Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ማነቆዎቹ ተለይተው ይፈቱ

0 304

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ማነቆዎቹ ተለይተው ይፈቱ

ብ. ነጋሽ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ሰሞኑን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አፈፃፀምና ቀጣይ ሁኔታዎች የገመገመበትን ጥናት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። የተቋሙ የባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ተገኝቶ ያካሄደውን ግምገማ ውጤት አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መግለጫ፣ እ ኤ አ የ2016/17 የሃገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት በ9 በመቶ እንደሚያድግ አመልክቷል። ኢኮኖሚው በ9 በመቶ ያድጋል ማለት ነው።

ጥናቱን ያካሄደው የአይ ኤም ኤፍ ቡድን መሪ ጁሊዮ ኤስካላኖ በሰጡት መግለጫ በ2016/17 ቁልፍ የሚባሉ ሃገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸው ሸቀጦች ዋጋ መቀነሱንና የድርቅ ተፅእኖ በተለያዩ የሃገሪቱ በተደጋጋሚ ማጋጠሙን ጠቅሰው፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁሞ ጥሩ አፈጻጸም ማሳየቱን አስታውቀዋል። የኢፌዴሪ መንግስት ድርቅ ላስከተለው የምግብ እጥረት ተጽእኖ ምላሽ ለመስጠት ከልማት አጋሮቹ መንግስታት ጋር በመሆን ያከናወናቸው ስራዎች በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩን መቋቋም መቻሉን በጥንካሬነት አንስተዋል።

ከመንግስት በጀት አጠቃቀም አኳያ ያለውን የሃገሪቱን ሁኔታም አስመልክቶ፣ የበጀት አጠቃቀሙ በጥንቃቄ የተመራ በመሆኑ የሃገሪቱ የበጀት ጉድለት አስቀድሞ ከተጠበቀው በታች መሆኑን ይህም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር ወደ 2 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ እንደነበረ አስታውቀዋል።

ግምገማውን ያደረገው የአይ ኤም ኤፍ ቡድን፣ የሃገሪቱ የወጪ ንግድ አፈፃፀም ግን ምንም እድገት ሳያሳይ ባለበት እንደቆመ አስታውቋል። በተለይም የዓለም የሸቀጦች ግብይት መቀዛቀዝና የወጪ ንግዱን ያጠናክራሉ ተብለው የተጠበቁ ፕሮጀክቶች መጓተት አፈፃፀሙ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን አመልክቷል። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ስኬት የገለጸው አይ ኤም ኤፍ በተለይ ከወጪ ንግድ ጋር በተያያዘ ያነሳው ችግር የኢኮኖሚ እድገቱን ቀጣይነት ከማረጋገጥ አኳያ አሳሳቢ ነው። ይህን የኢፌዴሪ መንግስትም ተገንዝቧል።

የንግድ ሚኒስቴር የሃገሪቱን የወጪ ንግድ አፈጻጸም አስመልክቶ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ ሰጥቷል። ሚኒስትሩ ይፋ ባደረገው መረጃ በ2009 በጀት ዓመት ከውጪ ንግድ 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቋል። ገቢው ከ2008 በጀት ዓመት ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር የ51 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። በበጀት ዓመቱ ከውጭ ንግድ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እንደነበረ ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፣ ይሁን እንጂ አፈጻጸሙ የዕቅዱን 61 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቋል። ይህም ከእቅዱ የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ አለው።

የወጪ ንግድ ገቢው አፈፃፀም ከእቅድ አኳያ ሲታይ ደካማ ሊሆን የቻለው በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብርና ምርቶች ፍላጎት በመቀነሱ የምርቶቹ ዋጋ በመውረዱ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል። በዚህ ምክንያት ለምሳሌ በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች የምርቱ ዓለም አቀፍ ፍላጎትና ዋጋ በማሽቆልቆሉ ምክንያት፣ በሌሎች የሰብል ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ የተገደዱበት ሁኔታ መኖሩን ሚኒስቴሩ አስታወቋል። በተለይ ቡና፣ የቁም እንስሳት፣ የጥራጥሬ ሰብሎችና የወርቅ ምርቶች በህግ ወጥ ንግድ ወደ ውጪ አገራት መሄዳቸው ለውጭ ንግድ ገቢው መቀዛቀዝ ሌላው ምክንያት መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። አምራች ኢንደስትሪው እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በሚፈለገው መጠን ለውጭ ገቢያ ማቅረብ አለመቻሉም ለገቢው ማሽቆልቆል በምክንያትነት ተጠቅሷል።

እንግዲህ፣ መንግስት የወጪ ንግድ አፈጻጸምን ለማሻሻል የተላያዩ እቅዶችን ተግባራዊ ለማደረግ መዘጋጀቱን ሲገልጽ ቆይቷል።።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የ2009 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክተው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ በግብርና ምርት የወጪ ንግድ በኩል አሁን ያለውን ጥሬ ምርት የመላክ ሁኔታ እሴት ወደሚጨመርባቸው ምርቶች መቀየር የወጪ ንግር ሚዛኑን ለማስተካካል ከሚወሰዱት እርምጃዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። በየአካባቢው በክልል መንግስታት ሊገነቡ የታቀዱትና በተወሰኑ ክልሎች በግንባታ ላይ የሚገኙት የግብርና ምርት ማቀነባባሪያ የኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚቋቋሙ ፋብሪካዎች ይህን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል ተበሎ እንደሚጠበቅም ጠቅላይ ምኒስትሩ አመልክተዋል።

የግብርና የወጪ ንግድ ምርቶችን በአይነት ማስፋት እንደሚያስፈልግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በተለይ የአበባና አትክልት ዘርፍ ትኩረት የተሰጣቸው መሆናቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጪ ንግድ ላይ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ የሚገኘውን የአበባ ልማት ለማስፋት ተጨማሪ መሬት እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተው፣ በመንግስት ስር ያሉ ቀደም ሲል የመንግስት እርሻ የነበሩ ቦታዎችን ለአበባ ልማት ለማዋል መታቀዱን ገልጸዋል።

እስከአሁን የአበባ ልማት የሚካሄድበት መሬት 1200 ሄክታር መሆኑንና ከዚህም በዓመት 250 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እነደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በመንግስት እርሻነት የተያዘ በተለያየ የሃገሪቱ አካባቢ ያለ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ለአበባ ልማት በማዋል የወጪ ንግድ ገቢውን በዚያው ልክ ለማሳደግ መታቀዱንም አመልክተዋል። ከዚህ ባሻገር ለሃገሪቱ የወጪ ንግድ አዲስ የሆነውን የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የወጪ ንግድ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።

የሃገሪቱን የማኑፋክቸሪንግና ኤክስፖርት ዘርፍ ለማሳደግ እስከያዝነው ዓመት አጋማሽ  የኢንደስትሪ ፓርኮች ቁጥርን ወደ 15 ለማድረስ መታቀዱን የኢንደስትሪያል ፓርኮች ቦርድ መረጃ ያመለከታል። በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ በስራ ላይ የሚገኙ የኢንደስትሪ ፓረኮች ቁጥር ሰባት ነው። የኢንደስትሪ ፓርኮቹን ቁጥር ወደ 15 ለማሳደግ የታቀደው በዋናነት እ ኤ አ እስከ 2025 ዓ/ም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከሀገሪቱ አመታዊ ምርት 20 በመቶውን፣ ከኤክስፖርት መጠኑ ደግሚ 50 በመቶውን እንዲሸፍን ለማድረግ ነው።

በያዝነው በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ የቂሊንጦ ፋርማሲዩቲካልና ቦሌ ለሚ ቁጥር 2 ኢንደስትሪያል ፓርኮች ስራ ይጀመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በበጀት ዓመቱ ማገባደጃ ላይ ደግሞ የባህር ዳር፣ የጅማ፣ የደብረ ብርሃንና አረርቲ ኢንደስትሪያል ፓርኮች ለምርት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የድሬዳዋና የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርኮች በቀጣይ ተጠናቀው ወደስራ ይገባሉ ተብሎ የጠበቃል።

ያም ሆነ ይህ በ2016/17 የኢትዮጵየን የኢኮኖሚ እድገት 9 በመቶ መሆኑን የገለጸውና ይህ እድገት ሃገሪቱ በድርቅ ተጽእኖ ስር እያለች መመዝገቡን ያደነቀው የዓለም ባንክ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ በተመለከተ ያስቀመጠው መረጃ ትክክል ነው። ከላይ የተገለጹትን እርምጃዎች በመውሰድ የሃገሪቱን የወጪ ንግድ ማሳደግ ካልተቻለ የኢኮኖሚው እድገት ቀጣይነት ፈተና ላይ እንደሚወድቅ ግልጽ ነው። ከላይ የተጠቀሱት የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ይወሰዳሉ ተብለው የታቀዱትና እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ተስፋ ሰጪዎች ቢሆኑም፣ የዘርፉን እድገት አንቀው የያዙ ሌሎች ችግሮች ተፈትሸው መፍትሄ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ማሰብ ተገቢ ነው።

ለምሳሌ የቆዳ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተቋቋሙ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ወደውጭ ከመላክ ይልቅ ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ይመርጣሉ። ይህን ማድረግ የሚያስችላቸው እድል ለማግኘት ከወጪ ንግድ ደረጃ በታች የሆኑ (defective) ምርቶችን እያመረቱ ለሃገር ውስጥ ገበያ ሲያቀርቡ እንደነበረ፤ ይህ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመደረሱ እንዳይበረታታ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች እንዲቃጠሉ መወሰኑ ይታወቃል። ይህ ብቻ አይደለም የወርቅ አምራቾች ለብሄራዊ ባንክ የሚያቀርቡት ምርት በእጅጉ አሽቆልቁሏል። ይህ የሆነው ምርቱ በኮንትሮባንደ ወደውጭ እየተላከ መሆኑን የሚያመለከቱ መረጃዎች አሉ።

የቡና ላኪዎች፣ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ በሃገር ውስጥ መሸጥ የሚመርጡበትን ሁኔታም ተመልክተናል። በዚህ ድርጊት በጥፋተኝነት የተከሰሱ ነጋዴዎችና የስራ ሃላፊዎች አሉ። በአጠቃላይ እነዚህንና ሌሎች ያልተጠቀሱ የወጪ ንግዱን እየተፈታተኑ የሚገኙ ችግሮችን በቁጥጥር ብቻ ለመከላከል መሞከር ብዙም አያስጉዝም። ከዚህ ይልቅ መሰረታዊ ምክንያቶቹን በመፈተሽ ከምንጩ ማድረቅ የዘርፉን ዘለቄታዊ እድገት ለማረጋገጥ አማራጭ የሌለው እርምጃ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው። የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ማነቆዎቹ ተለይተው መፈታት አለባቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy