ግብርናው
መዝገቡ ዋኘው
ከባዱን የክረምት ግዜ አሳልፈን ወደ በጋው ገብተናል፡፡ ክረምቱ የቀረ የቤት ስራ ያለበት ይመስል አሁንም አልፎ አልፎ መዝነቡን አላቆመም፡፡ ምናልባት አስተማማኝ ባልሆነው የአየር ንብረት ውስጥ የደረሱትን ሰብሎች ከወዲሁ መሸከፍ ይጠበቅብናል፡፡ አርሶ አደሮቻችን በአሁኑ ሰአት የክረምት የግብርና ስራዎቻቸውን አጠናቀው ወደ ምርት መሰብሰብ በመግባት ላይ በመሆናቸው አመቱን የለፉበት ምርት በቂ ትኩረት ባለመስጠት እንዳይበላሽ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
ይህንን አስመልክቶ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ በቂ ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ክረምቱ ከባድ ዝናብ ያስተናገደ በመሆኑ በዘንድሮው አመት ከፍተኛ የሆነ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል፡፡ የግብርናው ዘርፍ እድገት በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆኑ ለውጦች እንዲገኙ አስችሎአል፡፡
ዘረፉ የራሱንና የቤተሰቡን ሕይወት ለመለወጥ የቻለበትን ሁኔታ ፈጥሮአል፡፡ ምርቱን ከቤተሰቡ ፍጆታ አልፎ ለገበያ በመዋል ከፍተኛ የገንዘብ አቅም እንዲያገኝ፤ ስራውን ለማሳደግ የበቃበት የበለጠ ምርታማ ለመሆንም ተግቶና ነቅቶ የሚሰራበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡
በግብርና ባለሙያዎች በሚሰጠው ስልጠናና ተከታታይነት ያለው ትምሕርት አርሶ አደሩ ዘመናዊና ምርታማ የሆነ የአስተራረስ ዘዴን እንዲከተል በመደረጉ ከቀድሞዎቹ ግዜያት የተሻሉ ምርቶችን ማምረት ችሎአል፡፡ ሆኖም በምርት አሰባሰቡ ረገድ የግብርና ምርት የጥራት ችግርና ብክነት አሁንም ያልተቀረፉ ችግሮች ሁነው ዘልቀዋል፡፡ ይህንን ችግር መወጣት የሚቻለው አርሶ አደሩን በማስተማርና በማሳወቅ ነው መሆን ያለበት፡፡
በተለይም በድሕረ ምርት አያያዝና አጠባበቅ ጉድለት የተነሳ በዓመት አንድ ሦስተኛው የግብርና ምርታችን እንደሚባክን የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዲሁም በመንግስት የተካሄደ አንድ ጥናት ያረጋግጣል፡፡ ብክነት ብቻም ሳይሆን በማምረት ሂደት ውስጥ በአጨዳ፤ በመሰብሰብ፤ በውቂያ፤ በማበጠርና በመጓጓዝ፤ በማከማቸት ወቅት የምርት ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ሲባክን ይታያል፡፡
ምርት በወቅቱ ባለመታጨዱ ምክንያት ጊዜውን ባልጠበቀ ዝናብ ተበላሽቶ ለብክነትና ለጥራት መጓደል የሚጋለጥበት ሁኔታም በተደጋጋሚ ታይቶአል፡፡ ይህ ሁኔታ አገራችን የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመለወጥ እያደረገች ያለውን ጥረት የሚያሳንስና የአርሶ አደሩን ሕይወት ከድሕነት አዙሪት በፍጥነት እንዳይወጣ የሚያደርግ መሰናክል በመሆኑ በቀላሉ የሚታይ ችግር ስላልሆነ መፍትሄ ሊቀመጥለት ይገባል፡፡
አርሶ አደሩ ኋላቀር ከሆነ የግብርና ዘዴ ወጥቶ ዘመናዊ ቴክኒዮሎጂዎችን መጠቀምን ባሕሉ እንዲያደርግ በመንግስት በኩል ሰፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሂደቱ ግዜ ሊወስድ የሚችል ቢሆንም ዘመናዊ የእርሻ ምርቶችን ከማሳው ላይ ሊያጭድ፣ ሊሰበስብና ሊወቃበት የሚያስችለውን ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በእጁ እንዲገቡ ማድረግ ለችግሩ ወሳኝ መፍትሄ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
በማሕበር ተደራጅቶ የኢኮኖሚ አቅም ገንብቶ መሳሪያዎቹን በመንግስት በኩል ከውጭ እንዲገቡ ማድረግ ወይንም በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እንዲሰሩ በማድረግ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለአርሶ አደሩ የሚደርሱበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር ጀምሮ በየክልሎች የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል፡፡ በዚህ መንገድ እየሰሩ ያሉ የግል የግብርና ድርጅቶች የሰፋፊ እርሻ ባለቤቶች ዘመናዊ መሳሪያዎቹን በመጠቀም ውጤታማና ትርፋማ መሆን ችለዋል፡፡ ለዚህም ሲባል አርሶ አደሮቻችንን የዘመናዊ እርሻ መሳሪያዎች ተጠቃሚ ማድረግ በምርታቸው ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡
ይህንን እድል ለማግኘት መንገዶቹ ከጠበቡ ተደራጅቶና አቅም ገንብቶ መሳሪያዎቹን እስኪገዛና ስልጠናም ወስዶ ወደስራ አስኪገባ ድረስ አርሶ አደሩ በወቅቱ ማጨድ፤ መሰብሰብ፤ መውቃት እንዳለበትና ሰብሉን ከማጨድ ጀምሮ ጎተራው እስኪያስገባ ድረስ ያለው ሂደትም የምርት ጥራትን በማይጎዳና ብክነት በማይፈጥር ሁኔታ መስራት እንዳለበት ሰፊ የባለሙያዎች ድጋፍና ምክር ያስፈልገዋል፡፡ ዘመናዊ ቴክኒዮሎጂን በግዜና በሂደት መጠቀሙ ዘመናዊ ግብርናን ለማካሄድ የበለጠ የግብርና ምርትን ለመሰብሰብ ወሳኝ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር በመንግስት የተመሰረተው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አዳዲስ የግብርና ቴክኒዮሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ አርሶ አደሮቻችንና አርብቶ አደሮቻችንን የበለጠ ተጠቃሚ እንሚደሚያደርግ ይታመናል፡፡ የግብርናው ምርታማነት በበለጠ ደረጃ በማደጉ ድርቅን ለመቋቋም ያስቻለ አቅም በሀገር ደረጃ መገንባት ተችሎአል፡፡
አገራችን ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸውን ምርቶች በስፋትና በጥራት ማሳደግ ሀገራዊ ገቢያችንን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ሰፊ የውጭ ገበያን ይፈጥራል፡፡ በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በጥራት ከተመረቱ በውጭ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ስላላቸው በዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል፡፡
ከግብርናው ጋር በተያያዘ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከፍተኛ የሆነ የሰሊጥ ምርት በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡ የሰሊጥ ምርት አምራች በሆኑት ክልሎች የዘንድሮውን ምርት በክልሎቹ የሰው ኃይል ብቻ መሰብሰብ የሚቻል ባለመሆኑ ከልዩ ልዩ ክልሎች የጉልበት ሰራተኞች እንዲሳተፉ ጥሪ እያቀረቡ ያለበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡
ለዚህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የምርት ማሰባሰብ ስራ በሚሊዮን የሚቆጠር የሰው ኃይል የሚያስፈልግ ሁኖ በመገኘቱ ክልሎቹ በመላው ሀገሪቱ ስራውን ለመስራት የሚችሉ ዜጎች እንዲሰባሰቡ ጥሪ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ አጠቃላይ ምርቱን ለመሰብሰብ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡
ይህ የሚያሳው በእርግጥ ምርት ማሰባሰቡ ለተወሰነ ግዜ የሚሰራ ቢሆንም በስራ እድል ፈጠራ ረገድ አንድ ሚሊዮን ተኩል ለሆኑ ዜጎች ስራ መፍጠሩ ግብርናው ያለውን እምቅ ስራ የመፍጠር አቅም ያመለክታል፡፡ የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ የሆነው ግብርናው ወደፊትም ሰፊ የስራ እድሎችንና መስኮችን ለዜጎቻችን ይፈጥራል፡፡
ገና ያልተሰራባቸው ያልተነኩ እምቅ የስራ መስኮች በእርሻው፣ በከብት እርባታው፣ በንብ ማነቡ፣ በወተት ኃብቱ፣ በከብት ማድለቡ፣ በመስኖ ልማቱ፣ በደን ልማቱ፣ በተፈጥሮ እንክብካቤው ወዘተ በርካታ የስራ እድሎችን ሊፈጠር የሚችል ዘርፍ ነው፡፡ ግብርናው እያደጉ ለመጡት ሀገራዊ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ዋናና አስፈላጊ ግብአቶችን የሚያቀርብ በመሆኑ በተመጋጋቢነት ይሰራል፡፡
የግብርናው ዘርፍ በጣም ሰፊ ከመሆኑም አንጻር ብዙ ተሰርቶበታል፤ ይሁንና የሚፈለገው ውጤት ተገኝቶአል ለማለት አይቻልም፡፡ ግብርናችንን አሁን ካለበት ኋላቀር ደረጃ ወደ ዘመናዊ ሜካናይዝድ እርሻ ለማሸጋገር ስንችል የሰፊ ምርቶች ባለቤት ለመሆን እንበቃለን፡፡ በዚህ መስክ ሰፊ የሰው ኃይል ማሰልጠንና በስፋት ማሰማራት፤ ወደ ሕዝቡም ወርደው አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን እንዲያስተምሩ ማድረግ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ያስችለናል፡፡ ግብርናው ለኢንዱስትሪዎቻችንም የጥሬ እቃዎች አቅራቢ በመሆኑ በጥራትና በብቃት ያድግ ዘንድ ግድ ይላል፡፡