Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የግጭት ተፈናቃዮችን መርዳት ኢትዮጵያዊ ባህል ነው!

0 473

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የግጭት ተፈናቃዮችን መርዳት ኢትዮጵያዊ ባህል ነው!

                                     ደስታ ኃይሉ

ኢትዮጵያዊያን እንኳንስ የራሳቸውን ዜጋ ቀርቶ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ጎረቤቶቻቸውን በመርዳት የሚታወቁ ናቸው። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተከስቶ በነበረው ግጭት ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መርዳት የኢትዮጵያዊያን ባህል መሆኑን ህዝቡ እንደሚገነዘበው እርግጥ ነው። በሁለቱም ክልሎች ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን በማገዝ ኢትዮጵያዊያን ባህላችንን ለሌላው የዓለማችን ክፍሎች ማሳየት ይኖርብናል።

ግጭት ለየትኛውም ህዝብ እንደማይጠቅም ህዝቡ ያውቃል። ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም። በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደር ችግር፣ ከሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው። በክልሎች በተካሄዱ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ከህዝቡ በተገኘው ግብዓት መሠረት ጥፋት በፈፀሙ አመራሮች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

እርምጃውን በጥልቀትና በስፋት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት የግድ ነው። የህልውና ጉዳይም ነው። ምክንያቱም ችግሩ በቅርቡ በተወሰኑ የሃገራችን አካባቢዎች ለሰላም እና መረገጋት መጥፋት መንስኤ ሆኖ ተስተውሏልና። ሰላም ደግሞ የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸው የግድ ነው። እነዚህ የተጀመረውን የሠላም፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ኃይሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ሰላማችንን ለማድፍረስ፣ የዕድገት ግስጋሴያችንን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና ማለታቸው በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባበቢዎች የተከሰቱት ድርጊቶች ሁነኛ አስረጅዎች ናቸው።  

ያም ሆኖ ምክንያቶችን መድፈን ይገባል። ቀዳዳዎችን ያለ አንዳች ሽንቁር መድፈን የግድ ይላል። ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ወሳኝ ነው። ይህን ለመከወን የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና የማይፈልጉ፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ የጥፋት ኃይሎች ፖለቲካዊ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በቁርጠኝነት መታገል ይገባል።

በተለይም ግጭትን ቦታ ለማሳጣት የትምክህትንና የጥበት አራማጆችን መታገል የግድ ይላል። እንደሚታወቀው በትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ የተጠመቁ ኃይሎች ከሁሉ በላይ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ብዝሃነትን አጥብቀው ይጠላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሉ የእኔ ብሄር ብቻ ልዕለ ኃያል የሆነ፣ ቋንቋዬ፣ ባህሌና ማንነቴ ከሌላው የሚበልጥና የተለየ፣ ሁሌም ለመግዛት የተፈጠ ርኩ ነኝ ብሎ ያምናል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐንም ሌላውን ብሔርና ዜጋ ተራና ርካሽ፣ ለመመራት እንጂ ለመምራት ያልተፈጠረ ቋንቋው፣ ባህሉና ማንነቱ የወረደ አድርጐ ይቆጥረዋል፡፡ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትንም አይቀበልም። ስለሆነም ብዝሃነትን ደፍጥጦ የራሱን አስተሳ ሰብ፣ ቋንቋና ባህል በሌላው ላይ ለመጫን የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

ይህ ካልሆነ ሀገር ትጥፋ ህዝብም ይለቅ የሚል ህሳቤም የተጠናወተው ነው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔርተኝነትን የማይቀበል፣ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የግዛት አንድነት የሚያሳስበው ኃይል ነው። ከህዝብ ይልቅ ተራራና ወንዝ የሚናፍቅ ፀረ ህዝብ አመለካከት የተጠናወተውም ነው። የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የሆነው ጠባብነትን የተላበሰ ኃይል ደግሞ ሁሉንም ለእኔ እና ለእኔ ብቻ ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ሁሉ በጠባብነት መነፅር የሚመዝን የዚህ ዓለም ዕውነታ የሆነውን ብዘሃነትን ተቀብሎና ተቻችሎ መኖር የእሬት ያህል የሚጎመዝዘው ኋላ ቀር አሳቢ ነው። በጠባብነት ድንበር የታጠረ እንደመሆኑ መጠንም ከሱ ብሔር ውጪ ያለ ህዝብ በአካባቢው እንዳይኖር ሌላ ቋንቋ እንዳይነገር ይሰብካል፡፡ ያስባል፡፡ ያልማል፡፡

ይህ የጥበት ሃይል በመስበክ ብቻ ራሱን አያቅብም፡፡ የብሔሩ አባል ሌላውን በጥላቻና በጥርጣሬ እንዲመለከተው ዕድሉ ሲመቻችለትም እንዲያጠቃና እንዲያጠፋው ተግቶ ይሠራል፡፡ በአኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አይቀበልም። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፀር በመሆን ባይሳካለትም ሌላውን ዜጋ ለመጨፍለቅ ሲሞክር ይስተዋላል፡፡ ታዲያ የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፅኑ ጠላት የሆኑትና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው ሃገሮች ፈጽሞ ሊሠሩ የማይችሉት እነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች፤ በአሁኑ ወቅት በሰላማችንና በልማታችን ላይ የተደቀኑ እንቅፋትና ጋሬጣዎች መሆናችው ፍንትው ብሎ እየታየ ነው፡፡

ግጭት እንደ እኛ ያለና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መርስቶ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን ለመገንት በሕገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ያሰፈረ ህዝብ ውስጥ ቦታ የለውም። የ‘ከዚህ ወዲህና ወዲያ’ አስተሳሰብ ቦታ ሊኖረው አይችልም። እዚህ ያለው እዚያ ሄዶ የመስራት፣ እዚያ ያለው እዚህ መጥቶ ካልሰራ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊያመጡት ያሰቡት አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ሊገነባ የሚችል አይመስለኝም።

እናም አንድ በምጣኔ ሃብት የዳበረ ማህበረሰብ ለመገንባት በኢትዮጵያ ሶማሌ ውስጥ ያለው ዜጋ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውም የኢትዮጵያ ሶማሌ ሄዶ መስራት ይኖርበታል። ማንኛውም ዜጋ በየሄደበት በየትኛውም ክልል ተዘዋውሮ መስራት አለበት። ምክንያቱም ዜጎች የመንቀሳቀስና በየትኛውም ክልል ሄዶ ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብት ስላላቸው ነው።

ህዝቦች በጋራ ሰላም የመሆን፣ በጋራ የመልማትና የማደግ፣ በጋራ ዴሞክራሲን ለማጎልበት እምነትና ፈቃዳቸውን በሕገ መንግስታቸው ላይ ሳይቀርገልፀው ሲያበቁ፤ በጥላቻና ላይ በተመሰረተ የጥቂት ታጣቂዎችና የበታች አመራሮች ፍላጎት እውን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አስተሳሰቡ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ቦታ የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሊፈቅዱት ስለማይችሉት ጭምርም ነው። ለዚህም ነው በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ሲናገሩ ‘እዚያ ማዶና እዚህ ማዶ ያሉት ህዝቦች መጋጨት እንደማይፈልጉ ደጋግመው ነግረውናል’ በማለት የገለፁት።     

ታዲያ እዚህ ላይ ‘የክልሎች ወሰን መካለል የለበትም’ እያልኩ አለመሆኑን ውድ አንባቢያን ግንዛቤ ይይዙልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸው መገለጫ በሆነው ሕገ መንግስት መግቢያ ላይ “…የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን…” በማለት የገለፁበት አግባብ ቀደም ሲልና አሁን ይኖሩበትና እየኖሩበት ያሉበት ወሰን ያላቸው መሆኑን ያመላክታል። ምናልባትም በቀደምት አስተሳሰቦች ሳቢያ የተፋለሱ የድንበር ማካለል ካለም፤ ይህ ሁኔታ በራሳቸው የውሳኔ ድምፅ አማካኝነት የሚቃለል ይሆናል። በዚህ አሰራር መሰረትም ችግሮች ይቀረፋሉ። ያም ሆኖ ህዝቡ በተለመደው ኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት ከየትም ቦታ ለሚፈናቀል ዜጋ ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል አለበት። እንዲህ ዓይነቱ በችግር ወቅት አነዱ ለሌላኛው የመድረስ ባህል የኢትዮጵያዊ ባህል መገለጫ መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy