Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጅሎች እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም /ክፍል አንድ/

0 537

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

ጅሎች እንጂ ታሪክ ራሱን አይደግምም
አሜን ተፈሪ
ክፍል አንድ
የግጭት መብቀያ፣ መራቢያ እና መፈልፈያ የውይይት አለመኖር ነው፡፡ ውይይት ባለበት ግጭት አይከሰትም፡፡ ይህ ሐሳብ ምናልባት ችግር ያለበት መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በደንብ ስናጤነው፤ ‹‹ውይይት ባለበት ግጭት አይከሰትም›› መባሉ በጣም ትክክል ነው፡፡ የማይናወጽ እውነት ነው፡፡ ግጭት የሚበቅለው፣ የሚራባው እና የሚፈለፈለው ውይይት በሌለበት አካባቢ ነው፡፡ ሰው የሚያስብ ፍጡር ነው፡፡ ህይወቱን እና ንብረቱን የሚያጠፋ ችግር ውስጥ በቀላሉ መግባት አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ችግር ቢኖርም ነገሩን በውይይት መፍታት የሚችልበት ዕድል ካለ ውይይትን ይመርጣል፡፡ የተፈጠረበትን ችግር ተናገሮ፤ ሰሚ አግኝቶ ችግሩ ከተፈታለት እና ጥቅሙ ከተጠበቀለት ለምን ወደ ግጭት ይገባል፡፡ ለሰው ልጅ በበሰላም እና በህይወት ከመኖር የሚልቅ ሌላ ምን ጥቅም አለው? በህይወት ለመኖር የሚያስችሉት ሐብት እና ንብረቶቹም እንዲጠበቁለት ይፈልጋል፡፡ በእነዚህ ጥቅሞቹ ላይ አደጋ ሲያንዣብብበት መናገር ይፈልጋል፡፡ ጉዳዩ በንግግር የሚያልቅበት ዕድል ምቹ ከሆነ፤ ተናግሮም መፍትሔ ማግኘት ከቻለ ግጭት የሚነሳበት ዕድል ዝግ ይሆናል፡፡
ታዲያ አንዳንዴ ውይይት የመሰለ ነገር ኖሮ ግጭት ሲነሳ ወይም ሲባባስ እንመለከት ይሆናል፡፡ እንዲያውም አልፎ አልፎ ውይይቱ ችግር የሚያባብስ መስሎ ሊታየን ይችላል፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ውይይት የመሰለ ነገር ኖሮ ግጭት የሚከሰተው፤ ውይይቱ ነጻነት የሌለበት ወይም ውይይቱ ኃይል ባላቸው ሰዎች ተጽዕኖ ሥር ሲወድቅ፤ ውይይት የሚባል ነገር ኖሮ ግጭት ሊባባስ ይችላል፡፡ ትክክለኛ ውይይት የሚኖረው፤ ትክክለኛ ነጻነት ሲኖር ነው፡፡ ውይይት ግጭትን ሊያስወግዱ የማይችሉት ወይም ሊያባብሱ የሚችሉት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ወገኖች በነጻነት መወያየት የሚችሉበት መድረክ ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች በነጻነት መወያየት የሚችሉበት መድረክ ሊኖር የሚችለውም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ግጭት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሌለበት ወይም ባልዳበረበት ማህበረሰብ በተደጋጋሚ የመከሰት ችግር ነው፡፡ የግጭት ማስወገጃ ብልሃት፤ ውይይት ነው፡፡ የይስሙላ ያለሆነ ነጻ ውይይት ማድረግ የሚቻለውም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ነው፡፡
በመሆኑም ግጭቶችን ሲከሰቱ ወይም ለግጭት የመዳረግ አዝማሚያ ሲታይ፤ ቀድመን መፈተሽ የሚገባን፤ ለውይይት ምቹ የሚሆን ነገር መኖር አለመኖሩን ነው፡፡ ነጻ ውይይት ለማድረግ ያስችለናል ብለን ያጸናነው ስርዓት ካለም በስርዓቱ ውስጥ የተከሰቱ ብልሽቶች መኖር አለመኖራቸውን መመርመር ነው፡፡
እንደሚታወቀው፤ ህገ መንግስታችን ሐሳብን በግለጽ ነጻነት የመግለጽ መብትን አጎናጽፎናል፡፡ ሐሳብን በግለጽ ነጻነት የመግለጽ መብትም መረጃ የመፈለግ፣ የማሰባሰብ እና የማሰራጨት ጉዳዮች እንደሚያጠቃልል በህገ መንግስታችን ሰፍሯል፡፡ ታዲያ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከተለያዩ ወገኖች እንቅፋቶች ወይም ጫናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡ እንቅፋቶቹም ውስጣዊ እና ውጫዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚረጋገጠው በሳንሱር አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ የመብቱ ተጠቃሚ በራሱ ላይ የሚጭነው ማዕቀብም ይኖራል፡፡ ስለዚህ ከሌላ ወገን ከሚመጣ እና ከራስ ከሚመነጭ ሳንሱር ነጻ መሆንን ይጠይቃል፡፡
ሆኖም የነጻነት ጉዳይ ከሌላ ወገን እና ከራስ ከሚመነጭ ሳንሱር ነጻ በመሆን ብቻ አያበቃም፡፡ መረጃን በመፈለግ፣ በማሰባሰብ እና በማሰራጨት ረገድ እንቅፋት ካለ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ እክል ይኖራል፡፡ ስለዚህ መረጃን በመፈለግ፣ በማሰባሰብ እና በማሰራጨት ረገድ የሚኖር ጫና ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት ላይ የሚደርስ ጫና ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ምህዳር ውስጥ ነጻ ውይይት ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህ ዓይነት ምህዳር ውስጥ የሚደረግ ውይይት ግጭትን ሊያባብስ የሚችል ውይይት የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም እውነተኛ ውይይት ሊባል አይችልም፡፡ እንዲህ ያለ ውይይትም ግጭትን ሊከላከልም አይችልም፡፡ ስለሆነም፤ ‹‹ግጭት እንዳይኖር ማድረጊያው ብልሃት ውይይት ነው›› ሲባል፤ ነጻ ውይይት ማለት እንጂ፤ ጉልበት ያላቸው ወገኖች የሌሎች (የደካሞች) ድምጽ በአግባበቡ እንዳይሰማ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ የሚደረግ ውይይት አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ ውይይቱ የሚካሄድበት አጠቃላይ አውድም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ዓውድ ስንልም የፖለቲካ ባህል እና ታሪክን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡
ቀደም ሲል ነጻነት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ብቻ የሚኖር ሐብት መሆኑን ጠቅሰናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተቋማዊ ባህርይ ያለው የውይይት መድረክ ፕሬስ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ተቋም ያለው ጤንነት የውይይቱን ጤንነት ይወስነዋል፡፡ ግጭትን የማስቀረት ሚናውም በጤንነቱ ይወሰናል፡፡ ስለሆነም፤ በውይይት ግጭትን የማስቀረት ተግባር፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽን ጉዳይ የሚመለከት ሲሆን፤ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ጉዳይም በአብዛኛው ከሚዲያ ነጻነት እና የአሰራር ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ውይይት የማድረግ ጉዳይ ከፕሬስ ነጻነት ጋር ይተሳሰራል፡፡ እናም ግጭትን በመከላከል፣ በማስተዳደር እና በድህረ-ግጭት (ሰላምን መልሶ በመገንባት) ሁኔታዎች ውስጥ የሚዲያ ሚና ትልቅ ነው፡፡ ሚዲያ የውይይት መኪና በመሆኑ፤ ግጭትን በመከላከል ሂደት የዚህ መኪና አሰራር እና የባለሙያዎቹ የሥነ ምግባር ሁኔታ ወሳኝ ነው፡፡
ሆኖም የሚዲያውን ሁኔታ ከማየታችን በፊት፤ የሐገራችን ሚዲያ በምን አውድ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ መመልከት ይኖርብናል፡፡ የሐገራችን የሐሳብ ወይም የውይይት መኪና በምን ዓውድ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ለማወቅ የሐገሪቱን ታሪክ ዋነኛ ባህርይ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሐገሪቱን ታሪክ ዋነኛ ባህርይም ግጭት ነው፡፡ በአጠቃላይ የሐገራችን የውይይት መኪና ወይም ሚዲያ ለረጅም ዓመታት በግጭት ውስጥ አልፎ በመጣ ህብረተሰብ ውስጥ የሚሰራ መኪና በመሆኑ፤ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ጠንካራ ባህል በሌለው ህዝብ ውስጥ የሚገኝ መኪና ነው ነው (1)—(ባህላዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ዘንግቼ አይደለም)፡፡ እንዲሁም የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል በሌለበት ምህዳር የሚንቀሳቀስ መኪና ነው (2)፡፡ ለዴሞክራሲ ባህል ተቃራኒ የሆኑ አመለካከቶች በሰፊው በሚታዩበት ማህበራዊ ዐውድ የሚሰራ መኪና ነው (3)፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡
ከእኛ ሐገር ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የግጭት ምንጭ የሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምላሽ ሳያገኙ ረጅም ዘመናትን ኖረናል፡፡ በዚህ የተነሳ በማያባራ የግጭት ናዳ ስንታወክ ዘመናትን ገፍተናል፡፡ ከግጭት አዙሪት የሚያወጣ መላ ጠፍቶብን ስንታመስ ምዕተ ዓመታትን ዘልቀናል፡፡ ረጅሙ የሐገራችን ታሪክ ዋነኛ ገጽታ ግጭት ሆኖ የሚታየው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ አስጎንብሶ ከሚገዛን እና ዘወትር ከሚደቀድቀን የድህነት እና የኋላ ቀርነት ጭራቅ እግር ሥር መውጣት ተስኖን ቆይተናል፡፡ ለረጅም ዘመናት በግጭት ውስጥ ያለፍን በመሆናችን የተነሳ፤ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ቀንበር ተጭኖን ዘመናት ከመግፋታችን በተጨማሪ፤ ተቋማዊ የግጭት መካላከያ እና መፍቻ ብልሃት ውሉ እየጠፋብን ብዙ ጊዜ ተደናብረናል፡፡
ታዲያ ከዘመናዊነት ግፊት ጋር ነባሩ የግጭት መፍቻ ስርኣት እየተዳከመ ከመሄዱ በተጨማሪ፤ ቢኖርም አገልግሎቱ ከመንደር ያለፈ አይደለም፡፡ ስለዚህ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ስርዓቶቹ እንደ ሐገር የሚመጣን ቀውስ ለመከላከል የሚችሉ አይደሉም፡፡ ያም ሆኖ ጨርሶ ከመጥፋት የጠበቀን ይኸው ባህላዊ ስርዓት በመሆኑ ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ይሁንና በዘመናዊ የኑሮ ይትብሃል ለመሄድ የምንሞክር በመሆኑ፤ ባህላዊው የግጭት መፍቻ ስርዓት አጋዥ ከመሆን ያለፈ ሚና ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም ዘመናዊው የግጭት መፍቻ ስርኣት (ዴሞክራሲ) በፍጥነት እየተጠናከረ ካልሄደ፤ ከእንግዲህ የግጭት ተጋላጭነታችን ይበልጥ እየሰፋ ሊሄድ ይችላል፡፡
በተደጋጋሚ በሚያጋጥመን ግጭት የተነሳም ኢኮኖሚያዊ አቅማችን ደካማ እየሆነ መጥቶ በልቶ ለማደር የምንቸገር ህዝቦች ሆነናል፡፡ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፤ በልቶ ለማደር የሚያስችል ሥራ ለመስራት ዕደል ለማግኘት ጭምር ነው፡፡ ድህነቱ የከፋ በሆነ መጠንም፤ ለግጭት የምንዳረግበት ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ የግጭት ጉዳይ የሚያሳስበን በዚህ የተነሳ ነው፡፡
የዓለም ታሪክ የሚያስተምረን አንድ ቁም ነገርም አለ፡፡ በዓለም የተካሄዱ ትላልቅ ወይም ትናንሽ ግጭቶች ሁሉ ብዙ ደም ካፋሰሱ በኋላ የመጨረሻ መሳረጊያቸው እርቅ መሆኑን የዓለም ታሪክ ያስገነዝበናል፡፡ የግጭቶች ሁሉ ማሳረጊያ ውይይት እና ድርድር ከሆነ፤ ለውይይት እና ለድርድር በሩን ሰፋ አድርገን ግጭትን ማራቅ ይኖርብናል፡፡ ‹‹ዓይን ያጠፋ፤ ዓይኑ ይጥፋ›› ብለን ከማሰብ መውጣት ይኖርብናል፡፡ ማህተመ ጋንዲ ‹‹ዓይን ያጠፋ፤ ዓይኑ ይጥፋ የሚል መርህ ዓለም የዓይነ ስውራን መኖሪያ ያደርጋታል›› ይላል፡፡ ዓይንን ያጠፋ -ዓይኑ ይጥፋ በሚል አስተሳሰብ ሄደን፤ የታረፍነው ነገር በድህነት የዓይኑ የጠፋ ህብረሰተብ መሆን ብቻ ነው፡፡ ድህነት ደግሞ የግጭት መራቢያ ወይም መፈልፈያ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ አስተውሉ፡፡ ቀደም ያለውን የታሪክ ምዕራፍ ትተን ከዘመነ መሣፍንት ጀምረን እንየው፡፡ በዘመነ መሣፍንት በየጎጡ ተከፋፍለን እርስ በእርስ ስንጨራረስ ኖረናል፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 1983 ዓ.ም ባለው የታሪክ ምዕራፍ ባሳለፍናቸው 300 ገደማ የሚሆኑ ዓመታት ውስጥ የኖረ፤ የ300 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆነ አንድ ሰው የህይወት ታሪኩን ቢያጫውተን የመከራውን ከባድነት እንረዳው ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም በፊት ከወጣትነት ዕድሜ የደረሱ ሰዎች ሁሉ የህይወት ታሪካቸውን ብትጠይቋቸው የምትሰሙት አሳዛኝ ታሪክ ብቻ ነው፡፡ ቀደም ባለው ዘመን፤ በዘመቻ ተወልዶ፣ በአገልግል ታዝሎ፣ በየጊዜው በሚነሳ የእርስ በእርስ ግጭት እየተሰደደ፤ በየቤተ ዘመዱ ተጠግቶ፤ መረጋጋት ባጣ ቤተሰብ ያደገ ልጅ ብዙ ነው፡፡ የታላላቅ ሰዎቻችንን የህይወት ታሪክ ተመልከቱ፡፡ የስደት፣ የመከራ፣ የሰላም እና የነጻነት እጦት ያጠወለገው የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ሐገሪቱ በየጊዜው በሚነሳ ማዕበል ክፉኛ የምትናጥ ጀልባን ትመስላለች፡፡
የዘመነ መሣፍንቱ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት ወሬ እና ትንታኔ የሚያሻው አይደለም፡፡ ዘመኑ ራሱን ለመግለጽ የሚሳነው አይደለም፡፡ የሑከት ዘመን ነው፡፡ ይኽን የታሪክ ምዕራፍ ስንዘጋ የምናገኘው አጤ ቴዎድሮስን ነው፡፡ እርሳቸው እንዲሁ እንደዋተቱ የእንግሊዝ ጦር መጥቶ መድቅደላ አምባ ሲወጋቸው ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ተካታዩ አጤ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ለጦርነት ጉራዕ-ጉንደት-አንቺም- መተማ ወዘተ እየዋተቱ፤ አንድ ቀን እንኳን ሳያርፉ ከዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ተከታዬ አጤ ምኒልክ ናቸው፡፡ እርሳቸውም በጦር ሜዳ አድገው፣ በጦር ሜዳ ጎልምሰው በጦር ሜዳ አርጅተው፤ በመጨረሻ መረጋጋት ያጣ መንግስት ትተው አረፉ፡፡ በዚህ ሁሉ የታሪክ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላም እና መረጋጋት አላገኙም፡፡
ምናልባት፤ ታሪኩን በፖለቲካ መነጽር የሚመለከት ሰው፤ ሊነቅሰው የሚችለው ችግር መኖሩ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ አጤ ምኒልክ ወደ ደቡብ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ የኢትዮጵያ ግዛት ሲሄዱ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ሽፍታ ያስመረረው ነጋዴ፤ ጎሮዶማን ያስቸገረው አርሶ አደር፤ የአስተዳደሩን ባህርይ ተወት አድርጎ፤ ህግ የሚያስከብር አንድ ኃይለኛ መምጣቱን እንደ ሰላም አዋጅ ይመለከተው ነበር፡፡ ከዝርፊያ እና ከውንብድና ግፍ የተገላገለው አርሦ አደር እና የሲራራ ነጋዴ የአጤ ምኒልክን መምጣት በደስታ የሚመለከትበት ሁኔታ ነበር፡፡
በአጭሩ ከአድዋ እሰከ ወልወል (ማይጨው) ባለው ዘመን፤ ሐገሪቱ ከጦርነት ትንሽ ፋታ ብታገኝም፤ የረባ ነገር ሳይሰራ ጊዜው አለፈ፡፡ በሐገሪቱ በሥልጣን ሽኩቻ ትታመስ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው የሐገሪቱ ሁኔታ ያሳሰባቸው እንደ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ያሉ ምሁራን፤ መልካም አስተዳደር ሳይሆን የማይረባ አስተዳደር እንኳን ማጽናት አለመቻላችን አሳስቧቸው ይጨነቁ ነበር፡፡ ሐገር የሚለማው በትምህርት በመሆኑ፤ ትምህርት እንዲስፋፋ እና ስርዓት እንዲጸና ብዙ ወትውተዋል፡፡ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፤ በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ሐገሪቱን የማዘመን ሥራ ቢጀመርም፤ የተደላደለ ስርዓት መትከል አለመቻሉን እያዩ በጸጸት ይብከነከኑ ነበር፡፡ ሐገሪቱ በውስጥ ችግር እና በዙሪያዋ በሚያንዛብቡ ቅኝ ገዢዎች ሴራ ተወጥራ እያቃሰተች ሳለ፤ ምኒልክ አረፉ፡፡ በእቴጌ ጣይቱ፣ በልጅ ኢያሱ፣ በንግስት ዘውዲቱ እና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ ደጋፊዎች ሴራ እና ሽኩቻ የሚታመሰው መንግስት የረባ ሥራ ለመስራት የሚችል አልነበረም፡፡ ሽኩቻው በአጤ ኃይለስላሤ አሸናፊነት ተደምድሞ ስለ ትምህርት እና አስተዳደር ማሰብ እንደ ተጀመረ የአድዋን ቂም በመበቀል ስሜት የሚገፋው የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል መጥቶ፤ የሀገር ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ የተማሩ ወጣቶችን ለቅሞ በማጥፋት፤ ሐገሪቱን ክፉኛ አመሳቅሎ፤ ህዝቡንም ጨፍጭፎ ሄደ፡፡
ባለፉት 300 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም ፋታ አላገኘም፡፡ ለጊዜው የሥርዓቱን ባህርይ ወደ ጎን አድርገን፤ ከፋም ለማም ዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ጀምሮ፤ የተወሰኑ ልጆች ተምረው ለሐገራቸው መስራት ከሚችሉበት ዕድሜ ሲደርሱ፤ ለዕድገት እርሾ የሚሆን ነገር ሳይሠሩ በግጭት ለሞት ይዳረጉ ነበር፡፡ በመጨረሻም፤ ዘውዳዊው አገዛዝ አርጅቶ እና በስብሶ ሲገረሰስ የተፈጠረው የተስፋ ጭላንጭል በተመሳሳይ ሁኔታ ድርግም አለ፡፡ የተስፋው መዝሙር ወደ ሙሾ ተቀረ፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነቱም ተባብሶ ቀጠለ፡፡ የ1960ዎቹ ኢትዮጵያ የታላቋ ሶማሊያ ቅዠት በነበረው ዚያድ ባሬ መጠነ ሰፊ ወረራ እና ለ30 ዓመታት በዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ ሞት አፋፍ ተገፋች፡፡ ይህ ሂደት መቋጫ ያገኘው በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ከስልጣን ተወግዶ፤ ፌዴራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲጸና ነው፡፡ ይህን የሚታወቅ ታሪክ የማነሳው ለአጽዖት እንጂ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማስተማር አይደለም፡፡ የመጣንበት ጎዳና ምን ያህል አስከፊ መሆኑን እና ሐገሪቱ ወደ ግጭት እንዳትገባ በብዙ መጠንቀቅ እንዳለብን ለማሳሳብ ነው፡፡ እንዲሁም የሐገራችን ሚዲያ በምን ዓይነት አውድ ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ለማመልከት ነው፡፡ ሐገሪቱ እንዲህ ፋታ በሌለው የግጭት ወይም የጦርነት አዙሪት ውስጥ እየተዘፈቀች የምትቀጥል ከሆነ፤ እንደ ሐገር ከስተታችን እየተማርን፤ የጎደለውን እየሞላን፤ የተጣመመውን እያረቅን፤ የታሰበበት የልማት ዕቅድ መንደፍ ወይም መተግበር እንደማንችል ለማስታወስ ነው፡፡
የሐገር ዕድገትን አስቦ፣ ህጻናትን በትምህርት ኮትኩቶ አሳድጎ፤ በየመስኩ በማሰማራት የህዝቡን ህይወት የሚቀይር ሥራ ለመሥራት፤ ቢያንስ ከ30 ዓመታት የማያንስ የተቀናጀ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ እንደሚታወቀው፤ ሐገራችን ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ዘርግታ ልጆችዋን ማሰልጠን ከጀመረች ከአንድ ምዕተ ዓመት የበለጠ ዘመን መቁጠር አይቻልም፡፡ በዚህ አንድ ምዕተ ዓመት ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት ለመቅሰም የቻሉት ወጣቶች፤ ቀደም ሲል በኢጣሊያ ወራሪ ጦር፤ በኋላም በአፋኙ ወታደራዊ መንግስት ተገድለዋል፡፡ የቀሩትም ሐገራቸውን ጥለው በገፍ ተሰድደዋል፡፡ ሌሎቹም አፋኙን አገዛዝ ለመታገል ጠብመንጃ አንስተው ሜዳ ወጥተዋል፡፡ 30 ዓመታት በፈጀ የእርስ በእርስ ጦርነት ብዙ የሐገር ሐብት እና ውድ ጊዜ ባክኖ ቀርቷል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ዕድገት ሊታሰብ አይችልም፡፡
እንግዲህ ያለፉትን 300 ገደማ ዓመታት ያሳለፍነው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው፡፡ ሐገራችን ከጦርነት አንጻራዊ ፋታ ያገኘችው ባለፉት 25 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመኙ ዜጎች ሁሉ፤ የመጀመሪያ ሥራቸው ሊያደርጉት የሚገባቸው ጉዳይ ሐገሪቱ ወደ ግጭት የምትገባበትን በር ዝግ የማድረግ ሥራን ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ወደ ሌላ ቀውስ መግባት ችግሮቻችን ይበልጥ እየተወሳሰቡ እንዲሄዱ እና ሊታረሙ የማይችሉ ስህተቶች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ እና ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ አስተውለን መራመድ ይኖርብናል፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ግጭቶችንም በዚህ ዓይነት የምልከታ አንጻር መመርመር ይኖርብናል፡፡ ታዲያ በዚህ ዓይነት አውድ ውስጥ የሚሰራ ሚዲያ ወይም የውይይት መኪና ሊኖረው የሚገባው ሚና ምን መሆን አለበት? ይህን ጉዳይ በሌላ ክፍል እመለከተዋለሁ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy