Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥበትና ትምክህት የኪራይ ሰብሳቢነት ውላጆች…  

0 324

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥበትና ትምክህትኪራይ ሰብሳቢነት ውላጆች…  

አባ መላኩ

በቅርቡ በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ  የአገራችን አካባቢዎች  ብሄር ተኮር  ግጭቶችን ተመልክተናል። የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ልብ የሰበረ ግጭት ነበር። ሟቹም  ገዳዩም፣  ተፈናቋዩም  አፈናቃዩም፣ ጎጂውም ተጎጂውም  ወንድማማች  ህዝቦች ናቸው። የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ (የሶማሌ)  ህዝቦች መለየት በማይቻልበት ሁኔታ በባህልም ሆና በኃይማኖት አንድ ህዝብ ናቸው።  እነዚህ ህዝቦች  የጋራ ድንበር  ተጋሪዎች  እና አንዱ በሌላኛው ክልል ውስጥ ለዘመናት አብረው የኖሩ  ህዝቦች  ብቻ ሳይሆኑ  በበርካታ ነገሮች ተሳስረው አንዱ ሌላውን መስሎ ሳይሆን  ሆኖ እየኖሩ  ያሉ ህዝቦች ናቸው።   

አንዱ ካላንዱ ባዶ ባይሆን እንኳን ጎዶሎ ነው። የእነዚህ ህዝቦች አኗኗር በበርካታ ነገሮች እጅግ የጠበቀ አንድነት የሚንጸባረቅበት ከባህል እስከ ሃይማኖት ጠንካራ ትስስር የሚስተዋልበት ነው።  እነዚህ ህዝቦች ለዘመናት አብረው ኖረዋል፣  ክፉውንም ደጉንም አብረው አሳለፈዋል። እነዚህ ህዝቦች በርካታ መልካምና መጥፎ ታሪክን ተጋርተዋል፤ ተጋብተው ተዋልደዋል፤ በደም ተሳስረዋል፤ አንዱ ለሌላው ቆስሏል፣ ሞቷል። አዎ መለየት በማየቻልበት ሁኔታ አንዱ ሌላውን ሆኗል። ይሁንና  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድንበር አካባቢዎች  በተቀሰቀሱ ሁከቶች የእነዚህን ህዝቦች አብሮነትን ተፈታትኖታል። በጽንፈኞች የፖለቲካ ሴራ ሳቢያ በርካታ ንጹሃን ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል።

የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ድንበር ሳይለየቻው  ቋንቋ ሳይገድባቸው ተጋብተው ተዋልደው ያላቸውን ተሰጣጥተው፣ ተሳስበውና ተደጋግፈው ኖረዋል፤ በዕርግጠኝነት  ነገም ይኖራሉ። ጽንፈኛውና መርዘኛው አካል የቱንም ያህል ለመነጣጠል ቢሰራም አይሳካለትም፤ ምክንያቱም እነዚህ ህዝቦች በጠንካራ የአብሮነት ገመድ የተሳሰሩ በመሆናቸው ናቸው። የእነዚህ  ህዝቦች የስኬት ምንጮቻቸው  አብሮነታቸውና እርስ በርስ መደጋገፋቸው ነው። እነዚህን ህዝቦች ወዳልተፈለገ ነገር እንዲያመሩ ግጭት እንዲፈጠርና እንዲስፋፋ  ያደረጉት  ተማርኩ፣ ዘመናዊ ሆንኩ የሚለው የግል ጥቅሙን የሚያሳድደው በጥበትና ትምክህት አስተሳሰብ የተጨማለቀው አካል  ነው። በእንዲህ ያለ ግጭት አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ አካል አይኖርም።  

ጽንፈኛ ፖለቲከኞች  ስልጣን ናፋቂና በስልጣን ሱስ  የናወዙ በመሆናቸው በየትኛውም መንገድ ይሁን ወደ ስልጣን ማማው መሰቀል እንጂ ሂደቱ አያስጨንቃቸውም። የህዝቦች ህይወት መጥፋት፣ አካል መጉደል፣ ደም መፋሰስ፣ መፈናቀልና እንግልት ለጠባቡና ትምክህት ሃይሎች  ምናቸውም አይደል። የአገር አንድነት፣ የህዝቦች አብሮነት ለጽንፈኛው የፖለቲካ ሃይል ምኑም አይደል። ጽንፈኛው  ሃይል  ለዓላማው ስኬት እጅግ ስሜት ኮርኳሪ ነገሮችን በማራገብ የህዝቦች የአብሮ መኖር እሴቶችን ክፉኛ ጎድቷል። ይህን  እኩይ ተግባር  መዋጋት የሁላችንም  አገር ወዳድ ዜጎች  ግዴታ ሊሆን ይገባል። ኪራይ ሰብሳቢዎች የተጀመረው የለውጥ ንፋስ እንዳያገኛቸው በመስጋት በአገሪቱ መረጋጋት እንዳይኖር  ሁከትና ነውጥ እንዲስፋፋ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በመሆኑም  አገር ወዳድ ዜጎች  የእነዚህን  ሃይሎች ድብቅ  አጀንዳ ማጋለጥ ይጠበቅብናል። እነዚህ አካላት በሚዲያዎቻቸው  በተለይ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ የሚያደርጉትን ህዝቦችን የመነጣጠል መርዘኛ ፖለቲካ ልናወግዘው  ይገባል።

ጽንፈኛው ሃይል አገርን ማፍረስ እንጂ የአገር ዕድገትን አይመኝም፤ ውድመትን እንጂ ልማትን አያውቅም፤ ህዝቦችን መነጣጠል እንጂ የህዝቦች አንድነትን አይመኝም።  አዎ ልማት እንጂ ውድመት ጊዜ አይጠይቅም። ኪራይ ሰብሳቢው ሃይል በሁለቱ ህዝቦች መካከል  በፈጠረው ቀውስ  በአጭር ጊዜ  በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ ቀውሶች በአገራችን እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።  ይህ የጥፋት ሃይል አልተረዳውም  እንጂ ህዝቦችን በማጋጨት ዘለቄታዊ የፖለቲካ ትርፍ አይገኝም። ከነሶሪያ፣ ኢራቅ፣ የመንና ሊቢያ ልንማር ይገባል።  የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት አብረው  በመኖራቸው በሃይማኖት፣ በባህል  ተሳስረዋል፣ ተጋብተው ተዋልደው፣ በደምና በስጋ  ተሳስረው፣ ተከባብረውና እርስ በርስ ተቻችለው  ለዘመናት ኖረዋል። እነዚህን ህዝቦች  ለመነጣጠል መሯሯጥ  በየትኛውም  መስፈርት ተቀባይነት አይኖረውም። ጽንፈኛው ሃይል አምና  በአማራና  ትግራይ  ዘንድሮ ደግሞ  በኦሮሞና ሶማሌ  ህዝቦች መካከል ግጭት በመቀስቀስ  ህይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል። ጽንፈኛው ሃይል ለግጭት ምክንያት የሆነው  የፌዴራል ስርዓቱ አወቃቀር እንደሆነ አድርጎ  ለማቅረብ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች አብረው እንዳይኖሩ እንቅፋት የሚፈጥርበት አንዳችም ነገር የለም።    

በቀጣይ እንዲህ ያሉ ቅጥ ያጡ አካሄዶች ዳግም በአገራችን  እንዳይከሰቱ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። መንግስትም ለህዝብ  ቅሬታዎች በወቅቱ ምላሽ ይሰጥ፤ እንዲሁም  በእንዲህ ያለ ጽንፍ የወጣ ተግገባር ላይ የተሳተፉ፣ ለሁከቱ ምቹ ሁኔታ  የፈጠሩ፣ ወዘተ  ማንኛውም  ሃይሎች  ከህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል። ከዚህ ባሻገር መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ይጠናከሩ፣ ልማት አቅም በፈቀደ መጠን  የፋጠን። አዎ ልማት አቅምና ጊዜ  እንደሚጠይቅ  ይታወቃል። አልሳካ አለ እንጂ ቢሳካ ለእያንዳንዱ ወረዳ  ሁሉንም መሰረተ ልማት አሁኑኑ ብናሟላ መልካም ነበር። አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ሁሉም ነገር በአንዴ ሊሟላ  አይቻልም። ይሁንና ህዝብን በማሳተፍ ልማት መፋጠን እንደምንችል ባለፉት ዓመታት የነበሩ ተሞክሮዎችን አመላካች ናቸው። በመሆኑም በግጭት የተጎዱ ህዝቦች ህይወታቸው እንዲስተካከል የፌዴራል መንግስትም ሆነ የክልል መንግስታቶች የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሁሉም ችግሮች  በአንዴ ሊፈቱ ባይችሉም  በቅደም ተከተል እንደአንገብጋቢነታቸው ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል። የመጀመሪያውና ዋናው ነገር ሰላም ማስፈን ነው። መንግስት አሁን ላይ ትኩረት ያደረገው  ህዝቡን በማረጋጋትና ሰላምን በማስፈን ተግባር ላይ መሆኑ ተገቢ ነው። ሰላምን የማስጠበቅ ተግባር  የመንግስት ተግገባር ብቻ እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። መንግስት ብቻ ሳይሆን  ሁላችንም  በሰላማችን ልንደራደር አይገባም ማለት ይኖርብናል።

አገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻለችው ህዝብና መንግስት በቅርበት መስራት በመቻላቸው ነው።  ሰላማችን ዘላቂነትና  አስተማማኝ  እንዲሆን መንግስት የጀመረው ድህነትን የማጥፋት ሂደት ማጧጧፍ ይኖርብናል። እንዲሁም አገራችን እያስመዘገበች  ካለው ፈጣን ዕድገት ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን  የተደገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ድህነት የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ነው። በመሆኑም ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በቀጣይም እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች ቢከሰቱ እንኳን ግጭቶችን በባህላዊና ኃይማኖታዊ መንገድ መፍታት ኢትዮጵያዊ ባህላችን በመሆኑ ይህን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ሁላችንም የአቅማችንን ልንደግፍ ይገባል። መንግስትም አንድነታችንን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንድናደርግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል። የኦሮሞዎችም ሆኑ ሶማሌዎች መፈናቀል ለእኛ እኩል ጉዳታችን ነው።  

በርካታ ኦሮሞዎችን በቤታቸው ሸሽገው ከጥቃት የተከላከሉት ሶማሌዎች ናቸው፤ በተመሳሳይ በርካታ ሶማሌዎችን  በቤታቸው ሸሽገው ከጥቃት የተከላከሉት ኦሮሞዎች ናቸው። ለዚህ ነው  በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል በታሪክ ግጭት ተነስቶ አያውቅም የሚባለው።  ባለፉት ስርዓቶች  ገዢ መደባት የሚፈጽሙት በደልና አድልዖ ይኑር እንጂ አንዱ ህዝብ ሌላው ላይ ያደረሰው አንዳችም በደል አልነበረም።  ለዚህም ይመስለኛል እነዚያ ስርዓቶች ሲወድቁ ህዝቦች ወደግጭት አላመሩት።   አንዳንድ አካላት በድንበር አካባቢዎች የሚፈጠሩ  ግጭቶች  አጠቃላይ የፌዴራል ስርዓቱ ችግሮች አድርገው ለማቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ።  በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች በአብዛኛው አርብቶ አደሮች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለግጦሽና ለውሃ በሚያደርጉት እሽቅድምድም አልፎ አልፎ ለግጭት ማድረጋቸው አይቀርም።  እነዚህ በውሱን ሃብቶች ሳቢያ የሚፈጠሩ ግጭቶች የፌዴራል ስርዓቱ  ችግሮች ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም።  ጠባቡና ትምክህተኛው ሃይል ግጭቶችን ለመቀስቀስ የሚጠቀምባቸውን የጥፋት  ስልቶች   ማጋለጥ ከሰላም ወዳዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር  ነው።

የመልካም አስተዳድር እጦት ሌላው የግጭት መንስዔ ስለሚሆን መንግስት ህብረተሰቡ ቅሬታ ላነሳባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ መስጠት መቻል አለበት። በየአካባቢው ያሉ አመራሮች የህዝብን ችግር ያዳምጡ በወቅቱ ምላሽ ይስጡ። ምላሽ ሁሌም አዎንታዊ ላይሆን ይችላል። በወቅቱ  የሚሰጥ “አይሆንም” የሚል ምላሽ በራሱ  ተገቢና ትክክለኛ መልስ ነው። የዘገየ ፍትህ ከተከለከለ ይቆጣራል እንደሚባለው መንግስት ሁሌም የህዝብን የልብ ትርታ በቅርበት ማድመጥ ይኖርበታል። ልማትን የምናፋጥን እና መልካም አስተዳደርን የምናጎለብት ከሆነ የውጭ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ የውስጥ ጠላታችን  የሆኑት የጥበትና ትምክህት ተግባርና አመለካከት ቦታ ሊያገኙ አይችሉም። ለርካታዎቹ  የአገራችን ችግሮች ምክንያት ውጫዊ አይደሉም፤  በመሆኑም መፍትሄያቸውም ውስጣዊ ናቸው።

የጥበትና ትምክህት ሃይሎች እንኳን ህዝብን ቤተሰብን የሚነጣጥል መሰሪ አካሄድን የሚከተሉ በመሆናቸው ተገቢው ጥንቃቄ ካላደረግን እንዲሁም አካሄዳቸውን ካልነቃንባቸው አገራችንን ወደቀውስ ሊያመሯት ይችላሉ። የጽንፈኛው አካል የበሬ ወለደ ፖለቲካው ማንንም ስሜታዊ ያደርጋል።  ማንንም ያሳስታል። በተለይ ወጣቶች ላይ ይበረታል። በመሆኑም ወጣቶች የእነዚህን መሰሪ ሃይሎች  አካሄድ ሊነቁባቸው ይገባል።  የኪራይ ሰብሳቢነት  አስተሳሰብና ተግባር የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋንኛ ፈተና ነው።  በመሆኑም  ይህን እኩይ ተግባር በጋራ ልንታገለው ይገባል።  ኪራይ ሰብሳቢነት ውላጅ የሆኑት ጥበትንና ትምክህትን  ልንታገላቸውና ልናሸንፋቸው የምንችለው ልማትን በማፋጠንና  መልካም አስተዳደርን በማጎልበት ብቻ በመሆኑ ሁላችንም የየድርሻችንን ሃላፊነት ልንወጣ ይገባል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy