Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ ያተረፈ ዕድገት

0 303

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ ያተረፈ ዕድገት

                                                        ዘአማን በላይ

በቅርቡ የዓለም ባንክ ሀገራችን ለህዝቦቿ በፍትሃዊነት የምታቀርበውን የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ለሚከናወኑ ስራዎች ማስፈፀሚያ የሚውል የ700 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲሁም ለገጠር የምግብ ዋስትና ማስፈፀሚያ የሚውል የ600 ሚሊዮን ዶላር በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ሰጥቷል።

በእኔ እምነት ይህ ድጋፍና ብድር ከምንም ተነስቶ የተገኘ አይደለም። ምክንያቱም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ድጋፍና ብድር ጨምሮ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ለሀገራችን የሚያደርገው በኢፌዴሪ መንግስት የምትመራው ኢትዮጵያ በትክክለኛ የዕድገት ጎዳና እየተጓዘችና ባለተስፋ መሆኗን በሚገባ ስለተገነዘበ ነው። በተለይ ባለፉት አስር ዓመታት በተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች የተገኙት ለውጦች የሀገራችንን ከፍታ አመላካቾች ናቸው። ከዚህ አኳያ ግዙፍ ከሆኑት ተግባራት ውስጥ ሁለት ምሳሌዎችን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል—የመንገድንና የጤና ዘርፎችን እመርታዎች።

ኢትዮጵያ በዋነኛ የገጠር መንገዶች ግንባታ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውናለች፡፡ በተለይም የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የተገነቡ መንገዶች በርዝመትና በጥራት ቁጥራቸው ማደግ ችሏል፡፡

የመንገድ ጥራትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለግብርናው ዘርፍ ቀጥተኛ ድጋፍ ለመስጠት ትኩረት በመስጠቱ የአስፋልትና የገጠር መንገዶች ግንባታ ዕድገት የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም በሁለቱም የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች የህዳሴውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ መንግስት ለመንገድ ልማት ዘርፍ የሰጠው ትኩረት የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ መላ ሀገሪቱን በመንገድ መረብ ለማስተሳሰርና አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በዋና ዋና የገጠር መንገዶች ግንባታ ስራ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ምንም እንኳን የመንገድ ግንባታ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚጠይቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ዘርፉ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አኳያ የዘርፉን ልማት ለማፋጠን ሲባል የኢትዮጵያን የመንገድ አውታር መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ጋር የማስተካከል ራዕይ ሰንቆ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የመንገድ ስራው ዘርፍ የስራ ዕድልን የሚፈጥር ነው። በአሁኑ ወቅት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቋሚና በጊዜያዊ ስራዎች እድል ተፈጥሮላቸዋል። ይህም ዜጎች ሀገሪቱ በሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው። ይህም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ከመፍጠር አኳያ የራሱን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በባቡር መሰረተ ልማት ረገድ ከነበረው የዝግጅት እና የፋይናንስ አቅም ማነስ አንፃር ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ፍፃሜያቸውን ያገኙት የአዲስ አበባ ጅቡቲ መስመር እና የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የአዋሽ ሃራ ገበያ-መቀሌ መስመር ሥራዎችም በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በመሰረተ ልማት ዙሪያ ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመመደብ ህዝቡ የመሠረተ -ልማት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እና የኢኮኖሚያችን ተወዳዳሪነት አሳድገን ለተጨማሪ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው። ሆኖም ዘርፉ ከሚጠይቀው ግዙፍ ካፒታል አኳያ ችግሮች መስተዋላቸው አልቀረም።

በትራንስፖርት ዘርፍም የፋይናንስና የኘሮጀክት ማኔጅመንት አቅማችን ውሱን በመሆኑ ምክንያት ሰፋፊ ሥራዎች በማከናወን ላይ ብንገኝም ቅሉ፤ የሕዝቡን ሰፊ ፍላጐት ሙሉ በሙሉ ማርካት አልቻልንም። ስለሆነም በቀጣይም ቀደም ሲል የለየናቸው ሦስት ዋና ዋና ማነቆዎች ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የመሠረተ-ልማት ኘሮግራሞቻችን የሚፈልጉት ግዙፍ የፋይናንስና የውጪ ምንዛሪ አቅም ለማሟላት ቁጠባ፣ ኤክስፖርት፣ የሀገር ውስጥ የግንባታና የማምረት አቅም ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ ሌላው የኘሮጀክት ማስፈፀምና ማስተዳደር አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የቅድመ ግንባታ ዕቅድና ዝግጅት፣ ጥናትና ዲዛይን፣ ግዢና ኮንትራት አስተዳደር፣ ክትትልና ቁጥጥር፣ የግንባታና ማማከር አቅም፣ ወዘተ… ያጠቃልላል፡፡

ታዲያ በዚህ ዙሪያ ያለን አቅም እያደገ የመጣ ቢሆንም፤ በዛው ልክ የምንገነባቸው የመሠረተ ልማት ኘሮጀክቶች ግዙፍና ውስብስብ እየሆኑ የመጡ በመሆናቸው እስካሁን የፈጠርነው አቅም ክፍተቶች ቢታዩባቸውም ስኬቶቹ ግን አመርቂዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ኘሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅማችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የተሟላ የአቅም ግንባታ ኘሮግራም ተነድፎ ርብርብ እየተደረገ ነው።

“ማየት ማመን ነው” እንደሚባለው ይህን መሰሉን የመሰረተ ልማት ስራዎች ርብርብን ለማገዝ እንደ የዓለም ባንክ ዓይነት ተቋማት ለሀገራችን ድጋፍና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር መስጠታቸው የሀገራችን ዕድረት ትክክለኛና ህብረተሰቡም በፍትሃዊነት እንዲጠቀም መንግስት ያደረገውን ጥረት የሚያረጋግጡ ናቸው።

በጤና አጠባበቅ ረገድም ኢትዮጵያ ጉልህ ለውጥ አምጥታለች። በተለይ በጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም በመታገዝ በመሠረታዊ የጤና አጠባበቅና ቁጥጥር አገልግሎት ዙሪያ የህብረተሰቡን የተደራጀ ተሳትፎ ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እንዲከናወኑ እየተደረጉ ነው።

በተለይም ጥራቱ የተጠበቀ የሆስፒታል አገልግሎት መስጠቱን ማረጋገጥ፣ ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘም የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል፣ ተቋሞቹም በሰው ሃይልና በቁሳቁስ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት መጠናከራቸውን ማረጋገጥ በዕቅድ ዘመኑ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው ናቸው።

ከጤና በተጓዳኝ የዜጐችን የስነ ምግብ ፍላጐት እንዲሟሉ በማድረግ ጤናማና ምርታማ ዜጋ ማፍራት በሚል የተዘጋጀው ብሔራዊ የሥነ ምግብ ስትራቴጂ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ተሰጥቶት ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በዚህም የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ የማረጋገጥ፣ የእናቶችና ህፃናት እንክብካቤ፣ የጤና አገልግሎት እንዲዳረስ የማድረግና ጤናማ ከባቢ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት ገቢራዊ እየሆነ ነው።

የድህረ-2015 ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ዘላቂ የልማት ግቦች ከሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ተፈፃሚ እየሆነ ነው። ይህም ጥራቱ የተረጋገጠ የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት ሽፋን ወደ 100 በመቶ እንዲደስር ያስችላል። ይህን እቅድ መደገፍና የፋይናንስ ግኝትን ማመቻቸት እንደ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓይነት ተቋማት የሚጠበቅ ነው።

ያም ሆኖ የዓለም ባንክ ለሀገራችን የሰጠው የገንዘብ ድጋፍና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት ያተረፈችውን የዕድገት አመኔታ የሚያሳይ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም የፋይናንስ ተቋማት ሀገራችን እያስመዘገበች ያለችው ዕድገት የህዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው እውን እያደረገ መሆኑን በራሳቸው መስፈርት አረጋግጠው ‘ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል’ ብለው ያደረጉት መሆኑን ለመረዳት አይከብድም። ይህም ኢትዮጵያ ከተደገፈችና ከታገዘች ሌላ አንፀባራቂ ለውጥ ልታመጣ እንደምትችል በፅኑ ከማመን የመነጨ ለመሆኑ የሰሞኑ የባንኩ ድጋፍ ሁነኛ ማረጋገጫ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy