል የሸፈነ መሆኑን እና ወንዙን ለመታደግ እየተሰራ መሆኑን የኢንስቲቱዩቱ የደን፣ የግጦሽ መሬት እና እፅዋት ዳይሬክተር ዶክተር ዴቢሳ ለሜሳ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የብዝሃ ህይወት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሀኑ ኢደቲ በበኩላቸ፥ የውሃ አካላቱን በፍጥነት እየወረረ ያለውን የእምቦጭ አረም ለመቀነስ በሰው ሀይል ለመስራት መታሰቡንም ተናግረዋል።

በውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የኢኮ ሀይድሮሎጅ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ዮሀንስ ዘሪሁን፥ የእምቦጭ አረም በቆቃ እና ዝዋይ ሀይቆች ላይም መከሰቱን አረጋግጠዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ስጋት ከስሩ ለመንቀል ስራዎችን መጀመሩንም አቶ ዮሃንስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በመፍትሄነት ከያዛቸው ሁለት መንገዶች አንዱ አረሙን ከስሩ እስከ ደለሉ መንቀል የሚያስችል መሳሪያ ከውጭ ሀገር ማስመጣት ነው።

ይህ መሳሪያ አረሙን የመንቀል፣ ለአረሙ ምቹ የሆኑ ደለሎችን የማፅዳተ እና አረሙን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የመለወጥ አቅም ያለው መሆኑን ነው አቶ ዮሀንስ የሚናገሩት።

መሳሪያውን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት አረሙን ወደ ማዳበሪያነት ቀይሮ ለገበያ ከሚያቀርብ ኢቲሲ ከተሰኘ የሴኔጋል ኩባንያ ጋር የስምምነት ሰነድ መፈራረሙን አቶ ዮሃንስ ገልፀዋል።

መሳሪያው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን እስከ 2 ሚሊየን ዩሮ በላይ ወጪ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

መሳሪያውን በፍጥነት ወደ ሀገር በማስገባት አረሙ በሚታይባቸው ሀይቆች እና ወንዞች ላይ የማስወገድ ስራ እንደሚሰራም አቶ ዮሃንሰ ገልፀዋል።

በተጨማሪ አረሙ ወደ ውሃ እንዳይገባ የመከላከል አቅም ካላቸው ተክሎች ውስጥ ዋነኛ የሆነውን የደንገል ተክል የማልማት ስራ መስራትን በሌላ መፍትሄንት ይዟል።

የዚህን ተክል የማልማት ስራዎች ለመጀመር እና በሀይቆች ዙሪያ ተክሉ እንዲተከል ለማድረግ ፕሮጀክት መቀረፁንም አቶ ዮሃንስ ተናግረዋል።

ሀይቆች ራሳቸውን ከመሰል ችግሮች የመከላከል አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ጥናቶችን ለማካሄድ ስምምነት እየተደረገ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

 

በዙፋን ካሳሁን

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy