Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወል እሴቶቻችንን የሚያዛንፉ አስተሳሰቦችና መዘዞቻቸው

0 318

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወል እሴቶቻችንን የሚያዛንፉ አስተሳሰቦችና መዘዞቻቸው

                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

ኢትዮጵያዊያን በጋራ የያዟቸው እሴቶች በርከታ ናቸው። ከእነዚህ እሴቶች ውስጥ መቻቻልና መከባበር፣ የተቸገረን መርዳት፣ ተካፍሎ የመብላት፣ በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን በጋራ መፍታት ጥቂቶቹ ናቸው። በእነዚህ እሴቶቻቸውም እርስ በርስ እየተደጋገፉ ሀገራቸውን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ አብቅተዋታል።

በአንፃሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያዊያንና ህዝቦቿን የማይወክሉ እንዲሁም ለዘመናት ይዘዋቸው የመጡትን እሴቶች የሚያዛንፉ አስተሳሰቦች በአንዳንድ ህገ ወጦችና ፀረ ሰላም ሃይሎች ተግባራዊ ሲደረግ እየተመለከትን ነው። ‘የእኔ ድንበር እስከዚህ ወሰን ድረስ ስለሆነ እንዳትመጣ’ የሚሉ ቀደምት እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦች ብቅ ብሏል።

ለአንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ እመርታ የተሰለፈ ህዝብ ሌላኛውን በጥርጣሬ የመመልከት አዝማሚያም እየተስተዋለ ነው። ትምክህትና ጥበት የወለዷቸው አስተሳሰቦችን በመከተል የህዝቦችን ሰላም ለማደፍረስ የሚችሉ አስተሳሰቦችም እየታዩ ነው።

ይሁንና እነዚህ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኳቸውን የወል እሴቶቻችንን የሚያዛንፉ ተግባራት መዘዛቸው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ባለፉት ጊዜያት ተመልክተናል። ከወል እሴቶቻችን ሊያስወጡን የሚችሉት አስተሳሰቦች የሰው ህይወትን፣ የአካል መጉደልንና የንብረት መውደምን ከማስከተላቸው በስተቀር ለየትኛውም ህዝብ አንዳች ጠብ የሚል ነገር ያተረፉ አይደሉም።

በተለይም በሀገራችን ህዝቦች እየጎለበተ የመጣውን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን በመሸርሸር ረገድ ወደር አልተገኘላቸውም። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም የተተገበረው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፍሬ ማፍራት ችሏል፡፡ ምክንያቱም ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በሰላም የመኖርና ችግርንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ማህበረሰባዊ ግንኙነትን በብቸኝነት መከተል ነውና፡፡

እዚህ ላይ ‘ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ምንድነው?’ የሚል ጥያቄ በማንሳት ፅንሰ ሃሳቡን በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ይበልጥ ለማጎልበት ምን ማድረግ እንደሚገባ ለመመልከት እንሞክራለን።…ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከትምክህትና ከጠባብ ኃይሎች ጋር ለሚደረግ ትግል ዓይነተኛ መሳሪያ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ በመሆኑ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን የሚያረጋግጥ ነው።

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው። ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው፡፡ የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀሬ ነው።

እንደሚታወቀው ባለፉት 25 ዓመታት ትምክህትና ጠባብነትን ለመዋጋት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ሆኖም አመለካከቱ አልፎ አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹት አካላት አማካኝነት በመሆኑ ሁለቱን ማነቆዎች ከሕዝቡ ጋር በመታገል ለውጡን ማምጣት ይቻላል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኘነትን ከአራት መሰረታዊ ትርጓሜዎቹ አኳያ ማየት ይቻላል። እነርሱም ማንነትን ማወቅ፣ የሌሎችን ማንነት ማወቅ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና አካባቢን ማልማት ናቸው።

ማንነትን ከማወቅ አኳያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ያስፈልጋል። የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መለየትንም እንዲሁ። እንደ አቶ ሕላዊ የሌሎችን ማንነት በማወቅ ረገድም፣ ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም መለየት ያስፈልጋል።

እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን ያካትታል። አካባቢን ከማልማት አኳያም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ከባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን የሚያካትት ነው። በመሆኑም አራቱን የፅንሰ ሃሳቡን ብያኔና አተገባበርን በአግባቡ በመገንዘብ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ይበልጥ ገቢራዊ ማድረግ ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ ለዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዕውን መሆንና ማበብ የታገለ ድርጅትና እንዲሁም እሳቤውን በመርህ በፅናት በማስፈፀም ላይ የሚገኝ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው።

እርግጥ ብዙ ሕዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ‘የትምክህት ሐሳባችንን በነፃነት እንግለጽ፣ አትንኩን’ የማለት ነገር ይታያል፡፡ ይህንን አመለካከት መጠጊያ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡

ህገ- መንግሥቱ አስተሳሰባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግም ሆነ መንግስት የተለየና የተሳሳተ ሐሳብ ያላቸውም ሰዎች ቢሆኑም ሃሳባቸውን ለምን ይገልጻሉ የሚል ብዥታ ኖሯቸው የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲከብር በአንፃሩ ደግሞ  መከበርን ያተርፋል፡፡ እርግጥ ያለፈው ታሪክ አንድን ሕዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ይሞክራሉ፡፡ ይህ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡

ዛሬ ላይ አንድ ብሔር የበላይ በሌለበት ሁኔታ፣ እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በማጋጋም ትርፍ ለማግኘት መሞከር ተገቢ አይመስለኝም። የሚፈልግ አካል ካለም ሊሳካለት አይችልም፡፡ ለምን? ከተባለ፤ እየተካሄደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ውጤት እያስገኘ ከመሆኑም በላይ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ላይ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ በመቀጠሉ ነው፡፡

ርግጥ አንዳንድ የትምክህት ኃይሎች ህብረተሰቡን በተሳሳተ ጎዳና ሊመሩት ይችላሉ። አስተሳሰቡ እነርሱ የሚያምኑበትን ‘ከሁሉም የበላይ ነን፣ ከእኛ ወዲያ ለአሳር’ የሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ምልከታ በመሆኑ ሀገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ መንገድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም።

እንዲህ ዓይነቱ ፌዴራላዊ ስርዓቱም ይሁን ህዝቡ የማይደግፈውን የዴሞክራሲ ፀር አስተሳሰብን ሁሉም በየደረጃው ሊታገለው የሚገባ ይመስለኛል። አስተሳሰቡን ‘መንግስት ለብቻው ይወጣው’ ብለን የምናልፈው ከሆነ፣ ምንም ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ምክንያቱም መንግስት ከህዝቡ ጋር ካልሆነ በስተቀር ለብቻው የሚፈፅመው አንዳችም ነገር ስለማይኖር ነው።

እንደ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ዓይነት የወል እሴቶች ጠባብነትን በመዋጋት ረገድም ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው። በጠባብነት አስተሳሰብ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ቡድን ከእርሱ ውጪ ስላለው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ምንም ዓይነት ደንታ የለውም።

በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኘውን ማናቸውም እሴትን በራሱ ምህዳር ውስጥ አጥብቦ በማየት ይተረጉማል። ከትርጓሜ በዘለለም የሚገኙ ሀገራዊ ጥቅሞችን በራሱ ምህዳር ውስጥ ብቻ ለመጠቀም የሚሻ ነው። ይህ ደግሞ በጋራ ለማደግ ያሰብነውን የወል ምልከታ የሚሸረሽር ነው።

እናም ባለፉት ጊዜያት ስንተገብራቸው የመጣናቸውን የወል እሰቶቻችንን ሊበርዙ የሚችሉ አስተሳሰቦችን ሳይገነግኑ በአፋጣኝ መከላከል ይገባል። እነዚህ መርዘኛ አስተሳሰቦች መዘዛቸው የሰዎችን ህይወት ከመቅጠፍ በላይ ሀገር እንደ ሀገር የምታደርገውን ተግባፖች በመግታት ወደማንፈልገው ጎዳና የሚመሩን መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy