Artcles

ያልተቋረጡት ድሎች

By Admin

October 03, 2017

ያልተቋረጡት ድሎች

ዳዊት ምትኩ

አገራችን ባለፉት ዓመታት እያስመዘገበች ያለችው ፈጣንና ተከታታይ እድገት ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው። መንግሥትና ህዝብ በተለይም ባለፉት 10 ዓመታት ያስመዘገቡት የልማት ድሎች ሳይቋረጡ ግለታቸውን ጠብቀው ቀጥለዋል። እነዚህ ድሎች የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በየደረጃው እያረጋገጡ ነው። ለእነዚህ ድሎች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሰሞኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የሀገራችን ኢኮኖሚ እድገቱ መቀጠሉም ማስታወቁ የዚህ እውነታ አረጋጋጭ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ሀገራችን ላለፉት አስር ዓመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች። ይህም ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ያላት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል። “የአፍሪካ መነሳሳት” ተጠቃሽ ምሳሌ እንድትሆንም ያደረጋት መሆኑም እንዲሁ። ይህ ደግሞ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት መሆኑ አይካድም። እንደሚታወቀው የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ ያለፉት አስር ዓመታት አፈጻጸም ሲቃኝ አበረታች እንደነበር በተለያየ አጋጣሚ ተገልጿል፡፡ ያለፉት ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ዕድገት እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ አበረታች እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

በግብርናው ዘርፍ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች የታዩትን መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት አርሶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ ተሰርቷል። ምርትንና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ አርሶ አደሩን ለማገዝ ጥረት ተደርጓል።

እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ ግብዓቶች በማቅረብ ረገድም ቀላል የማይባል ሥራ ተከናውኗል። ከዚህ አንጻር የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ያስቻለ እንቅስቃሴ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።

ምርጥ ዘርን የማራባትና ለአርሶ አደሩ የማከፋፈል ተግባር አንዱ እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በማዕከል ደረጃ ካለው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት በተጨማሪ ክልሎች እንደየአስፈላጊነቱ የምርጥ ዘር ማዕከላትን በማቋቋም አርሶ አደሩን በቅርብ እያገዙ ይገኛሉ።

ሁሉም ክልሎች የየራሳቸውን የምርምር ማዕከላት በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ መልክ በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡  

ገዥው ፓርቲና መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ያካሄዱት ግምገማዎች ውጤት እንደሚያሳየው የአገሪቱ የልማት ተግባራት በአበረታች ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ነው። በገጠርና በከተማ የሚኖረውን ኅብረተሰብ በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በተያዘላቸው እቅድ መሠረት እየተከናወኑ ናቸው፡፡ ይህ የግብርና ምርትን የማሳደግ ሥራ በተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ለመምጣቱ ምስክር አያሻውም፡፡

እንደሚታወቀው ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማነቃቃት መንግስት የተለያዩ ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ፈቅዷል፡፡ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመት የግብር የእፎይታ ጊዜን ሰጥቷል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማደግ ሌላው ገጽታ የመሠረተ ልማት ግንባታ ነው፡፡

የቴሌኮም፣ የመብራት፣ የመጠጥ ውኃ እና የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ለአንድ አገር ምጣኔ ሀብት እድገት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። በአገሪቱ ከሀያ ዓመታት በፊት የነበረው የመሠረተ ልማት ግንባታ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡

እንደ መንገድ፡ ቴሌኮምና መብራት የመሳሰሉት ዋና ዋና የመሠረተ ልማት አውታሮች በከተሞች ብቻ የተወሰኑ ነበሩ፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት መሠረተ ልማትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩልም በቀደሙት ሥርዓታት ለትምህርት ተቋማት መስፋፋትና ለፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት  የተሰጠ ትኩረት አልነበረም፡፡ ከታች እስከ ላይ ድረስ የነበሩት የትምህርት ተቋማት ውስን ከመሆናቸውም በላይ የተቋቋሙት በከተሞች ብቻ ነበር፤ በአገሪቱ አንድም የግል ዩኒቨርስቲ ሆነ ኮሌጅ አልነበረም፡፡

በአሁኑ ሰዓት ግን ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ ትምህርት በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ እድሜው ለትምህርት  የደረሰ ህጻን ሁሉ የማዕዱ ተቋዳሽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሶስት ሰዎች አንዱ ተማሪ ነው፡፡

በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህጻናት የምገባ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ምገባው  ህጻናት በምግብ አቅርቦት ማነስ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይሰናከሉ ማገዝ ችሏል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ኢፍትሃዊ ሥርጭት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ አለመቻላቸውንና  የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ አልቀረም፡፡

በአገራችን ባለፉት ዓመታት ከተሰሩት ተግባራት አንዱ በአገሪቱ ፍትሃዊ የትምህርት ሥርጭት እንዲኖር መደረጉ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

በአገራችን ለተመዘገበው ሁለንተናዊ ለውጥ ሌላው መገለጫ በጤናው ዘርፍ የተገኘው ስኬት ነው፡፡ ጤናማ ትውልድ መገንባት ዋነኛው የልማት አካል ነው፡፡ እንበለ ጤናማ አምራች ዜጋ ዘላቂ ልማት አይታሰብም፡፡ ከዚህ አኳያ አገራችን የነበረችበትና አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን ማየት ለተሟላ ግንዛቤ ይረዳል፡፡

በኢትዮጵያ የዛሬ ሀያ ዓመት በፊት የነበረው የጤና ሽፋን ከ38 በመቶ በታች ነበር፡፡ ሽፋኑ በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች ብቻ የተወሰነ ስለነበር በገጠር የሚኖሩ እናቶች ለከፋ የጤና ችግር ይጋለጡ ነበር፡፡ ህጻናትና እናቶች በአቅራቢያቸው የህክምና አገልግሎት አያገኙም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ይዳረጉ የነበሩ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ግን በተከታታይ በተሰራው ስራ እጅግ ቀንሷል፡፡

የከተማ ሥራዎችን በተመለከተ በዋነኝነት የከተማውን ነዋሪ የገቢ አቅም ለማሳደግ የተካሄደው የሥራ ዕድል ፈጠራና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ አንፃር አበረታች ርቀት የተሄደበት መሆኑ ነው። ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በአስፈጻሚ አካት ጭምር እምነት ተይዞበታል፡፡ ከከተማው ልማት ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰው ሌላው ተግባር የቤት ልማት ግንባታ ነው፡፡

በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል  የኮንደምኒየም ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ እስካሁን በአዲስ አበባ ብቻ ከአሥር ሺህዎች ቤቶች በላይ ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡ ሌሎች  ከአሥር ሺህዎች በላይ የሚሆኑ ቤቶች ደግሞ በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

በመልካም አስተዳደር በኩል ያሉትን ሁኔታዎች በመፈተሽ በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ተጀምሮ የነበረው በሁሉም ክልሎች ከነዋሪው ጋር በችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ በምልልስ ህዝቡን ያሳተፈ የማጥራትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡

ጥልቅ ተሃድሶ ተካሂዶም በሲቪል ሰርቫንቱ ውስጥ ያለውን የመንግስት አሰራርን በመፈተሽ ከህዝቡ ጋር በመሆን እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ እነዚህ ተግባሮች የሚያሳዩን አገራችን ውስጥ እየተከናወኑ ያሉት ሁለንተናዊ ድሎች ያልተቋረጡና ወደፊትም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ነው፡፡