Artcles

የፍትሃዊነታችን ማረጋገጫ ግድብ                                                                         

By Admin

October 26, 2017

የፍትሃዊነታችን ማረጋገጫ ግድብ                                                                         

                                     ደስታ ኃይሉ

የህዳሴው ግድብ አገራችን የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አክብራ የምትሰራ መሆኗን የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት ነው። ግድቡ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የየትኛውንም አገር ህዝብ ጥቅም ሳይጎዱ ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመርኩዘው የሚያከናውኑትና ለቀጠናው አገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር የበኩሉን ሚና መወጣት የሚችል ፕሮጀክት ነው።

ግድቡ ለሀገራዊ ህልውናችን ቀጣይነት፣ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኑሮ መሻሻልና ከድህነታቸው መውጫነት ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው። በተፈጥሮ ሃብታችን እንድንኮራም ያደረገን ነው። ይህን የተፈጥሮ ሃብታችንን ማልማት ድህነትን መታገል መሆኑ መንጋት የለበትም።

እንደሚታውቀው ሀገራችንን ጨምሮ ሁሉም የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በድህነት የሚማቅቁና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁና ናቸው። በዚህም ሳቢያ በአመዛኙ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡

ቀደም ሲል ያገኙት የነበረው የዝናብ መጠን ከመቀነሱና በአየር መዛባት ሳቢያ ዜጎቻቸው በረሃብና በእርዛት ለመገረፍ ከመገደዳቸውም በላይ ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡ ግድቡ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉትና ለሀገራችንም ሆነ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነት ጉልህ ድርሻ የሚያበረክት ነው፡፡

ከዚህ አኳያም ሀገራዊ ፋይዳውን ስንመለከት ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የፀረ – ድህነት ትግል ከግብ በማድረስ ለህዳሴው ጉዞ ስኬት የሚያበረክተው ሚና የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌትሪክ ሽፋን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፤ ለዘመናት መብራት እንደ ገነት ለራቀው የገጠሩ ህዝባችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ይህም ለከፍተኛው የደንና የመሬት መራቆት ችግር እንዲሁም ሊከሰት የሚችለውን የአየር መዛባትና የሚያስከትለውን የድርቅ አደጋ የሚያስቀር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለሚደርሰው የጤና ችግር እልባት ይሰጣል፤ መሳ ለመሳም ለህክምና የሚወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ይህም ፋይዳውን ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል፡፡

ግድቡ ከዚህም የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኤሌትሪክ ሃይልን ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ ይቻላል። ይህም በድህነት ለሚሰቃየው ህዝባችን ህይወትና ኑሮ መሻሻል የሚረዳ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡ እናም ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ለዜጎች ኑሮ መለወጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በድህነትና በኋላቀርነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ስለሆነ የህልውናችን መሰረት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ቢኖር፤ ሀገራችን ምንም እንኳን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትከተልና ውጤታማ መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ወደ ኢንዱስትሪው መር ኢኮኖሚ መሸጋገሯ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የኤሌትሪክ ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡ እናም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተስተዋለ ከሚታየው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ ለቀጣይነቱ የህዳሴው ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚሰጠው ምላሽ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር እንጂ፡፡

በመሆኑም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ እነ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለአካባቢው ሠላምና መረጋጋት የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል፡፡ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡

የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ7 ነጥብ 10 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ተጨማሪ ውሃን ማስገኘት እንደሚችል ጥናቶች አረጋግጠዋል። ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ የሚመለከቱት አንዳንድ የውጭ ፖለቲከኞች የ“ይጎዳናል” ያረጀ አስተሳሰብን በማራመድ ጉዳዩን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጉት ነው፡፡

ይህ አስተሳሰብም እስካሁን ድረስ የጠፋ አይመስልም። በተለይም ግብፆች አስተሳሰቡን በተለያዩ መንገዶች ሲገልፁና እንደ ናይል ተፋሰስ ዓይነት የትብብር ማዕቀፍ ደጋግመው በጥያቄነት ሲያቀርቡት እየተስተዋሉ ነው።

ዳሩ ግን ሀገራችን ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አኳያ ሌሎችን የመጉዳት አስተሳሰብን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አታራምድም። ይልቁንም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምታምንና ይህንንም በተግባር እያረጋገጠች የምትገኝ መሆኗን በተለያዩ መድረኮች ማስመስከር ችላለች፡፡

ከዚህም መካከል የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የኢንቴቤው ስምምነት በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይህን ስምምነት ከዳር ለማድረስ ከአስራ ሶስት ዓመታት በላይ መፍጀቱ ምን ያህል ጥረት እንደጠየቀ ለመረዳት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በአባይ ተፋሰስ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የነበረው አስተሳሰብን መቀየሩ ብቻ የሚጠይቀውን ጥረት መገመት ስለማይከብድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች እየገነቡት ያለው ያለው የህዳሴው ግድብ አገራችን ኤሌክትሪክ በመሸጥ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ እንዲሆን ነው የሚፈልገው። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከግድቡ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ግብፅን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትም ተጠቃሚ መሆናቸው አይቀርም።

አገራችን ከዚህ የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚነትና በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ፍላጎቷ በመነሳትም ለዘመናት ተገድቦ የቆየውን ሀገሪቱ በተፈጥሯዊ ውኃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ ልትሰጥ አትችልም።

በመሆኑም የራሷን ፕሮጀክት በራሷ አቅም በመገንባት ላይ ያለች እንዲሁም ከድህነት ለመውጣት ስትል የምትገነባቸውን ማናቸውንም የልማት ግድቦችን ለአፍታም ቢሆን የማታቆም መሆኗን መገንዘብ ይገባል። ብሔራዊ ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ የማትሰጠውን ያህል የፍትሃዊ አመለካከቷ መገለጫ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ይገባል።