Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት

0 268

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት

                                                     ደስታ ኃይሉ

በአገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያለው ቦታ ግልፅ ነው። ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የራስን ማንነት አስከብሮ የሌሎችንም በዚያው ልክ ማክበር ነው። ከዚህ በተቃራኒ የሚታዩት የጥበትና የትምክህት አስተሳሰቦች በፌዴራላዊ ሥርዓታችን ውስጥ ቦታ የሌላቸውና የሚወገዙ ናቸው። እናም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲያብብ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ታሪኮች ተደምረው የሚፈጥሩት ውህደት ነው። ይህ የአገራችን ነባራዊ ክስተትን በልዩነት ውስጥ ባለ አንድነት ሊያስተናግድ የሚችለው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ነው። ለኢትዮጵያ ብቸኛው አማራጭ ፌዴራላዊ ሥርዓትን መከተል መሆኑን የሥርዓቱ ባለቤቶች የሆኑት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፅናት አምነውበት እንዲተገበር የወሰኑት።

ይህ ውሳኔያቸውም ለዛሬው እነርሱነታቸው ያበቃቸው ከመሆኑም በላይ፤ የፌዴራል ሥርዓቱ አንዳንድ ወገኖችና ፅንፈኞች ሃቁን ካለመገንዘብ አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት እንደሚሉት ዓይነት በድንቡሽት ላይ የተገነባ ቤት አለመሆኑንም አሳይተዋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ በህዝቦች ፈቃድ ተረጋግጦ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን ከ26 ዓመታት በኋላም ቢሆን በሚገባ ማረጋገጥ ስለቻሉ ነው።

ለነገሩ አንዳንዶቹ ይህን ሃቅ እያዩ እንኳን በማንኛው በማደግ ላይ በሚገኝ ሀገር ውሰጥ እንደሚፈጠረው በግጦሽ ቦታና በውኃ ምክንያት በአንዳንድ የሀገራችን ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ነባራዊ ክሰተቶችን እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪዎች ከአንዳንድ አካባቢዎች ተባረሩ በሚሉ የፌዴራል ሥርዓቱ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት ፌዴራሊዝሙ አደጋ ተደቅኖበታል ይላሉ። ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን የዚህን ሀገር ፌዴራሊዝም ካለመገንዘብ የሚመነጭ ነው።

የፌዴራሊዝም መሰረት ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ነው። ከ26 ዓመት ጉዞ መማር የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው። በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡ የበላይነት ባገኘባቸው አካባቢዎች እና ክልሎች ምንም ዓይነት ግጭት አይከሰትም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው። ይህንን ይበልጥ ለማስቀጠል አልፎ አልፎ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚስተዋሉትን የጠባብነት እና የትምክህት አስተሳሰቦች በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል።

እርግጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በብሔሮች መካከል የአመለካከት ዝምድና መፍጠር ችሏል፡፡ በመሆኑም ሀገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሰ እሴት ነው፡፡ የትምክትና ጠባብነት ፈተናዎች በአገሪቱ ቢኖሩም በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መሸነፋቸው አይቀሬ ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት ትምክህትና ጠባብነትን ለመዋጋት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ሆኖም አመለካከቱ አልፎ አልፎ የሚያንሰራራው በኪራይ ሰብሳቢነትና ባልተገባ ጥቅም በሚሹት አካላት አማካኝነት በመሆኑ ሁለቱን ማነቆዎች ከሕዝቡ ጋር በመታገል ለውጡን ማምጣት ይቻላል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኘነትን ከአራት መሰረታዊ ትርጓሜዎቹ አኳያ ማየት ይቻላል። እነርሱም ማንነትን ማወቅ፣ የሌሎችን ማንነት ማወቅ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እና አካባቢን ማልማት ናቸው።

ማንነትን ከማወቅ አኳያ የተለያዩ ፍላጎቶችና ጥቅሞችን መለየት ያስፈልጋል። የጋራ የሆኑ ባህሪያትን መለየትንም እንዲሁ። እንደ አቶ ሕላዊ የሌሎችን ማንነት በማወቅ ረገድም፣ ከሌሎች ጋር ያለውን የጋራ ፍላጎትና ጥቅም መለየት ያስፈልጋል።

እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመብለጥም ሆነ በማነስ ስሜት ውስጥ ሳይገባ በጋራ መጠቀምን ያካትታል። አካባቢን ከማልማት አኳያም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ከባቢን በተገቢው መንገድ ለልማት የማዋል ሁኔታን የሚያካትት ነው።

ብዙ ሕዝቦች ባሉበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነትን በጤናማ አስተሳሰብ በመምራት በመካከላቸው ፍቅር፣ መከባበርና መተሳሰብ እንዲዳብር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ይህ ግንኙነት ጤናማ ባልሆነ አስተሳሰብ በሚመራበት ጊዜ ግጭት መከሰቱ አይቀርም። በኢትዮጵያ የተማከለ አስተዳደር ከተመሠረተበት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ በማኅበረሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተመላበት፣ ግጭት የጠነከረበት፣ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ሰላም ያጣችበት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

እርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ‘የትምክህት ሐሳባችንን በነፃነት እንግለጽ፣ አትንኩን’ የማለት ነገር ይታያል፡፡ ይህንን አመለካከት መጠጊያ የሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡

ህገ- መንግሥቱ አስተሳሰባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግም ሆነ መንግስት የተለየና የተሳሳተ ሐሳብ ያላቸውም ሰዎች ቢሆኑም ሃሳባቸውን ለምን ይገልጻሉ የሚል ብዥታ ኖሯቸው የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና ለማረጋገጥና ህዝባዊ ወገንተኝነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ህዝብ የሚቆረቆር፣ የሌላውም ህዝብ መቆርቆር ይኖርበታል። ምክንያቱም አንዱ ሌላኛውን በእኩልነት ሲከብር በአንፃሩ ደግሞ  መከበርን ያተርፋል፡፡ እርግጥ ያለፈው ታሪክ አንድን ሕዝብ የራሱ ዘር ከሌላው ዘር በከፋ መልኩ በድሎት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ግን ገዥዎችን እንጂ ህዝብን የሚመለከት አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው የትምክህትና የጥበት ሃይሎች ያለፉትን የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶችን በማንሳት አንድን ህዝብ ለመኮነን ይሞክራሉ፡፡ ይህ ፍፁም ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡

ዛሬ ላይ አንድ ብሔር የበላይ በሌለበት ሁኔታ፣ እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በማጋጋም ትርፍ ለማግኘት መሞከር ተገቢ አይመስለኝም። የሚፈልግ አካል ካለም ሊሳካለት አይችልም፡፡ ምክንያቱም እየተካሄደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እሳቤ ውጤት እያስገኘ ከመሆኑም በላይ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ ላይ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ በመቀጠሉ ነው፡፡

እርግጥ አንዳንድ የትምክህት ኃይሎች ህብረተሰቡን በተሳሳተ ጎዳና ሊመሩት ይችላሉ። አስተሳሰቡ እነርሱ የሚያምኑበትን ‘ከሁሉም የበላይ ነን፣ ከእኛ ወዲያ ለአሳር’ የሚል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ምልከታ በመሆኑ ሀገራችን በምትከተለው ዴሞክራሲያዊ መንገድ ፍፁም ተቀባይነት የለውም።

እንዲህ ዓይነቱ ፌዴራላዊ ስርዓቱም ይሁን ህዝቡ የማይደግፈውን የዴሞክራሲ ፀር አስተሳሰብን ሁሉም በየደረጃው ሊታገለው የሚገባ ይመስለኛል። አስተሳሰቡን ‘መንግስት ለብቻው ይወጣው’ ብለን የምናልፈው ከሆነ፣ ምንም ለውጥ ሊመጣ አይችልም። መንግስት ከህዝቡ ጋር ካልሆነ በስተቀር ለብቻው የሚፈፅመው አንዳችም ነገር ሊኖር አይችልምና።

ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ይህን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለማንገስ በምንም መንገድ የማይገናኙ “አሳትና ጭዶች” ሲተባበበሩ መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። ይሁንና በፌዴራላዊ ስርዓታችን ውስጥ ቦታ ያለው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንጂ የጥበትና የትምክህት ቅሪቶች አለመሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy