Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ ያተረፈ ማህበራዊ ልማት

0 288

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመኔታ ያተረፈ ማህበራዊ ልማት

 

ስሜነህ

ሃገራችን በአፍሪካ የንግድ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሏት እድሎች እየተፈጠሩ መሆኑን ብዙዎች እያመኑ መጥተዋል። ይህም እምነት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መሆኑን የተመለከተ እና  የውጭ ሃገር ባለሃብቶች በሃገሪቱ ለሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ስራ የሃገሪቱ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን የተመለከቱ፤ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊም ልማታዊም ከመሆናችን ጋር የተያያዙ ናቸው። እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታና አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል።  

ይህ በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንጉ ዘርፍ ላይ የታየው ፈጣን እድገት መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትና በነደፈው አሰሪ ፖሊሲ አማካኝነት መሆኑ ይታወቃል። በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና እንደምትቀጥልና ከስድስት በመቶ በላይ ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧንም እንደምትገፋበት የሚያመላክቱት መረጃዎች ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከአለምአቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ የምጣኔ ሃብት የምርምር እና የጥናት ማእከሎችም ያረጋገጡት ነው።

በሃገሪቱ እየታየ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እድገት የተለያዩ የውጭ ባለሃብቶችን ትኩረት እንዲስብ ካስቻሉ እና ከላይ ከተመለከቱት በርካታ ምክንያቶች  በተጨማሪ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ውጤት የሆነው የመሰረተ ልማት እድገታችን ነው።

ሃገሪቱ ፈርጣማ ኢኮኖሚ ይኖራት ዘንድ በተለይ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርት፣ በኃይድሮ ፓወር፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በመሳሰሉት ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን ማግኘት ግድ ይላታል፡፡ ይህም የሚሆንበት አቢይ ምክንያት የኢኮኖሚ ዕድገቱ በአስተማማኝነት የሚቀጥለውና ሃገሪቱም መለወጥ የምትችለው፣ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግና ማስተናገድ ሲቻል ብቻ ስለሆነ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው በ2016 የአፍሪካ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የቀነሰ ሲሆን የኢትዮጵያን ለብቻው ነጥለን ስንመለከተው ግን 46 በመቶ ጨምሮ ይገኛል። ድርጅቱ የአውሮፓውያኑን የ2017 ኢንቨስትመንት ትንበያን በተመለከተ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳመለከተው ያለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ማለትም ከጥር ወር 2008 እስከ ታህሳስ 2009 ድረስ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መጠን ያለው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝታለች። በአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ተቀባይ ሆና የቆየችው እና በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችው አንጎላ 2016 ላይ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን አሽቆልቁሏል። በአህጉሪቱ ትልቁን ኢኮኖሚ የያዙት ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያም በዚሁ ዓመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ግኝታቸው ከነበረበት ወርዷል። ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጠንካራ እድገት የታየበት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ሲል ያላየችው መሆኑን ተመድ በሪፖርቱ ገልፇል። በ2016 በምስራቅ አፍሪካ 7.1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የተገኘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን የወሰደችው ኢትዮጵያ ነች።

በአጠቃላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከቀደመው ዓመት በ46 በመቶ እድገት አሳይቷል። ይህም አፈፃፀሟ በዓለም ላይ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ከሚገኙ አገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ የምታገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን እድገት የተቀጣጠለው አገሪቱ ለመሰረተ ልማት እና ለማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፎች እያዋለችው ያለችው መዋዕለ ንዋይ መሆኑን የተመድ ሪፖርት አስታውቋል። እንደ ሪፖርቱ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ በሚገኙ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቢያ የተፈጥሮ ሀብት ነው። ነገር ግን አገራት የኢንቨስትመንት አማራጫቸውን ዓይነት አስፍተው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ባደረጉት ጥረት እየተሳካላቸው ነው ሲልም ኢትዮጵያን በምሳሌነት አስቀምጧል።  

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች አሉ። የሃገሪቱ የተረጋጋ ፖለቲካና ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ሰፊ የሰው ኃይል እና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ በዋናነት የሚጠቀሱት ናቸው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲን የምትከተል በመሆኗ በኢነርጂው ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉም ሰፊ እድል አለ። በተለይ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ሃገራችን የሄደችባቸው ስኬታማ ርቀቶች የአለም የገንዘብ ተቋማትን አመኔታ እንድታገኝና የበለጠ እንድትተጋ የሚያስችላትን እድል ፈጥሮላታል።

በዚሁ መነሻም አገራችን ለህዝቦች በፍትሃዊነት የምታቀርበውን የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ለሚሰሩ ስራዎች ማስፈፀሚያ የሚውል 700 ሚሊዮን ዶላር በቅርቡ ከዓለም ባንክ ድጋፍ ያገኘች ሲሆን፤ በተጓዳኝ  ለገጠር የምግብ ዋስትና ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ 600 ሚሊዮን ዶላር በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር አግኝታለች። ይህም የሚያሳየው በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላት አመኔታ እየጨመረ የመጣ መሆኑን ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት ጉዟችን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለማዳረስ በመቻሉ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ተቋማት ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችና 3ሺ 300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የደረሰ ሲሆን፤ ከ27 ሚሊዩን በላይ ተማሪዎችንም ማስተናገድ ተችሏል። በዚህም እቅዳችንን በልማታዊ አቅጣጫ መርተን መሰረታዊ ለውጥን ማምጣታችን ለሌላው ዓለም ምሳሌ መሆን የምንችልበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። የአንደኛ ደረጃ ተሳትፎን ከ96 በመቶ በላይ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኩልም በውስን አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን ስርጭት በማስፋፋት ተሳትፎውን ከ43 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን፤ በመሰናዶ ትምህርት ፕሮግራም ከግማሽ ሚሊዩን በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ መሆናቸው፤ በየዓመቱ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃውንና ተገቢውን የማለፊያ ውጤት እያስመዘገቡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የተማሪዎች ቁጥርም ወደ 200ሺህ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ድንቅ ውጤት ያስመዘገብንበትና በገንዘብ ተቋማቱ አመኔታን ያተረፈልን የጤናው መስክ ነው። የጤና ፖሊሲያችን በዋናነት በሽታን በመከላከል ላይ የሚያተኮር ቢሆንም ከዚሁ ጐን ለጐን መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን የማስፋፋቱም ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎችን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለማስፋፋት በተደረገዉ የተቀናጀ ርብርብ በ1983 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 153 ብቻ የነበረው የጤና ጣቢያዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ3ሺ 500 በላይ ደርሷል። ለ25ሺ ህዝብ አንድ የጤና ጣቢያ ለማዳረስ የተያዘውን ግብ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን የሚገልጹት የጤና ጥበቃ ሚንስቴር መረጃዎች፤ የጤና ተቋማቱን አገልግሎት የማሻሻልና ግብአቶችን የማሟላት ሥራም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ያረጋግጣሉ።

በ1996 ዓ.ም ተቀርፆ ሥራ ላይ የዋለው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻልና በሽታን በመከላከሉ ስራ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክቷል። በመላ ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ የተሰማሩ ከ39ሺ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጐችን ለመፍጠር የተነደፈውን ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። በሁሉም የአገራችን የገጠር ቀበሌዎች ቢያንስ አንድ የጤና ኬላ የተገነባ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16ሺ 251 የሚበልጡ ጤና ኬላዎች ለህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ።

መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የሆስፒታል አገልግሎትን ለማሻሻልም አቅም በፈቀደ መጠን ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በ1983 ዓ.ም 72 ብቻ የነበረው የሆስፒታሎቻችን ቁጥር፤ በአሁኑ ወቅት በግሉ ዘርፍና በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሰሩትን ሳይጨምር የመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ ቁጥራቸው በአራት እጥፍ አድጎ ከ310 በላይ ደርሷል።

ከላይ በተመለከተው መልኩ ሃገራችን ከአለም ባንክ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ በድጋፍና በብድር መልክ ሊገኝ የቻለው መንግስት ትምህርትን፣ ጤናን፣ ግብርና፣ ንፁህ ውሃን እና የገጠር መንገድን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ እያደረገ ያለው መጠነ ሰፊ የልማት ጥረት እና በዚህም እየተገኘ ያለው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን በባንኩ መስፈርቶች መሠረት ሊረጋገጥ በመቻሉ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለሆነም በዚህ ባለመዘናጋት ከዚህ ለበለጠ ድጋፍና እርዳታ በገንዘብ ተቋማት ዘንድ አመኔታን ሊያተርፉ በሚያስችል አግባብ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ እና ከኪራይ ሰብሳቢነት በጸዳ መልክ መፈጸም ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy