Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ግድቡ ዜጎች በሰንደቅ ዓላማው ስር ለመሰባሰባቸው ማሳያ ነው!

0 246

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ግድቡ ዜጎች በሰንደቅ ዓላማው ስር ለመሰባሰባቸው ማሳያ ነው!

                                                               ቶሎሳ ኡርጌሳ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪካቸው የሚያቆሙት የውሃ ላይ ሃውልት ነው። ህዝቦች ይህን ታላቅ ስራ በራሳቸው ገንዘብ፣ እውቀትና ጉልበት እያከናወኑ ያሉት በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። በዚህ ርብርባቸውም ግንባታውን 62 በመቶ ማድረሳቸውን ሰሞኑን የወጡ መረጃዎች ይፋ አድርገዋል። ግድቡ በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙም ወደ 6500 ሜጋ ዋት ከፍ እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል።

ታዲያ ይህ እውነታ የሚያሳየን ሃው አለ። ይኸውም ይህን የኢትዮጵያ ህዝቦች በሀገራቸው ውስጥ ምንም ነገር ማድረግ እንደሚችሉ እያሳዩ ያሉት በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው መሆኑን ነው። ወደፊትም በሰንደቅ ዓላማው ስር እሰከተሰባሰቡ ድረስ የግድቡን ግንባታ ከፍፃሜው እንደሚያደርሱ የሚያጠራጥር ነገር አይኖርም—በህዝብ ሙሉ ድጋፍ ያለው ማንኛውም ስራ በስኬት ለፍፃሜ እንደሚደርስ ካለፉት ጊዜያት ተግባሮቻቸው በሚገባ ተምረዋልና።

ርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ይህን ግድብ ሲገነቡ የሌሎች የተፋሰሱን ሀገራት ህዝቦች ፍላጎትን በመጋፋት አይደለም—የጋራ ተጠቃሚነትን በፍትሃዊ መንገድ እውን ለማድረግ ከማሰብ እንጂ። ይልቁንም ከዕድገታችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠልም በአባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መሰረቱ የተጣለውና የሀገራች ህዝቦች ችቦውን እየተቀባበበሉ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉትና ለፍፃሜው እንደሚያበቁት እየገለፁት ያለው ይህ ግድብ፤ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ነው። በቅርቡ የወጡ ጥናቶች እንደሚያመላክቱትም፤ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ 500 ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለበርካታ ዓመታት ያህል በቀን ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ የሚገኘው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ- ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ “በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ሆነን ማንኛውንም ነገር መፈፀም እንችላለን” የሚል መንፈስን መፍጠር የቻለና ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንድንተርፍ የሚያደርገን ነው። እናም ቢያንስ በእነዚህ ሁኔታዎች ብቻ የሀገራችንን ፍትሐዊና “አብረን እንጠቀም” የሚል ቀና አስተሳሰብን ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፤ ለየትኛውም ወገን ቢሆን።

ምንም እንኳን ትናንት ሐብትን በጋራና በፍትሐዊ ሁኔታ የመጠቀም መርህን ተከትላ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ የምትገኘው ሀገራችን፤ ዛሬም ከዚህ መርህዋ ዝንፍ የምትል አይሆንም። ግድቡም ወንድም የሆነውን የግብፅ ህዝብ እንደማይጎዳ፣ ይልቁንም ከግድቡ ግንባታ ተጠቃሚ እንደሚሆን በፅናት ታምናለች።

ይህ እምነቷ ከምንም ተነስቶ የሚባል አይደለም—መሬት ላይ ያለውን የግድቡን ግንባታ መሰረት ያደረገ እንጂ። ከዚህ በመነሳትም እምነቷንና የትኛውንም ወገን ያለመጉዳት መርህዋን በተለያዩ ወቅቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መንግስታትና ህዝቦች አስረድታለች።

ታዲያ ይህን የኢፌዴሪ መንግስት በጋራ የመልማት መርህን ቀደም ሲል ጎረቤት ሱዳን፣ አሁን ደግሞ ወንድሞቻችን ግብፆች እውነታውን እየተረዱ የመጡ ይመስላል—ብቅ ጥልም የሚለው አቋማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚገነባ ፕሮጀክት በመርህ ላይ የተመሰረተ እንጂ በዘፈቀደ የሚመራ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝቦች የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ዓላማ የላቸውም።

የህዳሴው ግድብ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመርኩዞ ሁሉም ሀገራት እንዲጠቀሙ ከማለም የመነጨ ነው። ይህን የትኛውም ሀገር ሊገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም የሀገራችን ህዝቦችም ይሁኑ መንግስት ለህዝብ የሚያስቡ እንጂ የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች ተጠቃሚነትን የሚጋፉ አይደሉም። በሰንደቅ ዓላማው ስር ተሰባስበው ማናቸውንም ተግባራት መፈፀም እንዲችሉም ለዓለም አሳይተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን ህዝቦች በሰንደቅ ዓላማቸው ስር ተሰባስበው ልማትን ለማፋጠን የሚያደርጉት አንድ ማሳያ ነው። እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝቦች አንድነት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው እንዲሁም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕኑ ፍላጎትንና እምነትን መሰረት ያደረገ ነው። የዚህ ዕውነታ ነፀብራቅ መሰባሰቢያ ጥላ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማው መሆኑ አይካድም። እናም የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ህዝቦች ይህን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ጠብቀው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን የትኛውም ወገን ሊያውቀው የሚገባ ይመስለኛል።

ሰንደቅ ዓላማው በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ የተቀየሰው ህዳሴ መሰረትም ነው። ከዚህ አኳያም ሀገራችን በምጣኔ-ሃብት እንድታድግ፣ የዜጎችን ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚነት እንዲጎለብት፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ብሎም በርካታ ተግባራት ገቢራዊ ሆነው ውጤት ተገኝቶባቸዋል— በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ። ለዚህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ፍትህ መረጋገጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተ ይመስለኛል።

ለነገሩ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለውን የአንድነትና የእኩልነት ዓርማን አንግቦ በየደረጃው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ የሚገኘው የሀገራችን ህዝብ አሁን ካለበት ማንነተቱ መላቀቅና መለወጥ አይፈልግም ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም የቀደምት አበውንና እመውን የስልጣኔ ማንነት እየተመለከተ፣ የሀገሩን የድህነትና የኋላ ቀርነት ግርዶሽን በመቅደድ ወደ አዲስ ማንነቱ ተቀይሮ ለመታደስ የማይፈልግ ዜጋ ይኖራል ብሎ ማሰብ ስለማይቻል ነው።

በዚህ መንፈስ መሰረትም የትናንት የተመፅዋች ታሪኩን ለመቀየር የሀገራችን ህዝብ በሰንደቅ ዓላማው ጥላ ስር ተሰባስቦ የህዳሴውን ጉዞ ለማሳለጥ የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ላይ ይገኛል። ግድቡ “የባንዴራ ፕሮጀክት ነው” የሚባለውም ለዚህ ይመስለኛል። ይህ ፕሮጀክት ከመሰረተ-ድንጋይ መጣል ከምሮ አሁን እስከ ደረሰበት 62 በመቶ እድገቱ ድረስ የዚህ ሀገር ህዝብ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከደቂቅ እስከ ሊቅ ድረስ የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል። የሰንደቅ ዓላማውን ፋይዳን ከዚህ አኳያ እንኳን ቀለል አድርገን ብንመነዝረው፤ ህዝቦች የሚያሰሩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ካገኙ በሰንደቃቸው ስር ሆነው በጋራ የማያከናውኑት ነገር እንደማይኖር እንገነዘባለን። ሰንደቃችንን መንከባከብ ይህን መሰሉን ልማት እውን እንድናደርግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ መረዳት ይገባል።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy