Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጅሎች እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም

0 352

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ጅሎች እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም
አሜን ተፈሪ
ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ጽሑፌ የሐገራችን ሚዲያ ግጭቶችን ለመከላከል ትልቅ ትኩረት መስጠት የሚገባው መሆኑን ለማስረዳት፤ የታሪክ ጉዟችንን ለመቃኘት ሞክሬአለሁ፡፡ በዚህ በሁለተኛው ክፍል፤ ሚዲያዎች ግጭትን በመከላከል፤ ግጭቶች ከተከሰቱም በኋላ ቀውሱን ለማረጋጋት በመሥራት እንዲሁም በድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ ሂደት ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት ምን ዓይነት የአሰራር መርህ ሲከተሉ እንደሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ሐገራችን በአንጻራዊ ሚዛን የተሻለ የሰላም ዘመን ያየችው ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ዓመታት ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ብዝሃነትን ማክበር የተሳናት ሐገራችን ከግጭት ነጻ መሆን አቅቷት፤ ለልማት ሊውል ይችል የነበረው ሐገራዊ ሐብት እና ጉልበት በግጭት እሣት ተበልቷል፡፡ አሁን የግጭት ምንጭ ሆኖ የቆየውን ብዝሃነትን ያለማክበር ችግር ለመፍታት ሞክረናል፡፡ በ1960ዎቹ የነበረው ትውልድ፤ ከባድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ፤ የጊዜው ዓለም አቀፋዊ እና ሐገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንዳመለከተው ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ያለውን ፖለቲካዊ አቋም ይዞ ታግሏል፡፡ የህዝቡን ጥያቄ አንግቦ፤ ለ17 ዓመታት ከአምባ ገነነን መንግስት ጋር ተፋልሞ፤ ትግሉን በድል በማጠናቀቅ፤ ፖለቲካዊ የሐሳብ ልዮነቶች በጠብመንጃ ሳይሆን በክርክር መስተናገድ የሚችሉበት ፌዴራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አቁሟል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ያለው ወሳኙ ሥራ የተተኪው ትውልድ ይሆናል፡፡ የተመቻቸውን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ እንደ ዓይን ብሌን ጠብቆ፤ በዴሞክራሲያዊ የሐሳብ ትግል የጎደለውን ሞልቶ፤ የተጣመመውን አቃንቶ፤ ይህን ከዘመናት መከራ በኋላ የተገኘ ምቹ ሁኔታ ሳያበላሽ ለተሻለ እና ለላቀ ድል ለመብቃት ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡
ታዲያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ገና ለጋ በመሆኑ፤ የስርኣቱ ምሰሶ የሆኑ ተቋማትን የማጠናከሩ ከባድ ሥራ ገና ብዙ የሚያደክም ነው፡፡ በዚህ ስርዓት መሠረታዊ መርሆዎች እና እሴቶች የተገነባ ፖለቲካዊ ባህል ሊዳብር የሚችለው በተጨባጭ የህይወት ልምድ በመሆኑ አልፎ አልፎ መደነቃቀፍ አይቀርልንም፡፡
ቀደም ባለው ዘመን የግጭት ምንጭ ሆኖ የቆየውን ነገር ለይተናል፡፡ ብዝሃነትን ያለ ማክበር ችግር ወደ ግጭት እንዳይወስደን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ፈጥረናል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ማሣው ተዘጋጀቷል፡፡ ሆኖም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እርሻውን የማለስለስ፣ የፖለቲካዊ እሴቶች ዘርን የመምረጥ፣ የማረም እና መኮትኮት ሥራ ይቀረናል፡፡ ይህ ሥራ ከባድ ሥራ ነው፡፡ እናም ይህ ሥራ በተጨባጭ የህይወት ልምድ እየተሻሻለ እና እየተጠናከረ የሚሄድ በመሆኑ ትዕግስት እና የአስተዋይነት መንፈስን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ምህዳር የሚንቀሳቀሰው ሐገራችን ሚዲያ ትልቅ ኃላፊነት የተሸከመ ሚዲያ ነው፡፡ ከኃፊነቶቹ ዋነኛው የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ነቅቶ በመጠበቅ፤ እየተጠናከረ እንዲሄድ የማድረግ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ነጻ ወይም ገለልተኛ፤ ለሙያው ሥነ ምግባሮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጥ፤ የውይይት መድረክ በመሆን ግጭቶችን ቀድሞ መከላከል፤ ሲከሰቱም የማረጋጋት ሚና መጫወት እና በድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል፡፡
ሐገራችን ተስፋ ያላት ሐገር ነች፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ምህዋር ውስጥ የምትገኝ ሐገር ነች፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁሉንም የሚያረካ ባይሆንም፤ ሐገሪቱን ከድህነት ለማውጣት በሚያስችል ጎዳና ላይ መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከድህነት አዘቅት ጎትቶ እያወጣ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡ አንዳች የተስፋ ጮራ ሳታይ ዘመናትን የተጓዘችው ሐገር ከአድማስ ባሻገር የፈነጠቀ የብርሃን ጭላንጭል መመልከት ከምትችልበት ሥፍራ እንድትደርስ ያደረገ የልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ የተስፋ ብርሃን ይበልጥ እየደመቀ እና ሁሉንም አካባቢ የሚሸፍን ብርሃን እንዲሆን፤ ጉዟችን በግጭት ሳይደናቀፍ በጀመርነው ጎዳና መራመድ መቀጠል ይኖርብናል፡፡
የኢትዮጵያውያን አንጻራዊ ሰላም ማግኘት ባሉበት የታሪክ ምዕራፍ ተዐምር እየሰሩ የመጡ ህዝቦች ናቸው፡፡ እነ አክሱም፣ ላሊበላ የጀጎል ግንብ ወዘተ ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነት እስር ቤት እንድትወጣ የተደላደለ የሰላም ዘመናት ያስፈልጋታል፡፡ ስለዚህ በታሪካችን ካየነው የግጭት አዙሪት ውስጥ በድንገተኛ ክስተቶች ተጠልፈን እንዳንገባ በንቃት መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ወደ ግጭት ከመግባት በእጅጉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የሌሎች ሐገራትን ወደ ግጭት ወይም ወደ ጦርነት ሊያስገባ የሚችል በቂ ምክንያቶች ወይም ችግሮችን ጭምር በትዕግስት የማለፍ አስተዋይነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅማችንን ማጠናከር ይገባናል፡፡ የምንገኘው በቀላሉ ቱግ የሚሉ ብዙ ችግሮች ባሉበት የአፍሪካ ቀንድ በመሆኑ፤ በነዳጅ ጉድጓድ አካባቢ እሣት ይዘን መገኘት የለብንም፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ዘመናት በተከሰቱ ትላልቅ ግጭቶች ሳቢያ ሰላም አጥተን ኖረናል፡፡ የሰላም እጦቱ ከድህነት እስር ቤት ጥሎናል፡፡ ድህነትም የግጭት ምንጭ ይሆናል፡፡ ድህነት የሰላም መውቅሮችን ያፈራርሳል፡፡ ህዝብን ሆደ ባሻ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ከግጭት ለመራቅ ድህነትን ማስወገድ፣ ድህንትን ለማስወገድ ደግሞ ሰላም እንደሚያስፈልገን ተረድተን ወደ ግጭት ከሚወስድ ጎዳና ላለመግባት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ሂደት የሚዲያ የማይተካ ሚና አለው፡፡
ሚዲያ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም በማስፈን ሂደት ባለው ሚና ዙሪያ በርካታ ትንተናዎች ተሰርተዋል፡፡ ሆኖም ሚዲያ ግጭትን በመከላከል ረገድ ያለው ሚና ብዙም ትኩረት አላገኘም፡፡ በተመሳሳይ ሚዲያ ግጭትን በመቀስቀስ ረገድ የሚኖረው አስተዋጽዖ በቅጡ አልተነተነም፡፡ ከዚህ ሊገኝ የሚችለው ትምህርትም በወጉ አልቀመረም፡፡ ሚዲያ ግጭትን በመከላከል ረገድ፣ ግጭትን በማገረም (በማስተዳደር) እና በድህረ -ግጭት ወቅት ሰላምን መልሶ በመገንባት ሂደት (Post-Conflict reconstruction) ያለው ሚና በደንብ መታየት አለበት፡፡ ይህ ትምህርት ለኛ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች በማነሳት ማሰብ እና መወያየት ይኖርብናል፡፡
ሀ). ሚዲያ ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ችግርን በማረገብ ረገድ ያለው ሚና ምንድነው?
ለ). የግጭት ክስተቶችን በመዘገብ ወይም ባለመዘገብ ረገድ በተለያዩ ሚዲያዎች ዘንድ የሚታየው ልዩነት ምን ይመስላል?
ሐ). ሚዲያ ራሱ የግጭት ምንጭ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል?
በዚህ ጽሑፍ ጥያቄዎቹን ከማንሳት በቀር የተተነተነ ሐሳብ ለማቅረብ አልችልም፡፡ ሆኖም፤ በጥቅሉ ሚዲያ በግጭት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና በመግለጽ፤ የሐገራችን ሚዲያ በግጭት ውስጥ ሊጫወቱ የሚገባቸውን ሚና ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ሚዲያ በግጭት ውስጥ ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ቁልፍ ሚናዎችን ይጫወታል፡፡ በአንድ በኩል፤ በግጭቱ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የተፈጠረውን ግጭት የማባባስ ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ገለልተኛ አቋም ይዞ ራሱን ከግጭቱ ተሳታፊነት በማራቅ ግጭቶች ሰላማዊ እልባት የሚያገኙበትን ወይም ሁከቱ መወገድ ገንቢ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሚዲያ ከሁለቱ ተቃራኒ ሚናዎች በአንዱ ተሳታፊ ሆኖ የሚገኘው፤ ከግጭቱ በፊት ወይም በኋላ ባለው ሂደት የሚኖረውን ሚና የሚወስኑ በርካታ ውስብስብ ጉዳዮች አሉ፡፡
አንድ ግጭት ሲከሰት፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት እና ፊና ለይተው የቆሙት ወገኖች ተቃራኒ የሆኑ አቋሞች ይይዛሉ፡፡ ሁሉም ወገኖች የሚዲያው ሽፋን የእነሱን ጥቅም የሚያረጋግጥ እንዲሆን ይሻሉ፡፡ አንዱ በግጭቱ የደረሰው ጉዳት ተጋንኖ እንዲቀርብ፤ ሌላው ተኳስሶ እንዲዘገብ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለዘገባ የሚሰማራው ሚዲያ ገለልተኛ ካለሆነ እና በሥነ ምግባር የሚመራ ካልሆነ ግጭቱን የማባባስ ሚና ይኖረዋል፡፡
1. ሚዲያው በግጭቱ ተሳታፊ ከሆኑ ወገኖች ጋር ያለው ግኙነት፣ ትስስር ወይም ዝምድና፤
2. በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት ወይም ስልጣን ከያዙ ቡድኖች ቁጥጥር ነጻ መሆን አለመሆኑም በሥራው የሚኖረውን ነጻነት ይውስነዋል፡፡
በመሆኑም፤ ግጭትን በማስወገድ፣ ሰላምን ወይም መረጋጋትን በመመለስ እና በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና የሚኖራቸው ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ‹‹ደካማ ወገኖች›› ግጭቱ ስፋት ያለው ሆኖ እና ተጋንኖ እንዲቀርብ ወይም የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ይፈልጋሉ፡፡ የእነሱ ጥያቄ ሰፊ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በተቃራኒው፤ መንግስትን ጨምሮ ‹‹ጠንካራ ኃይል›› ያላቸው ወገኖች፤ ግጭቱ ስፋት የሌለው ሆኖ እንዲቀርብ ወይም ጨርሶ የሚዲያ ሽፋን እንዳያገኝ ይጣጣራሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሚዲያዎች የሚኖራቸው ሚና ግጭትን የማስወገድ ወይም ሰላምን የመመለስ እንዲሆን፤
ሀ. የፕሬስ ነጻነትን ማረጋገጥ፤
ለ.የግጭቶችን መንስዔ (ዎች) መረዳት እና መረጃዎችን ሳይሸፍጡ ማቅረብ፤
ሐ. ገለልተኛነትን መጠበቅ፤ ሥነ ምግባራዊ፣ ሚዛናዊ መሆን እና የዘገባ ስታንዳርዶችን ተከትሎ መሥራት፤
መ. ለድምጽ አልባዎቹ (ደካሞቹ) ድምጽ መሆን፤
ሠ. ሚዛናዊ ለሆኑ፣ የተሰበረውን ድልድይ የሚገነባ፤ የቀደመውን መልካም ግንኙነት የሚዘክሩ ድምጾች ጉልህ ሥፍራ እንዲይዙ ማድረግ ወይም የጥላቻ ንግግሮች መድረክ አለመሆን፤ ወዘተ ያስፈልጋል፡፡
ሚዲያዎች ይህን ማድረግ ሲሳናቸው፤ ሚዛናዊ ድምፆች እየተገፉ፤ የመረጋጋት ሚና የሚኖራቸው ሚዛናዊ ድምጾች እንደ ከሃዲ ተቆጥረው የሚገፉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የፈጠራ ወንጀሎች ወይም ጥቃቶች እየቀረቡ ቀውሱ የሚባባስበት ዕድል እየሰፋ ይሄዳል፡፡ በሩዋንዳ እና በባልካን ሐገሮች እንደተመለከትነው፤ ሚዲያዎች ግጭትን በማባባስ ብቻ ሳይሆን ግጭትን በቀስቀስ ረገድ ተሳታፊ ለሆኑ ይችላሉ፡፡ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴውን የሚያደራጁ እና የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎችን አይተናል፡፡ በይጎዝላቪያም አጥፊ የብሔርተኝነት ስሜት ማራገቢያ ሆነው ሲያገልግሉ ተመልክተናል፡፡
ከእነዚህ ክስተቶች ልንወስድ የምንችለው፤ መንግስት ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው፡፡ ሙያዊ አሰራር የሚጠናከርበትን ሁኔታ መፍጠር እና ህዝቡ መጻዒ ዕድሉ ብሩህ ሆኖ እንደታየው የሚያደርግ የልማት ሥራን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy