Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፋይናንስ ስርአቱን ለማዘመን

0 1,261

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የፋይናንስ ስርአቱን ለማዘመን

ዮናስ

የመካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ዘርፍን ምርታማነት ለማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጎልበት በመንግስት በኩል የተለያዩ ድጋፎች የተደረጉ ስለመሆኑ የሚያወሱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ አንዳንዶቹ በተለይም ነባሮቹ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች አቅማቸው ቢዳብርም የተጠበቀውን ውጤት አላስገኙም። ለዚህ የሚጠቀሰው ምክንያት የቴክኖሎጂ ቀርነቱ በምርት ጥራት ላይ ጉድለት ማስከተሉ እና የፋይናንስ ስርአቱ አካታች አለመሆኑ ነው። በዘርፉ የሚታየው የሃይል አቅርቦት ውስንነት፣ የመሠረተ ልማት አለማሟላት፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል ክፍተት ዋንኛ ማነቆዎች ሆነው በጥናቶቹ ተመልክተዋል። እነዚህን ለመፍታት ባለፉት አምስት አመታት ርብርብ ተደርጓል። ነገር ግን ዘርፉ ላይ ጎልቶ የሚታይ ለውጥ አሁንም አልመጣም።

የመካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ኢንቨስትመንት የማስፋት፣ ከአነስተኛ ኢንዱስትሪ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ እየተሸጋገሩ ያሉትን የማበረታታት፣ ከተለያዩ ዘርፎች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ሽግግር የሚያደርጉ ባለሃብቶችን በበቂ ሁኔታ በተለይ በፋይናንስ ያለመደገፍ በመንግስት በኩል የሚታዩ ውስንነቶች ናቸው። በሽግግር ሂደቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ ልማታዊ ሀገራዊ ባለሃብቶችን ማበራከት የሚቻለው የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በማደረቅና ለልማታዊ ባለሃብቱ ሁሉአቀፍ የሆነ ድጋፍ ማድረግ ሲቻል ነው። አለበለዚያ የሚሉት ጥናቶች በዘርፉ የሚፈለገው ለውጥ በፍጥነት ማምጣት አይቻልም። የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ክላስተሮች ግንባታ በጥራትና በፍጥነት በመፈፀም ሀገር በቀል ባለሃብቶችን ለማበረታታት አይቻልም።

ልማታዊ ባለሃብቱን በስፋትና ከበቂ ድጋፍ ጋር ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቆርጦ እንዲገባ በማድረግ ረገድ አመራሩ ጋር የሚታየው የያዝ ለቀቅ አካሄዱን መቀየር አለበት። በዘርፉ ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚደረገው መንግስታዊ ድጋፍ ከለላ በማድረግ አመራሩ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዝንባሌና ተግባር መጋለጥ የለበትም። በዘርፉ የሚስተዋለው የአቅም፣ የክሂሎት፣ የአመለካከትና የፋይናንስ ችግሮችን መፍታት የተሃድሶ መስመሩ ቁልፍ አጀንዳዎች መሆናቸው በመንግስት በኩል ተመልክቷል።

የተሃድሶ መስመሩ ሌላኛው ማነቆ የወጪ ንግዳችን በተፈለገው ጥራትና ፍጥነት በብዛት በአለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ በመሆን የውጪ ምንዛሬ ፍላጎታችንን ሊያረካ በሚችል ረገድ እየተፈፀመ አለመሆኑ ነው። የኤክስፖርት ዘርፋችን በከፊል ከግብርና በማላቀቅ በከፊል እሴት ተጨምሮባቸው ያለቀላቸውን ምርቶችን ወደ አለም ገበያ ማቅረብና የውጪ ንግዳችን አቅርቦት አይነትና መጠን የመጨመር እቅዳችን በተፈለገው መንገድ የተሰራ አይደለም።

ከአለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ የሚታይ ቢሆንም የምርቶቻችንና መጠን፣ አይነት ላይ የጎላ ለውጥ ባለመፈጠሩ በውጪ ምንዛሪ ግኝታችን ላይ ተፅእኖ አሳድሯል። የፋይናንስ ስርአቱ ደግሞ ሌላኛውና ዋነኛው ማነቆ ነው። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የወጪ ንግድ ከአጠቃላይ የሃገር ውስጥ የሚኖረው ድርሻ 22.5 በመቶ /በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን/ ቢሆንም የተደረሰበት ውጤት 13.7 በመቶ ነው። በአንፃሩ የገቢ ንግዱ 30.4 በመቶ  በመሆኑ ክፍተቱ ከ16 በመቶ በላይ ያደርገዋል። ይህን ክፍተት ለማጥበብ የወጪ ንግዳችን አይነት፣ መጠንና ስብጥር መጨመር አንድ ነገር ሆኖ በጥራት ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘትም ግድ ይላል። ይህ የሚፈታው ደግሞ በሁለት አቅጣጫ እንደሆነ ተቀምጧል። የሃገር ውስጥ የቁጠባ መጠንን በማሳደግና የውጪ ንግዳችን ተወዳዳሪና ተደራሽ በማድረግ።

ሀገራዊ የቁጠባ አቅማችንም በብር ብቻ ሳይሆን በውጪ ምንዛሬ መካሄድ ስለሚኖርበት የውጪ ንግዳችን ስራ የተሃድሶ መስመሩን ለማስቀጠልና ወደ ምንፈልገው ኢንዱስትራላይዜሽን የምናደርገውን ሽግግር ለማፋጠን አስቻይ ሁኔታም ስለሆነ ጭምር ነው። ስለዚህም የወጪ ንግድ ስራችን ለማሻላል፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ በዘርፉ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች የተለያዩ ድጋፎችና ማበረታቻዎች እየተሰጡ ቢቆዩምና ጎልተው የሚታዩትን ማነቆዎች መፍታት ግን አጣዳፊ የቤት ስራ ነው። እነሱም ተወዳዳሪነት፣ ጥራት፣ የወጪ ንግድ ስብጥርን ማብዛትና የፋይናንስ ስርአቱን አካታች በማድረግ ምርታማነትን ማጎልበት፤ በዚህም የዘርፉን አሠራር ፍፁም ከኪራይ ሰብሳቢነት ማፅዳትና ማዘመን ናቸው።

በዚሁ መነሻ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን ለማስፋፋትና ለማሳደግ የተቀረፀው ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ይፋ ተደርጓል። የስትራቴጂው ዓላማ ሁሉን አቀፍና ዘመናዊ የሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንድሁም በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡ አመቺና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የፋይናንስ አገልግሎቶችን በፈጠራዎች በመታገዝ ለሁሉም ግለሰቦችና ድርጅቶች ተደራሽ ማድረግ ነው።

ስትራቴጂው በዋናነት በገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች የፋይናንስ ተቋማት እንዲስፋፉ እና መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ዜጎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል። ከላይ በተመለከተው አግባብ ጥናቶቹ የሚያመለክቱት በኢትዮጵያ የመደበኛ ፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ነው። ለዚህም አራት ምክንያቶች የተጠቀሱ ሲሆን የመጀመሪያው የፋይናንስ እና ተዛማጅ መሰረተ ልማቶች አለመዳበርና አለማደግ የሚለው ነው።

በሌላ በኩልም የፋይናንስ ምርቶችና አገልግሎቶች ጥራትና የአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች ርቀት የተጠቃሚውን ሁኔታ ያገናዘቡና ያማከሉ አለመሆናቸው፤ ተገልጋዩ በተለይም በገጠሩ ክፍል የሚገኘውንና አነስተኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ ለፋይናንስ ስርአት ያለው እውቀትና ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን እና በቂ የፋይናንስ ተገልጋዮች ጥበቃ አለመኖር በሀገሪቱ መደበኛ ያልሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉም ሌለኞቹ ምክንያቶች ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በአለም ባንክ በተደረገ ጥናት በ2007 ዓ.ም በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ የሆኑ ጎልማሶች ብዛት 22 በመቶ ብቻ መሆኑን ያሳያል፤ ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አማካይ 34 በመቶ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው። በጥናቱ ከተካተቱ ጎልማሶች መካከል 78 በመቶዎቹ አነስተኛ ገንዘብ ለመበደርም ሆነ ለመቆጠብ ወደ መደበኛ ባንክ አይኬድም የሚል የተሳሳተ አለመካከት አላቸው። 12 በመቶዎቹ ደግሞ የፋይናንስ አገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች ርቀት አገልግሎቱን እንዳይጠቀሙ እንዳደረጋቸው ነው ጥናቶቹ የሚያመለክቱት። የተለያዩ እና ተስማሚ የፋይናንስ አገልግሎት መስጫ መዳረሻዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር የፋይናንስ ተደራሽነቱን ውስን እንዳደረጉት ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ይገኙበታል።  ለአብነትም 35 በመቶ የባንክ እና 54 በመቶ የመድን ሰጪ ቅርንጫፎች በአዲስ አበባ የተከማቹ በመሆናቸውና የተቀሩትም በዋና ከተሞች ላይ ብቻ መገኘታቸው የፋይናንስ ተደራሽነቱ ላይ ተፅዕኖ ፈጥረዋል።

የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥና የተንቀሳቃሽ ስልክ ኔትዎርክ ጥራት ማነስ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚከናወኑ የፋይናንስ ግብይቶች አስተማማኝ እንዳይሆኑ እንቅፋት መሆናቸውም ሌለኞቹ ተግዳሮቶች መሆናቸው ይህን ስትራቴጂ ለመንደፍ ምክንያት ሆነዋል።

ከዚህም ባሻገር የብሄራዊ የመታወቂያ ካርድ ስርአት ተግባራዊ ባለመሆኑ የፋይናንስ ተቋማት የደንበኞቻቸውን ማንነት በግልፅ ለመለየት፣ ተያያዥ ስራዎችን ለማሻሻል፣ ሂሳብ ለመክፈትና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ስጋቶችን ለመቀነስ አለመቻላቸውም ሌላኛው በፋይናንስ ተደራሽነቱ ላይ ጫና የፈጠረ ጉዳይ ነው። በዋጋና በጥራት ተስማሚ የሆኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለምሳሌ ቁጠባ፣ ብድር፣ ክፍያ፣ ሀዋላ እና የመድን አገልግሎት በሰፊውና በበቂ ሁኔታ ያለማቅረብ የሃገሪቱ የፋይናንስ ስርአት ላይ የሚታዩ ዋነኛ ማነቆዎች ናቸው።
በመንግስት የሚፈፀሙ እንደ ደመወዝ፣ የጡረታ፣ የሴፍቲኔት እና ሌሎች ክፍያዎች በጥሬ ገንዘብ የሚፈፀሙ መሆናቸውም ይታወቃል።

እነዚህ ክፍያዎች በተጠቃሚው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ቢደረጉ ግን የፋይናንስ አካታችነትን የበለጠ ለማስፋት እና የቁጠባ ባህልን ሊያሳድግ እንደሚችል ይፋ በሆነው ሰነድ ላይ ተመልክቷል። በኢትዮጵያ የዳበረ የቁጠባ ባህል ቢኖርም አብዛኛውን ድርሻ የያዘው ባህላዊ የቁጠባ አይነት እንደሆነ የሚያመለክተው ሰነድ፤ በሀገሪቱ 48 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች የሚቆጥቡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ መደበኛ ተቋማትን የሚጠቀሙት 14 በመቶ ብቻ ናቸው፤ ቀሪዎቹ ማለትም 34 በመቶዎቹ ግን ባህላዊ የቁጠባ ዘዴን እንደሚጠቀሙም አመልክቷል።

በመሆኑም የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ጡረተኞችን እንዲሁም አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ በአጠቃላይ ሁሉን አካታች እና ተደራሽ ያደረገ ብሄራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተቀርፆ  መፅደቁ ተገቢና ምናልባትም የዘገየ ሊባል የሚችል ውሳኔ ነው።

በሃገራችን የሚገኙ ባንኮችን አመታዊ ሪፖርት ስንሰማ ከሌላው ዓለም በተለየ ከፍተኛ አትራፊዎች ሆነው እናገኛቸዋለን። አትራፊ የመሆናቸውን ያህል ግን የአገልግሎት ተደራሽነታቸው እጅጉን ኋላቀር እንደሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ። ባንኮቹ ያላቸው አቅም ምን ያህል እንደሆነ ሲመዘንም፣ አጠቃላይ የካፒታል አቅማቸው ከ50 ቢሊዮን ብር አይበልጥም። ይህም በኬንያ ወይም በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ አንድ ባንክ ያነሰ አቅም እንዳላቸው አመላካች ነው።  

እነዚህ ባንኮቻችን ብድር የመስጠት አቅማቸው፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው፣ ቁጠባ የማሰባሰብ ብቃታቸውና ሌሎች በዘርፉ የሚጠቀሱ አገልግሎቶች ሲነሱ፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች አኳያ የሚገኙበት አቋም እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። የፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴን ያሳድጋል፣ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ያመጣል ተብሎ በብሐራዊ ባንክ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ካካተታቸው ነጥቦች መረዳት እንደሚቻለው፣ መደበኛው የፋይናንስ ዘርፍ ያልተደረሰበትና ያልተነካ መሆኑን ነው።

የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2011 ባካሄደው የኢንተርፕራይዞች የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ካሉ የንግድ ድርጅቶች መካከል 94.7 በመቶው በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ወይም የቁጠባ ሒሳብ የነበራቸው ናቸው። ነገር ግን 33 በመቶ ድርጅቶች የባንክ ብድር እንደሚፈልጉት ሊያገኙ ባለመቻላቸው፣ በሥራቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት ፍጥሯል። በ16 በመቶው ብቻ ብድር ማግኘታቸውን የዓለም ባንክ ጥናት ያመለክታል። የፋይናንስ አገልግሎት ለማግኘት ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ አይገባም የሚለውና እንደ መለኪያ የተቀመጠው መመዘኛ፣ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይም ብዙ እንደሚቀረው ተመልክቷል። ስለሆነም አዲሱ ስትራቴጂ የችግሮቹ ሁሉ መሰረታዊ መፍትሄ ነውና የዘገየ ቢሆንም ተገቢና ወሳኝ እርምጃ ነው።

ብሔራዊ ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ ከብሔራዊ ባንክ ባሻገር ሌሎች የግልና የመንግሥት ተቋማት ተሳታፊ የሚሆኑባቸው አሠራሮች ዕቅዶች የተነደፉ ሲሆን፣ ለስትራቴጂው ዋና ኃላፊነት እንዳለባቸው ከተጠቀሱት ውስጥ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር (በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራውን ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤት ያስተባብራል) የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎችም ይሳተፋሉ፡፡ ለተፈጻሚነቱም ከብሔራዊ ምክር ቤቱ በተጓዳኝ፣ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ዓብይ ኮሚቴ፣ የፋይናንስ አካታችነት ጽሕፈት ቤትና መሰል ተቋማት የተደራጁ ስለመሆኑ ይፋ በተደረገው ስትራቴጂ ተመልክቷል ።

ባጠቃላይ፣ አካታች የሚሆነው የፋይናንስ ሥርዓት ቁጠባን  የሚያበረታታ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር እና የስራ ዕድልን እንደሚያበረታታ፤ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ ያዳርሳል ተብሎ ታምኖበታልና ያሽቆለቆለውን የወጪ ንግድ እንዲያገግምና ብሎም ሁሉአቀፍ በሆነ መልክ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ያግዛል፤ በመሆኑም ለዘርፉ አስፈላጊው ትኩረት ሁሉ ሊሰጠው ይግድ ይሆናል ማለት ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy