Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጋራ ሰላም ይቅደም

0 555

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጋራ ሰላም ይቅደም

                                                                                      ይልቃል ፍርዱ

የሀገርና የሕዝብ  ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሰላም ለሀገር ልማትና እድገት ዋነኛው ምሰሶና መሰረት ነው፡፡ ሰላም በአለማችን ትልቅ ዋጋ ያለው በምንም አይነት መስፈርት ሊሰፈርና ሊለካ የማይችል ነው፡፡ ስለሰላም ውድና መተኪያ የሌለው ዋጋ ለማወቅ በሰላም እጦት የሚሰቃዩትን ሀገራትና ሕዝቦች መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ሶርያ፣ የመን፣ ሊቢያና ሌሎችም የቅርብ አመታት ምስክሮች ናቸው፡፡

በሀገራትና በሕዝቦች መካከል ሰላም እንዳይኖር የሚሰሩ፤ የተለያየ አላማና ፍላጎት ያላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የእነዚህ መሰረታዊ ግብና አላማ በሚደፈርሰው ሰላም፣ በሚፈጠረው ሁከትና ትርምስ መካከል የራሳቸውን ጥቅምና የፖለቲካ ፍላጎት መጠበቅና ማስጠበቅ ነው፡፡ በአለማችን ላይ ከዚህም በላይ ተከስቶ ታይቶአል፡፡

የተለያዩ አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ በሚቀሰቅሱት፣ በሚያነሱት ሁከትና ብጥብጥ ግጭት እንዲፈጠር፣ ሁኔታው መልኩን ቀይሮ ወደከፋ ትርምስ እንዲለወጥና እንዲሰፋ በማድረግ የሕዝብ እልቂትን የሀገራቱን መሰረታዊ ልማት የማፈራረስ፣ ኢኮኖሚያቸውን ሙሉ በሙሉ ሽባ አድርጎ የመግደል፣ ሠራተኛውን ሕዝብ ከስራ ተፈናቅሎ ለከፋ ችግር እንዲዳረግ የማድረግ፤ በእርስ በእርስ ግጭቱና ትርምሱ መሀል ታሪካዊ ቅርሶችን የመዝረፍ ወንጀለኛ ስራ ሁሉ ሲሰሩ ኖረዋል፡፡ አለም አቀፍ ማፊያዎችም ሁከትና ትርምስ ባለባቸው ሀገራት ለመዝረፍ ሲሉ ፈጥነው ነው የሚገቡት፡፡

የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በዘረፋ የማጋዝ በዚሁም በብዛት የጦር መሳሪያዎችን ከውጭ በማስገባት ንግዱን ማጧጧፍ የግጭት ደረጃው ከመጠን በላይ እንዲሰፋና እንዲለጠጥ በማድረግ ሕዝቡን እርስ በእርሱ ማፋጀት እነዚሁ ወገኖች ከሚከተሉዋቸው ሀገራትን የማፈራረስ ስልቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የውጭ ኃይሎች በሀገር ውስጥ ካሉት ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የሕዝቡን ችግሮች በማጉላትና በመቀስቀስ ወጣቱን በስፋት በስሜታዊነት እንዲሰለፍ በማድረግ በጥፋት አቅጣጫ እንዲነጉድ እየቆሰቆሱ በመንዳት ሕዝቡ ባላሰበውና ባልገመተው መልኩ ሰላሙን ተነጥቆ ሀገሩም ፈራርሳ መጠጊያና መሸሸጊያ አጥቶ ሀብትና ንብረቱ ወድሞ የልጆቹንም ሕይወት አጥቶ መንደርና ቀኤውን ለቆ እንዲሰደድ የሆነበትን ሁኔታ  ተከስቶ አይተናል፡፡

የሀገር ሰላም ማጣትና መደፍረስ ከግለሰብ ጀምሮ የቤተሰብን፤ ከዛም አልፎ የሕዝብን ሕይወትና ኑሮ ያደፈርሳል፡፡ የሕዝብ ሕይወት ሲናጋና የሀገር ሕይወትመ አብሮ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ ጥንታዊ የነበሩትን እነሶርያን፣ ሊቢያን ያፈራረሱዋቸው በዚህ መልኩ ነው፡፡

ቀድሞ በነበረው ሁኔታ ኃያላን ሀገራት በማይመለከታቸው የሌሎች ሀገራት ጉዳይ እየገቡ ሲያሻቸው የእግረኛ ሠራዊት በማሰማርት፣ በል ሲላቸውም የአየር ድብደባ በማድረግ የየሀገራቱን መሰረታዊ ልማት፣ የኢኮኖሚ አውታሮች፣ ፋብሪካዎች፣ መንገዶችና ድልድዮች በጀት ድብደባ እንዳልነበረ አድርገው ሲያፈራርሱት ኖረዋል፡፡

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ መልሶ ለመገንባት እርዳታ እናደርጋለን፤ እኛው እንገባለን ብለው እነሱው ሞግዚት ሁነው ከሚያቋቋሙት መንግስት ጋር ተደራድረው በከፍተኛ ደረጃ ውልም ተፈራርመው በብዙ ሚሊዮኖች የሚያገኙበትን ፕሮጀክት ዘርግተው ያንኑ ያወደሙትን ሀገር መልሰን እንገነባለን ብለው ይገባሉ፡፡ ፋብሪካውን፣ ድልድዩን፣ መንገዱን፣ የኤሌክሪክ ማከፋፈያውን፣  ትምህርትቤቱን፣ ሆስፒታሉን . . . ሊሰሩ ዳግም ድሀ ሀገራትን ሊዘርፉ አሰፍስፎ መሰማራት የዘወትር ስራቸው ነው።

ጥያቄው እነዚህን የሕዝብ መገልገያዎች ቀድሞስ ቢሆን ለምን ማፍረስ አስፈለገ? የሚለው ነው፡፡ አጭሩ መልስ ለእነሱ አፍርሶና አውድሞ እንደገና እንሰራዋለን ማለት በብዙ ሚሊዮኖች የሚዘርፉበት ንግድ ስለሆነ ነው፡፡ በሀገር ውድመት፣ በሕዝቡ ስቃይ፣ መከራ፣ ሞትና ስደት  ውድቀት እነሱ ይከብሩበታል፡፡ የእዚያ ሀገር የእነሱ ተላላኪና አጋፋሪ፤ የራሱን ሀገር አውድሞ፣ ሕዝቡን አስጨርሶ ያጫፍራል፡፡ እሱም አልመች ሲላቸው ማጥፊያ መንገድ ይፈልጉለታል፡፡

የወጭ ኃይሎች እንዲህ እንዲህም ነበሩ፤ አሁንም ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የራሳቸውን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ያከብራሉ፤ ያስከብራሉ፡፡ ሌላው ሀገር ጠፋ፤ ወደመ፤ ለእነሱ ደንታቸው አይደለም፡፡ ለሀገሩ መጠበብና መጨነቅ፤ ሀገሩን ከጥፋትና ከወድመት መከላከል ቀዳዳ አለመክፈት ያለበት የራሱ ሀገር ባለቤት የሆነው ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ከሀገራት ወድቀትና መፈራረስ ብዙ ተምረናል፡፡ እንዲህ አይነቱ አስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ በሀገሩ ተከስቶ ማየት የሚፈልግ ሕዝብ የለም፡፡ ሕዝብ ሰላሙን አጥብቆ ይሻል፤ ይጠብቃል፡፡ የሰላም ዋጋ ምን ያህል የከበረ መሆኑንም አሳምሮ ያውቃል፡፡

ሰላም ከሌለ ሰርቶ አግኝቶ መግባት አይቻልም፡፡ በሰላም ሰርቶ ውሎ መመለስም የለም፡፡ ሕዝብም ሀገርም አደጋ ላይ ይወድቃሉ፡፡ ይሕ እንዳይሆን እንዳይከሰት ነው ሕዝብ ለሀገሩ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ የሰላም ዋጋ በገንዘብ አይሰላም፡፡

የቱንም ያህል የፖለቲካ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ቢኖሩ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም በማሰብ፤ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት በተመላበት መንገድ በመነጋገር፤ በመደማመጥ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት ነው ሊፈቱ የሚገባቸው፡፡

ከዚህ ውጭ ያለው የእልህ መጋባትና የማነህ ማነህ መንገድ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚሉት አይነት በእርስ በእርስ ትንቅንቅ ሀገርን  ለማፍረስ አሰፍስፈው ለሚጠብቁዋትና ውድቀትዋን ለሚመኙት የውጭ ጠላቶች አሳልፎ ከመስጠት ውጭ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ በኋላ፤ የፈሰሰ ውሀ አይታፈስ እንዲሉ፤ እዬዬ ቢባል መመለሻ የለውም፡፡ ቀድሞ ነው መጠንቀቅ የሚገባው፡፡

በሀገር ጉዳይ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም፡፡ የጋራ፤ የሁሉም ቤት ስለሆነች፡፡ ለዚህ ነው ስልጡን የሆነ የፖለቲካ መፍትሔ ማስቀመጥ መከተል የሚገባን፡፡ ልዩነት ውበት እንጂ በጠላትነት የሚያፈራርጅ መሆን የለበትም፡፡ ልዩነት የብዝሀነት መገለጫ ብቻም አይደለም፤ ውበትም ጥንካሬም ጭምር ነው፡፡

ልዩነትን መፍታት የሚቻለው በመከባበርና በመደማመጥ መንፈስ ብቻ ነው፡፡ መደማመጥ፤ መከባበር፤ ልዩነትን በልዩነት ይዞ የጋራ በሚያደርጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም ለሀገር ሰላም ልማትና እድገት በጋራ መስራት፤ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ፤ ሰላምን መልካም አስተዳደርና ፍትሕን ማስፈን፤ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ የሀገር ሰላምና መረጋጋት የሚከበረውና የሚጠበቀው በሕዝብ ነው፡፡ ሀገር የጋራ፤ የሕዝብ ናትና፡፡

በሕዝብ መሀል መናቆርና መጋጨት እንዲፈጠር ተግተው እንቅልፍ አጥተው የሚሰሩ መርገምቶች ያሰቡት አይሳካላቸውም፡፡ የሀገርና የሕዝብ ሰላም ስለሚቀድም ሁሉም ወገን መቆም ያለበት በቅድሚያ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ብቻ ነው፡፡ ዙሪያዋን በጠላቶች በተከበበች ሀገር የውስጥ እሳት መቆስቆስም ሆነ መጫር ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ለጠላቶችዋ ሲሳይ እንድትሆን ከማድረግ ውጪ የሚጠቅም ምንም ነገር የለውም፡፡

ይህንን እኩይ ሴራ መመከትና ማጋለጥ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ሰላምና ደሕንነት መጠበቅ፣ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠልና ለውጤት ማብቃት የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም የጋራ ሀገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ከሀገር ሰላም በፊት የሚቀድም ሌላ ምንም ጉዳይ የለም፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy